13ኛ የጨዋታ ሳምንት ነገ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ጅማሮውን ሲያደርግ በጨዋታዎቹ ላይ ያተኮሩ መረጃዎች ቀጥለው ቀርበዋል።
ወላይታ ድቻ ከ ሀምበርቾ
የጨዋታ ሳምንቱ የመክፈቻ መርሃግብር በሰንጠረዡ እኩሌታ ላይ የሚገኙትን ወላይታ ድቻዎችን በሊጉ ግርጌ ከሚገኙት ሀምበርቾ የሚያገናኝ ይሆናል።
በ18 ነጥቦች በ8ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ወላይታ ድቻዎች ከተከታታይ የሽንፈት እና የአቻ ውጤቶች በኋላ ወደ ድል ለመመለስ የሚያደርጉት ጨዋታ እንደሚሆን ሲጠበቅ በአንፃሩ ሀምበርቾዎች ደግሞ ከ12 ጨዋታዎች በኋላ ሲዳማ ቡና ላይ የተቀዳጁትን የውድድር ዘመኑ የመጀመሪያ ሙሉ ሦስት ነጥብን ለማስቀጠል ብርቱ ፉክክር እንደሚያደርጉ የሚጠበቅበት ጨዋታ ይሆናል።
ባለፈው የጨዋታ ሳምንት ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር በስተመጨረሻም ነጥብ ተጋርተው በወጡበት ጨዋታ ወላይታ ድቻዎች በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ግብ አስተናግደው አመዛኙን የጨዋታ ክፍለጊዜ ጨዋታውን ሲያሳድዱ ቢቆዩም ወደ ራሱ የግብ ክልል የተሰበሰበውን ተጋጣሚያቸውን ለማስከፈት የነበራቸው የማጥቃት ጨዋታ ጥራት ግን አመርቂ አልነበረም።
በተጨማሪም በመጨረሻ ሁለት የሊግ ጨዋታቸው በሁለቱም በመጀመሪያ አምስት ደቂቃ ግቦችን የማስተናገዳቸው ጉዳይ በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃ ቡድኑ ስላለበት የትኩረት ማነስ ማሳያ ሲሆን ይህን ክፍተት ለመድፈን አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ በቀጣይ ጥረት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ሲዳማ ቡናን በበረከት ወንድሙ ሁለት ግቦች በመርታት የመጀመሪያ ሙሉ ሦስት ነጥባቸውን ያሳኩት ሀምበርቾዎች በጨዋታው የነበራቸው የመከላከል አደረጃጀት ሆነ በማጥቃት ሽግግሮች ወቅት የነበራቸው አፈፃፀም ከወትሮው የላቀ ነበር።
በጨዋታው እንደ ነገው ተጋጣሚያቸው ወላይታ ድቻ ሁሉ ግብ ሊሆኑ የሚችሉ ተጨማሪ አጋጣሚዎችን ቢፈጥሩም በሚያስቆጭ መልኩ ሲያባክኑ የተስተዋሉ ሲሆን ፤ ከምንም በላይ ግን የተመዘገበው ውጤት የቡድኑን ሥነ ልቦና ከፍ እንደሚያደርግ ይጠበቃል።
በወላይታ ድቻዎች በኩል ረዘም ያለ ጊዜ ጉዳት ላይ ከሚገኙት መልካሙ ቦጋለ እና ባዬ ገዛኸኝ በስተቀር ሙሉ ስብስብ ለነገ ዝግጁ መሆኑ ሲታወቅ በሀምበርቾ በኩል ቴዎድሮስ በቀለ እና ምናሴ ቢራቱ በጉዳት ምክንያት እንዲሁም ብሩክ ቃልቦሬ ደግሞ በቅጣት የነገው ጨዋታ ያልፋቸዋል።
የዕለቱን ቀዳሚ መርሃግብር በመሐል ዳኝነት መለሠ ንጉሴ ሲመራው በረዳትነት ደግሞ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛዋ ወጋየሁ ዘውዱ እና አማን ሞላ አራተኛ ዳኛ በመሆን ደግሞ አዳነ ወርቁ ተመድቧል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ
የዕለቱ ሁለተኛ መርሃግብር እጅግ ተጠባቂውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን እና የቅዱስ ጊዮርጊስን ፉክክር ያስተናግዳል።
ለሊጉ አዲስ የሆኑት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች የሚቀመሱ አልሆኑም ፤ ካደረጓቸው አስራ ሁለት የሊግ ጨዋታዎች ዘጠኙን በድል ሲወጡ በሁለቱ ነጥብ ተጋርተው በአንዱ ብቻ ተሸንፈው በሃያ ዘጠኝ ነጥቦች በሰንጠረዡ አናት ተሰይመዋል።
ከነጥብም ባለፈ በመከላከል ሆነ በማጥቃት ቁጥሮች በሊጉ ምርጡ የሆነው የአሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ ቡድን በነገው ጨዋታ እንደ ባለፈው ሳምንት ሁሉ በሰንጠረዡ አናት ተፎካካሪያቸው ከሆነው ቅዱስ ጊዮርጊስ ሙሉ ሦስት ነጥብ መውሰድ የቡድኑን የተፎካካሪነት መጠን ይበልጥ የሚያረጋግጥ ይሆናል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት ምናልባት ከተመለከትናቸው የቅዱስ ጊዮርጊስ የጨዋታ ዕለት እንቅስቃሴ ከደካማዎቹ አንዱን አስመልክተውን በድሬዳዋ ከተማ ካስተናገዱት የሦስት ለባዶ ሽንፈት በኋላ ወደ ነገው ጨዋታ የሚመጡት ፈረሰኞቹ በዚህ ጨዋታ ለአስከፊው ሽንፈት ምላሽ የመስጠት ግዴታ ውስጥ ሆነው የሚያደርጉት ጨዋታ ይሆናል ፤ ከመሪው ንግድ ባንክ ከወዲሁ በስምንት ነጥብ ርቀት በሃያ አንድ ነጥቦች በሦስተኛ ደረጃ ለሚገኙት ጊዮርጊሶች የነገው ጨዋታ ከዚህ መነሻነት ላቅ ያለ ትርጉም ይኖረዋል።
በድሬዳዋው ጨዋታ በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ትክክል የነበረ ነገር ለመጥቀስ እስኪቸግር ድረስ እንደ ቡድን ሆነ በግለሰብ ደረጃ ፍፁም ደካማ የነበሩ ሲሆን ይህን ማረም ነገ የግድ የሚላቸው ይሆናል ፤ በተጨማሪም ዘንድሮ በሊጉ ምርጥ ብቃቱን ዳግም እያሳየ የሚገኘው እና በስምንት ግቦች የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የሆነው አቤል ያለው ወደ ግብፅ ለማምራት ዝግጅት ላይ መሆኑ ለቅዱስ ጊዮርጊሶች ሌላው አሳሳቢ ዜና ነው።
ተጋጣሚዎቹ በሊጉ በነበራቸው የ35 ጨዋታ ግንኙነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከፍተኛ የበላይነት ያለው ሲሆን 23 አሸንፎ ፣ በ9 ጨዋታ አቻ ተለያይተው ንግድ ባንክ 3 ጨዋታ አሸንፏል። ፈረሰኞቹ 64 ጎሎች ሲያስቆጥሩ ሀምራዊዎቹ 19 ጎሎች አስቆጥረዋል። በግንኙነታቸው ንግድ ባንክ ለመጨረሻ ጊዜ ያሸነፈው በ1998 ነበር።
ይህን ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ በዋና ዳኝነት ሲመራው ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ትግል ግዛው እና ረዳት ዳኛ ሙስጠፋ መኪ በረዳት ዳኝነት እንዲሁም ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሠ በአራተኛ ዳኝነት ተሰይሟል።