አድዋን ለብዙኀን ለማስተዋወቅ ያለመ የእግር ኳስ ፌስቲቫል በአትላንታ ይደረጋል።
ኢትዮጵያን በዓለም ደረጃ ስሟን ከፍ ከሚያደርጉ ሁነቶች መካከል የአድዋ ድል መታሰቢያ በዓል ግንባር ቀደሙ እንደሆነ ይታወቃል። በየዓመቱ በድምቀት የሚከበረውን በዓል በይበልጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ ያለመ የእግር ኳስ ውድድር እና ፌስቲቫል ከያዝነው ጥር ወር መጨረሻ አንስቶ ለአንድ ወር ያህል በአሜሪካ አትላንታ ሲልቨር ፓርክ ስታዲየም ሊደረግ ስለመሆኑ የውድድሩ የፋይናንስ እና ሎጀስቲክ ክፍል ኃላፊ ዮሴፍ ተሾመ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጸዋል። ዘጠኝ ቡድኖችን ከተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች በማቀፍ የሚደረገው ይህ የእግር ኳስ ውድድር አድዋን በዋናነት በውጪ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በተጨማሪ ሌሎች ሀገራትም በጥልቀት እንዲረዱት እና እንዲያውቁት ለማድረግ እንዲቻል ውድድሩ ለመጀመሪያ ጊዜ ሊዘጋጅ እንደቻለ አቶ ዮሴፍ ነግረውናል።
“አድዋን ለኢትዮጵያውያን ፣ ለትውልደ ኢትዮጵያዊያን እንዲሁም ለመላው ዓለም” በሚል መሪ ሀሳብ እንደሚደረግ የተገለፀው ይህ ውድድር በፍፃሜው ዕለት ላይ በርካቶች የሚገኙበት ደማቅ የመዝጊያ ፌስቲቫልን ጨምሮ በሕይወት የሌሉ ተጫዋቾች እና ኢትዮጵያዊያን እንደሚወሱበት እንዲሁም አድዋን የሚዘክሩ መርሐግብሮችም ጭምር እንዳሉ የተነገረ ሲሆን በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾችም ስለ ሀገራቸው አውቀው ሀገራቸውን በመወከል እንዲጫወቱ ኮሚቴው በቀጣይ ለመሥራት ከያዟቸው ዕቅዶች መሐል ስለመሆኑም አክለው ለዝግጅት ክፍላችን አሳውቀዋል።