የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን እና ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል ጋር ያለው ውል መጠናቀቁን ተከትሎ በይፋ መለያየቱን የኢ.እ.ፌ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆነው በ2013 የተሾሙት አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል በአራት ዓመታት ቆይታቸው ቡድኑ በ2022 እና 2024 የዓለም ዋንጫ ማጣርያዎች እስከ መጨረሻው ዙር እንዲደርስ ያስቻሉ ሲሆን በ2022 በዩጋንዳ በተሰናዳው የሴካፋ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ዋንጫ ውድድር አሸናፊ እንዲሆን አስችለዋል። ከ20 ዓመት በታች ቡድኑ በተጨማሪ ከግንቦት 2014 ጀምሮ የዋናው ሴቶች ብሔራዊ ቡድን (ሉሲዎቹ) አሰልጣኝ በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩ ሲሆን በቆይታቸውም የሴካፋ ሴቶች ዋንጫን በ3ኛ ደረጃ እንዲያጠናቅቅ አድርገዋል። በተጨማሪ በኦሊምፒክ ማጣሪያ ከሁለተኛ ዙር ፣ ከአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ደግሞ ከአንደኛ ዙር ተሰናብተዋል።
ሆኖም ያላቸው የውል ጊዜ መጠናቀቁን ተከትሎ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በይፋ ከአሰልጣኙ ጋር መለያየቱን በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ያወጣው መረጃ ያመላክታል። በቅርቡ ለሚካሄደው የአፍሪካ ጨዋታዎች ቡድኑን የሚያዘጋጀው አዲስ አሰልጣኝ በፌዴሬሽኑ ያልተገለፀ ሲሆን በቅርቡ ይፋ እንደሚሆን ይጠበቃል።