በአሥረኛ ሣምንት ጨዋታዎች ላይ ጎልተው በወጡ ተጫዋቾች ይህንን ምርጥ ቡድን ሠርተናል።
አደራደር 4-2-2-2
ግብ ጠባቂ
ቢኒያም ገነቱ – ወላይታ ድቻ
የጦና ንቦቹ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በረቱበት ጨዋታ የግብ ጠባቂው ብቃት የሚደነቅ ነበር። በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ ያዳናቸው በርካታ ፈታኝ ሙከራዎች በቦታው ያለ ተቀናቃኝ ተመራጭ አድርገውታል።
ተከላካዮች
ወጋየሁ ቡርቃ – ሻሸመኔ ከተማ
ሻሸመኔዎች በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረባቸው ግብ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ነጥብ ሲጋሩ የቀኝ መስመር ተከላካዩ ወጋየሁ የተጋጣሚን የመስመር እንቅስቃሴ የገታበት እና የአንድ ለአንድ ግንኙነቶችን ያሸነፍ የነበረበት መንገድ ግሩም ነበር።
እስማኤል አብዱልጋኒዩ – ድሬዳዋ ከተማ
ብርቱካናማዎቹ ኢትዮጵያ መድን ላይ ወሳኝ ድል ሲቀዳጁ በተደጋጋሚ ጨዋታዎች ላይ ትኩረት ሳቢ እየሆነ የመጣው የመሃል ተከላካዩ እስማኤል በተለይም ቡድኑ በሁለተኛው አጋማሽ ጫና ውስጥ ሲገባ ኳሶችን በአንድ ንክኪ ከአደጋ ክልል ሲያርቅበት የነበረው መንገድ ለቡድኑ እፎይታን የሰጠ ነበር።
አዛርያስ አቤል – ወላይታ ድቻ
በወላይታ ድቻ ቤት ከኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታ በኋላ ሁለተኛ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታውን ያደረገው አዛርያስ ቡድኑ ንግድ ባንክ ላይ አሸናፊ የሆነበትን ግብ በግንባር ገጭቶ ከማስቆጠሩ ባሻገር በቦታው ያደረገው እንቅስቃሴ በምርጥ ቡድናችን ውስጥ እንዲካተት አስችሎታል።
ሳሙኤል ዮሐንስ – ሀዲያ ሆሳዕና
ነብሮቹ ከፈረሠኞቹ ጋር ያለ ግብ በተለያዩበት ጨዋታ የመስመር ተከላካዩ ሳሙኤል ብቃት የሚደነቅ ነበር። በጨዋታው የመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ግብ ለማስቆጠር ተቃርቦ በግቡ የግራ ቋሚ ሲመለስበት በተደጋጋሚ ይፈጥራቸው የነበሩ ዕድሎች እና ስኬታማ የመከላከል እንቅስቃሴው በቦታው ተመራጭ አድርጎታል።
አማካዮች
ብዙዓየሁ ሠይፉ – ወላይታ ድቻ
የጦና ንቦቹ የሊጉን መሪ ንግድ ባንክን ያለመሸነፍ ጉዞ ሲገቱ በዕረፍት የለሽ እንቅስቃሴው ከሣምንት ሣምንት የተሳካ ጊዜ እያሳለፈ የሚገኘው ብዙዓየሁ አስተዋጽኦ የጎላ የነበር ሲሆን በተለይም በመልሶ ማጥቃት የሚሄዱ ኳሶችን ከማቋረጡ በላይ የሚያገኘውን ኳስ በተረጋጋ ሁኔታ ከራሱ የግብ ክልል ይዞ የሚወጣበት መንገድ ማራኪ ነበር።
አበባየሁ ሀጂሶ – ወላይታ ድቻ
እንደ ቡድን አጋሩ ብዙዓየሁ ሁሉ አማካይ ስፍራ ላይ የተሳካ ቀን ያሳለፈው አበባየሁ በተለይም ወሳኙ አማካይ አብነት ደምሴ በጉዳት ከወጣ በኋላ የቡድኑን ሚዛን በመጠበቅ ኃላፊነቱን በአግባቡ የተወጣ ሲሆን ከሳጥን ሳጥን የሚያደርጋቸው ሩጫዎቹ አስደናቂ ነበሩ።
አጥቂዎች
አብዱልቃድር ናስር – ሻሸመኔ ከተማ
ሻሸመኔዎች በውድድር ዓመቱ ብቸኛ ድላቸውን ለማግኘት እጅግ ተቃርበው በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረባቸው ግብ ነጥብ ሲጋሩ ሁለተኛ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታውን ያደረገው አብዱልቃድር ካደረገው እንቅስቃሴ ባሻገር የቡድኑን ብቸኛ ግብም ክህሎት በተሞላበት አጨራረስ ማስቆጠር ችሏል።
ቢኒያም ፍቅሩ – ወላይታ ድቻ
የጦና ንቦቹ አጥቂ የሆነው ቢኒያም በጨዋታ ሣምንቱ ግብ ማስቆጠር ባይችልም የንግድ ባንክ ተከላካዮች ላይ ሥራ ከማብዛቱ ባሻገር እጅግ ሳቢ በሆነ የግል ክህሎቱ ለተመልካች አዝናኝ እንቅስቃሴ ሲያደርግ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎችም በውድድሩ ከታዩ ድንቅ ጎሎች መካከል አንዱን ሊያስቆጥር እጅግ ተቃርቦ በግቡ አግዳሚ ተመልሶበታል።
ምንይሉ ወንድሙ – መቻል
መቻል ሀዋሳ ከተማን አሸንፎ ነጥቡን ከሊጉ መሪ ንግድ ባንክ ጋር ዕኩል ሲያደርግ የምንይሉ ብቃት ድንቅ ነበር። አጥቂው የቡድኑን የመጀመሪያ ግብ በግንባር በመግጨት ማስቆጠር ሲችል የሀዋሳው አጥቂ ዓሊ ሱሌይማን ወደ ግብ የላከውን ፈታኝ ኳስም በግሩም ቅልጥፍና ከመስመር ላይ ያገደበት መንገድ ለቡድኑ ውጤት ጉልህ አስተዋጽኦ ነበረው።
ጌታነህ ከበደ – ፋሲል ከነማ
በተከታታይ የጨዋታ ሣምንታት የቡድኑን የማሸነፊያ ግቦች እያስቆጠረ ሚናውን እያጎላ የመጣው ጌታነህ ባሳለፍነው ሣምንትም ወልቂጤ ከተማን 1ለ0 ሲያሸንፉ እጅግ ግሩም የሆነ የቅጣት ምት ግብ በማስቆጠር ቡድኑን ለተከታታይ ድል አብቅቷል።
አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ – ወላይታ ድቻ
በሁሉም ተመልካቾች ዘንድ ከሣምንት ሣምንት ለመታየት ከሚናፈቁ ቡድኖች መካከል አንዱ የሆነውን ወላይታ ድቻን የሚያሰለጥኑት አሰልጣኝ ያሬድ ቡድናቸው ብርቱ ፉክክር አድርጎ የሊጉን መሪ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ያለመሸነፍ ጉዞ ሲገታ የመረጡት አጨዋወት እና በተለይም ወሳኙ አማካይ አብነት ደምሴ በጉዳት ለመውጣት ከተገደደ በኋላም የቡድኑን ሚዛን ያስጠበቁበት መንገድ እጅግ ግሩም የነበር ሲሆን የዚህን ሣምንት ምርጥ አሥራአንድ ቡድናችንንም እንዲመሩ መርጠናቸዋል።
ተጠባባቂዎች
ፖሉማ ፖጁ – ሀምበርቾ
የአብሥራ ሙሉጌታ – ሻሸመኔ ከተማ
አህመድ ረሺድ – አዳማ ከተማ
አብዱልሰላም የሱፍ – ሀምበርቾ
ሽመልስ በቀለ – መቻል
ካርሎስ ዳምጠው – ድሬዳዋ ከተማ
ዮሴፍ ታረቀኝ – አዳማ ከተማ
አቡበከር ሳኒ – ወልቂጤ ከተማ