በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሚሳተፉ ሦስት ክለቦች ለጉብኝት የወዳጅነት ጨዋታ ወደ ደቡብ አፍሪካ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እንደሚያመሩ ሶከር ኢትዮጵያ በብቸኝነት ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።
የሀገራችን ከፍተኛው የሊግ እርከን ውድድር የመጀመሪያውን ዙር ፍልሚያ ሊያገባድድ ሁለት የጨዋታ ሳምንታት የሚቀሩት ሲሆን ከ10 የዕረፍት ቀናት በኋላም በሀዋሳ አልያም በድሬዳዋ የሁለተኛው ዙር ውድድር የሚደረግ ይሆናል። የ2ኛው ዙር ውድድር ከመጀመሩ በፊትም አራት የሊጉ ክለቦች ከሀገር ውጪ የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ እና የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ-ግብር ለማከናወን እንቅስቃሴ ላይ መሆናቸውን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።
ክለቦቹ ኢትዮጵያ ቡና፣ ሀዲያ ሆሳዕና እና ሀምበሪቾ ናቸው። በዚህም ሀዲያ ሆሳዕና እና ሀምበሪቾ ወደ ደቡብ አፍሪካ ሲያመሩ ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ ወደ ዱባይ የሚያመራ ይሆናል።
በሂደቱም ሦስቱም ክለቦች የግብዧ ደብዳቤው የደረሳቸው ሲሆን ዛሬን ጨምሮ ያለፉትን ቀናት የፓስፖርት ቅድመ ዝግጅቶች እየተጠናቀቁ ነው። ከቪዛ ጋር ተያይዞ አዲስ ነገር ካልተፈጠረ በስተቀር ክለቦቹ ወደታቀደው ስፍራ በማምራት የወዳጅነት ጨዋታ እንዲሁም የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ-ግብር እንደሚያከናውኑ ተነግሯል።
በተያያዘ ቅዱስ ጊዮርጊስም እንደ ኢትዮጵያ ቡና ወደ ዱባይ ለማምረት ውጥኖች ያሉ ቢሆኑም እስካሁን የገፉ እንቅስቃሴዎች እንደሌሉ አውቀናል።