በምሽቱ ጨዋታ የጣና ሞገዶቹን የገጠሙት አዳማዎች 2ለ1 በማሸነፍ ተከታታይ ድል አሳክተዋል።
በምሽቱ መርሐግብር ባህር ዳር ከተማ እና አዳማ ከተማ ሲገናኙ የጣና ሞገዶቹ በ12ኛ ሣምንት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 2ለ1 ሲሸነፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የአራት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ አላዛር ማርቆስ ፣ ያሬድ ባዬህ ፣ ፍቅረሚካኤል ዓለሙ እና ፍጹም ጥላሁን በፔፔ ሰይዶ ፣ ፍሬዘር ካሳ ፣ አለልኝ አዘነ እና ዓባይነህ ፌኖ ተተክተው ገብተዋል። አዳማዎች በአንጻሩ ሀዋሳ ከተማን 3ለ2 ከረቱበት ጨዋታ ባደረጉት የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ ታዬ ጋሻው ፣ አድናን ረሻድ እና ፉዓድ ኢብራሂም በአህመድ ረሺድ ፣ በሐይደር ሸረፋ እና በቻርለስ ሪባኑ ተተክተው በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ ገብተዋል።
ሳቢ ፉክክር በተደረገበት የመጀመሪያ አጋማሽ አዳማዎች በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በቁጥር በዝተው ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመግባት ተጭነው መጫወት ሲችሉ በርካታ የግብ ዕድልም መፍጠር ችለዋል። ከእነዚህ መካከል ቦና ዓሊ ከቅጣት ምት ዮሴፍ ታረቀኝ ደግሞ ከክፍት ጨዋታ ከግራ መስመር ያደረጉትን ሙከራ ግብ ጠባቂው አላዛር ማርቆስ መልሷቸዋል።
አዳማዎች በፈጣን ሽግግሮች የተጋጣሚን ሳጥን በተደጋጋሚ በፈተኑበት የማጥቃት እንቅስቃሴ 22ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸው ግብ አስቆጥረዋል። ቦና ዓሊ ከአድናን ረሻድ በተቀበለው ኳስ ከሳጥን አጠገብ መሬት ለመሬት የመታው ኳስ የግቡን የግራ ቋሚ ገጭቶ ግብ ሆኗል።
ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን በማሻሻል የአቻነት ግብ ፍለጋ መታተር የጀመሩት የጣና ሞገዶቹ 25ኛው ደቂቃ ላይ አስቆጥረዋል። መሳይ አገኘሁ ከቀኝ መስመር የዮሴፍ ታረቀኝ እና ሱራፌል ዐዎልን አለመግባባት ተጠቅሞ ያገኘውን ኳስ ወደ ውስጥ ሲያሻግረው ኳሱን ያገኘው ሀብታሙ ታደሠ በግሩም ሁኔታ በግንባር በመግጨት መረቡ ላይ አሳርፎታል።
ጨዋታው እየተጋጋለ ሲቀጥል ባህርዳሮች 30ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ቸርነት ጉግሣ ከሀብታሙ ታደሠ ጋር ተቀባብሎ በሳጥኑ የግራ ክፍል የወሰደውን ኳስ በደካማ አጨራረስ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
መጠነኛ ፉክክር እያስተናገደ ማራኪ ሆኖ በቀጠለው ጨዋታ በመጠኑ እየተቀዛቀዙ የሄዱ የነበሩት አዳማዎች 43ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ የግብ ዕድል ፈጥረው ቦና ዓሊ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ዮሴፍ ታረቀኝ ወደ ግብ ሊሞክረው ሲል ተከላካዩ ፍጹም ፍትሕዓለው በግሩም ቅልጥፍና አግዶበታል። በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት ደግሞ በባህር ዳር ከተማ በኩል ፍሬው ሰለሞን ከሀብታሙ ታደሰ በተቀበለው ኳስ ከሳጥን አጠገብ መሬት ለመሬት በመምታት ያደረገው ሙከራ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።
ከዕረፍት መልስ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ጨዋታው የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል በመጠኑ ተቀዛቅዞ ሲቀጥል በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫውን መውሰድ በቻሉት አዳማዎች በኩል 52ኛው ደቂቃ ላይ አድናን ረሻድ ከቦና ዓሊ በተቀበለው ኳስ ከሳጥን ውጪ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው አላዛር ማርቆስ በቀላሉ ይዞበታል።
ፉዓድ ኢብራሂም እና ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሜዳ የገባውን ታዬ ጋሻውን በጉዳት ምክንያት ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሜዳ በገባው ሬድዋን ሸሪፍ እና ሙሴ ኪሮስ ለመቀየር የተገደዱት አዳማዎች በተጨማሪም ኤልያስ ለገሠን በአድናን ረሻድ ተክተው በማስገባት እና ወደ ተጋጣሚ ሳጥን መታተራቸውን በመቀጠል 74ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸዋል። ፍጹም ፍትሕዓለው ፍቅሩ ዓለማየሁ ላይ ጥፋት ሠርቷል በሚል በኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ ውሳኔ የተሰጠውን አወዛጋቢ የፍጹም ቅጣት ምት ዮሴፍ ታረቀኝ በግራ በኩል ሲመታው ግብ ጠባቂው አላዛር ሳይደርስበት ቀርቶ መረቡ ላይ አርፏል።
በሁለተኛው አጋማሽ እጅግ ተቀዛቅዘው የቀረቡት ባህር ዳር ከተማዎች ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ለመድረስ እጅግ ሲቸገሩ 85ኛው ደቂቃ ላይ ደቂቃ ላይ ፍጹም ፍትሕዓለው ከሳጥን ውጪ ካደረገው ዒላማውን ያልጠበቀ ሙከራ ውጪም የተሻለ የግብ ዕድል መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል። በአዳማ ከተማ በኩል በአንጻሩ ሳዲቅ ዳሪ በቢኒያም ዐይተን ተቀይሮ በመግባት እንደ ታዬ ጋሻው እና ሬድዋን ሸሪፍ የመጀመሪያ ጨዋታውን አድርጓል። ሆኖም ቦና ዓሊ በጭማሪ ደቂቃዎች ውስጥ ካደረገው ሙከራ ውጪ ተጠቃሽ እንቅስቃሴ ሳይደረግ ጨዋታው በአዳማ ከተማ 2ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የባህር ዳር ከተማው አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው እንደ ቡድን ጥሩ ጊዜ ላይ አለመሆናቸውን እና ጫና ውስጥ ያሉ ተጫዋቾችን ስነ ልቦና መመለስ ግዴታ እንደሆነ በመጠቆም በአጋማሹ የዝውውር መስኮትም ተጫዋች ማስፈረም እንደሚፈልጉ በመናገር አዳማዎች ውጤቱ እንደሚገባቸው ነገር ግን የተሰጠባቸውን የፍጹም ቅጣት ምት እንዳላመኑበት ገልጸዋል። የአዳማው አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ በበኩላቸው ካለባቸው ጫና አንጻር በውጤቱ የተለየ ደስታ ማሳየታቸውን ገልጸው እያደገ የሚሄድ ጥሩ እንቅስቃሴ እንዳደረጉ እና በስኳድ በኩል አሳሳቢ ችግር እንደሌለባቸው በመናገር በአስተዳደር ጉዳይ ጥያቄ እንዳላቸውም ጠቁመዋል።