የካፍ ኤሊት ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ እና አልቢትር ባምላክ ተሰማ ዛሬ የሚደረገው ተጠባቂ ጨዋታ ላይ በጋራ በሙያቸው ግልጋሎት እንዲሰጡ ተመድበዋል።
34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በአይቮሪኮስት አዘጋጅነት እየተከናወነ እንደሚገኝ ይታወቃል። በዚህ አህጉራዊ ውድድር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተሳትፎ ባይኖረውም ሦስት የሀገራችን ባለሙያዎች ስፍራው ተገኝተው ግልጋሎት እየሰጡ ይገኛል። ከሦስቱ ባለሙያዎች መካከል የካፍ ኤሊት ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ እስካሁን አራት ጨዋታዎች ላይ የቴክኒክ ጥናት ለማድረግ ተመድበው የሰሩ ሲሆን አልቢትር ባምላክ ተሰማ በበኩላቸው አንድ ጨዋታ በመሐል ዳኝነት ተጨማሪ አንድ ጨዋታ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ግልጋሎት ሰጥተዋል።
ሶከር ኢትዮጵያ አሁን ባገኘችው መረጃ ደግሞ ሁለቱ የሀገራችን እንቁዎች ዛሬ ምሽት 2 ሰዓት የሚደረገውን የጋምቢያ እና ካሜሩን ጨዋታ በጋራ በሙያቸው ግልጋሎት እንዲሰጡ ተመድበዋል።
ባምላክ ጨዋታውን በመሐል ዳኝነት ከአንጎላ ከመጡት ሁለት ረዳቶቹ እንዲሁም አልጄሪያዊው አራተኛ ዳኛ ጋር በመሆን ሲመሩት ኢንስትራክተር አብርሃም ደግሞ ከኬኒያዊ አጋራቸው ጋር በመሆን የቴክኒክ ጥናት ቡድን ተወካይ ሆነው ተመድበዋል።