ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ | መሪው አርባምንጭ ከተማ በሰፊ ግብ ልዩነት አሸንፎ መሪነቱን አስቀጥሏል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ የመጀመሪያ ዙር የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ሲጀምሩ አርባምንጭ ከተማ ፣ ጋሞ ጨንቻ እና ደሴ ከተማ አሸንፈዋል።

የምድቡ ቀዳሚ መርሃ ግብር አርባምንጭ ከተማን ከካፋ ቡና አገናኝቶ መሪው አርባምንጭ ከተማ አራት ለአንድ በሆነ በሰፊ ውጤት ተጋጣሚውን አሸንፏል።

ጨዋታው እንደተጀመረ ግብ ለማስቆጠር ኳስን ተቆጣጥረው ወደ ፊት እየገፉ ሲጫወቱ የቆዩት አዞዎቹ የመጀመሪያ ግብ ለማስቆጠር አስር ደቂቃ ፈጅቶባቸዋል። በ11ኛው ደቂቃ የፊት መስመር ተጫዋች የሆነው ፍቃዱ መኮንን የካፋ ቡናው ግብ ጠባቂ በሰራው ስህተት ያገኘውን ኳስ ከመረብ ጋር አገናኝቶ ቀዳሚ አድርጓቸው ነበር።

ካፋ ቡና በአንፃሩ ደካማ እንቅስቃሴ ያሳዩበትን አርባአምስት ለመመልከት ችለናል። ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር አብዝተው ጥረት ያደረጉት አዞዎቹ በ35ኛው ደቂቃ በፍቅር ግዛቸው ከመሃል ሜዳ አከባቢ በራሱ ጥረት ኳስን በመስመር አድርጎ ይዞ በመግባት ሌላኛዋን ግብ አስቆጥሮ መሪነታቸው 2ለ0 እንዲሆን አስችሏል። ሁለተኛ ግብ ተቆጥሮባቸው መረጋጋት የተሰናቸው ካፋዎቹ ሶስተኛዋን ግብ ለማስተናገድ ሦስት ደቂቃ ብቻ ነበር የፈጀባቸው። በ38ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት የተሻማውን ግብ አበበ ጥላሁን በግንባሩ ገጭቶ አስቆጥሮ 3ለ0 በሆነ ውጤት ወደመልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ካፋ ቡናዎች በሁለተኛው አጋማሽ ጥሩ የጨዋታ እንቅስቃሴ ለማድረግ ጥረት አድርገዋል። ሆኖም ጠንከራውን የአርባምንጭ ከተማ ተከላካይ መሰመር ደፍሮ ግብ ማስቆጠር ተስኗቸዋል። በ76ኛው ደቂቃ ሙሉቀን ተሾመ ለካፋ ቡና ግብ አስቆጥሮ ወደ ጨዋታ እንዲመልሱ ጥረት አድርጓል።

ሆኖም ግን በ81ኛው ደቂቃ የካፋ ቡና ተጫዋቾች እሸቱ መና እና መታሰቢያ ገዛኸኝ ከእለቱ ዳኛ ጋር በገቡት ሰጣ ገባ በቀይ ካርድ ከሜዳ በመውጣታቸው ቀሪውን ጨዋታ በ9 ተጫዋች ለመጫወት ተገደዋል። ይሄንን እድል ያገኙት አርባምንጮች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጥረት በሚያደርጉበት ጊዜ በ83ኛው ደቂቃ የካፋ ቡና ተከላካዮች በአህመድ ሁሴን ላይ በግብ ክልል አከባቢ ጥፋት ፈፅሞ ፍፁም ቅጣት ምት አገንተዋል። ያገኙትንም ፍፁም ቅጣት ምት ጥፋት የተሰራበት ራሱ አህመድ ሁሴን መጥቶ አስቆጥሮ ጨዋታው 4ለ1 በሆነ ውጤት እንዲጠናቀቅ አድርጓል።

ቀን ስምንት ሰዓት ላይ በተከናወነው በሌላኛው መርሃ ግብር ጋሞ ጨንቻ መጀመሪያ አጋማሽ 2ለ0 እየተመራ ወጥቶ በሁለተኛው አጋማሽ ባስቆጠሩት አምስት ግቦች ቢሾፍቱ ከተማን 5ለ2 ረተዋል።

አዝናኝ በነበረው በ8 ሰዓቱ ጨዋታ ቢሾፍቱ ከተማ የመጀመሪያ አጋማሽ በተጋጣሚው ላይ የጨዋታ ብልጫ በመውሰድ እየመራ ወደመልበሻ ክፍል መግባት ችለው ነበር። በቁጥር በረከት ካለ ከግብ ሙከራ በኋላ የጥረታቸውን ውጤት የሆነው ግብ በ12ኛው ደቂቃ ዳዊት ሽፈራው ከአብዱላዚዝ ዑመር ጋር በአንድ ላንድ ቅብብል ያገኘውን ኳስ ከመረብ ጋር አገናኝቶ ቢሾፊቱ ከተማዎችን መሪ አድርጓቸዋል።

ሙሉ የጨዋታ በላይነት የወሰዱት ቢሾፍቱዎች ብዙ ለግብ የተቃረቡ ኳሶችን አግንተው ሳይጠቀሙ ቀርተዋል።ገሞ ጨንቻ በአንፃሩ ደካማ የኳስ ቁጥጥር ያሳየበትን አጋማሽ ሲያሳልፉ እምብዛም የግብ ሙከራ ሲያድርጉ አልተስተዋሉም። የመጀመሪያ አጋማሽ ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ቀርቶ እያለ በ44ኛው ደቂቃ የቢሾፍቱ ከተማ የፊት መስመር ተጫዋች የመጀመሪያ ግብ አስቆጣሪው ዳዊት ሽፈራው ከርቀት አክርሮ መቶ ድንቅ ግብ በማስቆጠር 2ለ0 በሆነ ውጤት እየመሩ ወደመልበሻ ክፍል እንዲገቡ አድርጓል።

ጋሞ ጨንቻዎች በሁለተኛው አጋማሽ የተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ ጠንከር ብለው በመግባት የተወሰደባቸውን የጨዋታ ብልጫ ማስመለስ ችለዋል። እንዲሁም ከግሩም እንቅስቃሴ ጋር በመመለስ ሳቢ የሆነ ጨዋታ ለተመልካች አስመልክተዋል ለግብ ሙከራዎችንም አድርገዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ እንደጀመረ በ50ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው ፋሲካ አለኝታ ከተከላካይ ጀርባ የተጣለውን ኳስ አግንቶ ከመረብ ጋር አገናኝቶ ጋሞ ጨንቻዎችን ወደጨዋታው መልሷቸዋል። በዚህ ግብ ያላበቁት ጋሞዎች በ55ኛው፣በ59ኛው፣በ61ኛው እንዲሁም በ66ኛው ደቂቃ 4 ግቦችን አከታትለው ማስቆጠር ችለዋል።

የአቻነት ግቧን በ55ኛው ደቂቃ አያልቅበት በቀለ ከታደለ ታንቶ ጋር ባደረጉት ቅበብሎሽ ግሩም ግብ አስቆጥሯል። አቻ ከሆኑ በኋላ መረጋጋት የተሳናቸው ቢሾፍቱዎች በተደጋጋሚ ስህተት ሲሰሩ የተስተዋሉ ሲሆን በ59ኛው ደቂቃ የተሰራውን ስህተት በመጠቀም ኢዮብ ተስፋዬ ለጋሞ ጨንቻ ሶስተኛውን ግብ በማስቆጠር መሪነቱን እንዲረከቡ  አስችሏል። እንዲሁም በ61ኛው ደቂቃ ታደለ ታንቶ በኦራሱ ጥረት ግሩም ግብ አስቆጥሮ ጋሞ ጨንቻ 4ለ2 እንዲመሩ አስችሏል።

ተጨማሪ ግቦችን ለማስቆጠር 5 ያህል ደቂቃ ብቻ የፈጀባቸው ጋሞ ጨንቻዎች በ66ኛው ደቂቃ በድጋሚ በአምበላቸው በለገሠ ዳዊት አማካኝነት አምስተኛ ግብ አስቆጥረው መሪነታቸውን አስፍተዋል። ደካማውን ሁለተኛ አጋማሽ ያሳለፉት ቢሾፍቱዎች ይሄ ነው ሚባል የኳስ ቁጥጥርም ሆነ የግብ ሙከራ ሳያድርጉ ጨዋታው ሊገባደድ ችሏል። በዚህም ጋሞ ጨንቻ ከመመራት ተነስተው ተጋጣሚውን ቢሾፍቱ ከተማን 5ለ2 ማሸነፍ ችሏል።

የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ ደሴ ከተማን ከአዲስከተማ ክ/ከተማ አገናኝቶ በደሴ ከተማ በላይነት ተጠናቋል።

በተከታታይ ነጥብ እየጣሉ የነበሩት ደሴ ከተማዎች ከድል የራቁትን አዲስ ከተማዎችን የገጠሙት ጨዋታ ጥሩ የጨዋታ እንቅስቃሴ የታየበት ጨዋታ ሲሆን በመጀመሪያ አጋማሽ ደሴ ከተማዎች የጨዋታ ብልጫ ወስደው መጫወት ችለዋል።

በጥሩ እንቅስቃሴ ወደድል የተመለሱት ደሴ ከተማዎች በተደጋጋሚ ግብ ለማስቆጠር ለግብ የተቃረበ ሙከራ ሲያድርጉ ተስተውለዋል። እንዲሁም የጨዋታ ብልጫ ወስደው ተጋጣሚያቸው ላይ ጫና ሲያሳድሩ ለመመልከት ችለናል። ሆኖም ግን አንድ ግብ ለማስቆጠር 36 ደቂቃዎችን መጠበቅ ግዴታ ሆኖባቸዋል።

ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ በ36ኛው ደቂቃ  በእርስ በእርስ ቅብብል የተገኘው ኳስ ወደግብ ተመቶ በረኛው እንደምንም ለማዳን ጥረት ሲያድርግ ከሷን ለማራቅ ጥረት ቢያድርግም አቡሽ ደርቤ ድጋሚ አግኝቷት ከመረብ ጋር አገናኝቶ የመጀመሪያ አጋማሽ እየመሩ ወደ መልበሻ ክፍል እንዲገቡ አድርጓል።

 

በሁለተኛው አጋማሽም ጥሩውን ደሴ ከተማ ለማስቀጠል ጥረት ያደረጉት ደሴዎቹ በ58ኛው ደቂቃ የመጀመሪያ ግብ አስቆጣሪው አቡሽ ደርቤ ከሚካኤል ለማ የተሻገረለትን ኳስ አየር ላይ እንዳለች አክርሮ መጥቶ ግሩም ግብ አስቆጥረው መሪነታቸውን ወደ ሁለት አሳድጓል።

አዲስ ከተማ ክ/ከተማ በአንፃሩ ጥሩ ለመንቀሳቀስ ጥረት ያደረጉ ሲሆን ጥሩ ጥሩ የግብ የተቃረቡ ኳሶችን አግንተው መጠቀም አልቻሉም። በ60ኛው ደቂቃ ግብ ጠባቂያቸው ከግብ ክልል ሆኖ ኳስ በመንካቱ በቀይ ከሜዳ በመውጣቱ ቀሪውን 30 ደቂቃ በጎዶሎ ተጫዋች ለመጫወት ተገደዋል።

ቢሆንም በጥሩ እንቅሰቃሴ ወደ ተቃራኒ ቡድን ግብ ክልል በሚገቡበት ሰዓት የደሴ ከተማ ተከላካዮች በሰሩት ስህተት ፍፁም ቅጣት ምት አግንተው በ65ኛው ደቂቃ ፍቃዱ አሰፋ ወደግብነት ቀይሮ የግብ ልዩነታቸውን በማጥበብ ወደጨዋታ እንዲመልሱ አድርጓል።

አዲስ ከተማዎች ግብ ካስቆጠሩ በኋላ በመነቃቃት በመጫወት ግብ ለማስቆጠር ጥረት ቢያድርጉም የደሴ ከተማን ተከላካይ አልፎ ግብ ማስቆጠር ተስኗቸዋል። ይልቁንም በ70ኛው ደቂቃ ደሴ ከተማው የመስመር ተመላለሽ  ታፈሰ ሰርካ በርቀት መጥቶ ግብ አስቆጥሮ አዲስ ከተማዎች የአቻነት ግብ ፍለጋ የሚያድርጉትን ጥረት እንዲገቱ አድርጓል።

ግብ አስቆጥሮ ደስታውን በመግለፅ ማሊያውን ያወለቀው ታፈሰ ሰርካ ቀድሞ ቢጫ በመመልከቱ የቀይ ካርድ ሰላባ በመሆኑ ቀሪዎቹ 20 ደቂቃዎች በሁለቱም ቡድኖች መካከል እኩል የተጫዋች ቁጥር እንዲኖር ያደረገ ቢሆንም ሁለቱም ቡድኖች ተጨማሪ ግብ ሳያስቆጥሩ ጨዋታው 3ለ1 በሆነ ውጤት በደሴ ከተማ አሸናፊነት ተቋጭቷል።