ሪፖርት | ነብሮቹ 8ኛ የአቻ ውጤታቸውን አስመዝግበዋል

በሣምንቱ የመጨረሻ መርሐግብር ሀዲያ ሆሳዕና እና ወላይታ ድቻ 1-1 ተለያይተዋል።

በምሽቱ መርሐግብር ሀዲያ ሆሳዕና እና ወላይታ ድቻ ሲገናኙ ነብሮቹ በ11ኛው ሣምንት ከኢትዮጵያ ቡና ጋር 1ለ1 ሲለያዩ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ ብሩክ ማርቆስ እና ዳዋ ሆቴሳ በግርማ በቀለ እና ደስታ ዋሚሾ ተተክተው ገብተዋል። በተመሣሣይ ሣምንት በሀዋሳ ከተማ 2ለ1 በተረቱት የጦና ንቦቹ በኩል በተደረጉ ሦስት ቅያሪዎች ፍጹም ግርማ ፣ አብነት ደምሴ እና ናታን ጋሻው በመሳይ ኒኮል ፣ ኢዮብ ተስፋዬ እና ቢኒያም ፍቅሩ ተተክተው በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ ተካተዋል።


12፡00 ሲል በዋና ዳኛ ኃይማኖት አዳነ መሪነት በተጀመረው ጨዋታ ግሩም አጀማመር ያደረጉት ሀዲያዎች ገና በ3ኛው ደቂቃ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ግብ ጠባቂው ታፔ አልዛየር በረጅሙ የመታውን ኳስ ዳዋ ሆቴሳ በግንባር ገጭቶ ወደኋላ ካሳለፈው በኋላ ኳሱን ያገኘው ሠመረ ሀፍታይ ግብ ጠባቂው ቢኒያም ገነቱ ኳሱን ከመቆጣጠሩ በፊት በፍጥነት ሸውዶ በመውሰድ በግሩም ክህሎት አስቆጥሮታል።

ያልተጠበቀ ግብ ያሰተናገዱት ድቻዎች 6ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያውን ዒላማውን የጠበቀ ሙከራቸውን ሲያደርጉ ዘላለም አባተ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ጸጋዬ ብርሃኑ በግንባር ገጭቶ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ታፔ አልዛየር ሲይዝበት ያንኑ ኳስ በፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ የወሰዱት ሀዲያዎች የግብ ዕድል ፈጥረው ተመስገን ብርሃኑ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሆኖ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ቢኒያም ገነቱ መልሶበታል።

በተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ተጭነው መጫወታቸውን የቀጠሉት ነብሮቹ 16ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው በረከት ወልደዮሐንስ ከቀኝ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ያገኘው መለሰ ሚሻሞ በግንባር ገጭቶ ያደረገውን ሙከራ የግቡ የግራ ቋሚ መልሶበታል።

16ኛው ደቂቃ ላይ አጥቂያቸውን ጸጋዬ ብርሃኑን በጉዳት አጥተው በዮናታን ኤልያስ ለመተካት የተገደዱት እና ባልተረጋጋ እንቅስቃሴ የተጋጣሚያቸውን የማጥቃት እንቅስቃሴ ለመግታት የተቸገሩት ወላይታ ድቻዎች 27ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ግብ ለማስተናገድ ተቃርበው ሠመረ ሀፍታይ በግራ መስመር ከዳዋ ሆቴሳ ጋር ተቀባብሎ የወሰደውን ኳስ ወደ ውስጥ ሲቀንሰው ኳሱን ያገኘው ተመስገን ብርሃኑ በድንቅ ከህሎት አመቻችቶ ያደረገውን ፈታኝ ሙከራ ቢኒያም ገነቱ በአስደናቂ ቅልጥፍና አስወጥቶበታል።

ወላይታ ድቻዎች ቀስ በቀስ መጠነኛ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በመውሰድ እና የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን በማነቃቃት ተጭነው ለመጫወት ቢሞክሩም የጠሩ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲቸገሩ 44ኛው ደቂቃ ላይ ናታን ጋሻው ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ወደ ውስጥ ቀንሶት ሳይጠቀሙበት ከቀሩት ኳስ ዉጪም የተጋጣሚን የግብ ክልል መፈተን አልቻሉም። አጋማሹ ሊጠናቀቅ ሴኮንዶች ሲቀሩም የሀዲያው ዳዋ ሆቴሳ ለሁለተኛ ጊዜ ከቅጣት ምት ግሩም ሙከራ ማድረግ ችሎ ነበር።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በመጠኑ ተቀዛቅዞ ሲቀጥል በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የጦና ንቦቹ በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ በመውሰድ በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ቢታትሩም በጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው የሚጫወቱትን ሀዲያዎችን ሰብረው ለመግባት ተቸግረዋል።

በመጨረሻዎቹ 20 ደቂቃዎች ጨዋታው በተሻለ ግለት ብርቱ ፉክክር ሲደረግበት 70ኛው ደቂቃ ላይ በወላይታ ድቻ በኩል ተቀይሮ የገባው ብሥራት በቀለ ከቅጣት ምት መነሻን ያደረገ ኳስ ወደ ግብ ለመሞከር ጥሮ ሲወጣበት ከሰባት ደቂቃዎች በኋላ የጦና ንቦቹ ተሳክቶላቸው የአቻነት ግብ አስቆጥረዋል። ሳሙኤል ዮሐንስ ዮናታን ኤልያስ ላይ በሠራው ጥፋት የተሰጠውን የቅጣት ምት አብነት ደምሴ በግሩም ሁኔታ መረቡ ላይ አሳርፎታል።

ሀዲያዎች ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ የጨዋታ ሂደታቸውን በመጠኑ ወደ ማጥቃት በመቀየር በድጋሚ ለመነቃቃት ጥረት ቢያደርጉም ድቻዎች በተሻለ የራስ መተማመን ጨዋታውን መቆጣጠር ችለዋል። ሆኖም ተጨማሪ ተጠቃሽ እንቅስቃሴ ሳይደረግ ጨዋታው 1ለ1 ተጠናቋል።


ከጨዋታ በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የወላይታ ድቻው አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ በመጀመሪያው አጋማሽ ተበልጠው እንደነበር ያንንም በሁለተኛው አጋማሽ ማስተካከላቸውን እና የተጋጣሚያቸውን የመከላከል አደረጃጃት ሠብረው ለመግባት መቸገራቸውን ሲገልጹ የጸጋዬ ብርሃኑ በጉዳት መውጣት ያሰቡትን እንዳያሳኩ እንዳደረጋቸው ጠቁመዋል። የሀዲያ ሆሳዕናው አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ በበኩላቸው በመጀመሪያው አጋማሽ የተሻሉ እንደነበሩ ጠቅሰው ያገኟቸውን የግብ ዕድሎች አለመጠቀማቸው ዋጋ እንዳስከፈላቸው ተናግረዋል።