እጅግ አስገራሚ የሜዳ ላይ ፉክክርን በተመለከትንበት ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ከዕረፍት በኋላ ባስቆጠሯቸው ግቦች ኢትዮጵያ መድንን 4ለ1 ረተው መሪነታቸውን አጠናክረዋል።
ሁለቱም ቡድኖች ባለፈው ሳምንት በወላይታ ድቻ እና ድሬዳዋ ከተማ በተመሳሳይ ካስተናገዷቸው ሽንፈቶች አኳያ ለዛሬው ጨዋታ ቅያሪዎችን አድርገዋል። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባደረገው የሦስት ተጫዋች ቅያሪ ገናናው ረጋሳ ፣ ብሩክ እንዳለ እና ሲሞን ፒተርን ፣ በእንዳለ ዮሐንስ ፣ ሀብታሙ ሸዋለም እና አዲስ ግደይ ሲተኳቸው በኢትዮጵያ መድን በኩል የአራት ተጫዋቾች ለውጥ ተደርጓል። አዲስ ተስፋዬ ፣ አቡበከር ወንድሙ ፣ ኦሊሴማ ቺኔዱ እና ቼኩዌመካ ጎድሰን ወጥተው ተካልኝ ደጀኔ ፣ አሚር ሙደሲር ፣ ብሩክ ሙሉጌታ እና ያሬድ ዳርዛ ተተክተዋል።
የዕለቱ ዳኛ አሸብር ሰቦቃ ፊሽካቸውን በማሰማት ጨዋታውን ካስጀመሩበት ደቂቃ አንስቶ ጠንካራ ፉክክርን ማስመልከት የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች መርሐግብር ፈጠን ባሉ እንቀስቃሴ በመታጀብ የሜዳውን ክፍል በመለጠጥ ከሁለቱ ኮሪደሮች ወደ ውስጥ በሚጣል ኳስ ለማጥቃት ጥረት ያደረጉት መድኖች ገና 2ኛው ደቂቃ ላይ አደገኛ ሙከራ ሰንዝረዋል። ብሩክ ከማዕዘን አሻምቶት ተካልኝ ደጀኔ በግንባር ገጭቶ የግቡን አግዳሚ የውስጥ ብረት ገጭታ የተመለሰችዋ ኳስን ቀዳሚዋ ሙከራ ሆናለች።
መድኖች በሌላ ሙከራቸው ወገኔ ገዛኸኝ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታት እና ግብ ጠባቂው ፍሬው የመለሰበት ተጠቃሿ ሙከራቸው ነች። ለንግድ ባንክ ተጫዋቾች የመጫወቻ ቦታን በማጥበብ በጥልቀት አልያም በመስመር አጨዋወት ከጎል ጋር ለመቆራኘት ፋታ የለሽ እንቅስቃሴ ላይ ያዘወተሩት መድኖች ተሳክቶላቸው ግብ አግኝተዋል። ከግራ የባንክ የሜዳ ክፍል ንጋቱ ታግሎ ብሩክ እና ወገኔ ተቀባብለው ወገኔ ያሻገረለትን ኳስ መሐመድ አበራ የግብ ጠባቂው ፍሬው ጌታሁን የጊዜ አጠባበቅ ስህተት አግዞት በግንባር ገጭቶ ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል።
ምንም እንኳን ግብ ይቆጠርባቸው እንጂ በተሻጋሪ እና ከተከላካይ ጀርባ በሚጣሉ እና አዲስ ፣ ኪቲካ እና ሱሌይማንን ዋነኛ መነሻ በማድረግ ሲጫወቱ የሚታዩት ንግድ ባንኮች ከየትኛውም አቅጣጫ በዓየር ላይ ለአጥቂዎቻቸው የሚያደርሷቸው ኳሶች ለመድን ተከላካዮች አመቺ የሆኑ ነበሩ። ማራኪነቱ እየጎመራ ከደቂቃ ደቂቃ ሽግግር እያደረገ በቀጠለው ጨዋታ ተመጣጣኝ የሆነ የሜዳ ውስጥ ቅርፅን በተለይ ወደ አጋማሹ መባቻ አስራ አምስት ያህል ደቂቃዎችን ቢያስመለክተንም ከጎል ጋር ለመገናኘት ከሚደረግ ጥረት አኳያ ከንግድ ባንክ ኢትዮጵያ መድን የተሻለ ሆኖ ታይቷል። 38ኛው ደቂቃ መድኖች ብሩክ ሙሉጌታ ከቀኝ የግቡ ሳጥን ከተከላካዮች ታግሎ ከያሬድ ጋር የተጫወተውን ኳስ ያሬድ ወደ ጎል መትቶ ፍሬው ካወጣበት ክስተት በኋላ ተጨማሪ ነገርን ሳንመለከት ጨዋታው በ1ለ0 የመድን መሪነት ወደ መልበሻ ክፍል አምርቷል።
ለተመልካች ሳቢነቱ ሳይደበዝዝ በሁለተኛው አጋማሽ በተመለሰው ጨዋታ ተመጣጣኝ ፉክክርን ከጅምሩ ያሳየን ቢመስልም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እጅግ አስደናቂ የሜዳ ላይ መነሳሳትን ያየንበት ነበር። ሁለቱም የመዲናይቱ ክለቦች ከተሻጋሪ ከቆሙ ኳሶች ግቦችን ለማስቆጠር ሲታትሩ ብናስተውልም የአማካይ ተጫዋቹን ሀብታሙ ሸዋለምን አስወጥተው ቢኒያም ጌታቸውን ወደ ሜዳ በማስገባት የአጥቂ ቁጥራቸውን ከፍ ያደረጉት ንግድ ባንኮች 55ኛው ደቂቃ ላይ ከቆመ ኳስ ወደ አቻነት ተሸጋግረዋል።
በረከት ግዛው ከግራ የተገኘውን የቅጣት ምት ወደ ውስጥ ሲያሻማ አምበሉ ፈቱዲን ጀማል በግንባር ገጭቶ ቡድኑን 1ለ1 አድርጓል። ኳስን ይዘው ወደ ተጋጣሚ ሜዳ ሊገቡ ሲሉ በፍጥነት በንግድ ባንክ ተጫዋቾች ተነጥቀው በሚሻገር እና በቆመ ኳስ ብልጫን ሲወሰድባቸው የሚታዩት መድኖች 62ኛው ደቂቃ ታምራት ተስፋዬ ከግራ ወደ ወደ ሳጥን ልኮ ቢኒያም አመቻችቶ አዲስ ግደይ ወደ ግብ መትቶ አብበከር ከመለሰበት ሙከራ በኋላ ከተመሳሳይ ቦታ ጎል አስቆጠረዋል።
70ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ግዛው ያሻገራት ኳስ ፈቱዲን ጀማል ለቡድኑም ሆነ ለራሱ ሁለተኛ ጎል አድርጓታል። የጨዋታው ግለት እና ፍትጊያ እየመጨረ በዘቀለው ጨዋታ 73ኛው ደቂቃ ላይ ባሲሩ ዑመር ወደ ቀኝ የሰጠውን ኳስ አዲስ ግደይ በድንቅ አጨራረስ ሦስተኛ ጎል ከመረብ አዋህዷል። የንግድ ባንክን የማጥቃት ኃይል የመጨረሻዎቹን አስር ደቂቃ መቋቋም የከበዳቸው መድኖች 83ኛው ደቂቃ ባሲሩ ዑመር ዳግም ያሾለከለትን ኳስ ቢኒያም ጌታቸው አክሎ ጨዋታው ወደ 4ለ1 ተሸጋግሯል። መድኖች ጎል ከተቆጠረባቸው ከአንድ ደቂቃ ቆይታ መልስ የግራ ተከላካዩ ያሬድ ካሳዬ ከዳኛ ጋር በፈጠረው ሰጣ ገባ በሁለት ቢጫ ከሜዳ ከተወገደ በኋላ ጨዋታው በንግድ ባንክ 4ለ1 አሸናፊነት ፍፃሜን አግኝቷል።