ሲዳማ ቡና ከተከታታይ ሁለት ሽንፈቶች በኋላ በጭማሪ ደቂቃ ግብ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን 2ለ1 በመርታት ወሳኝ ድልን አሳክቷል።
ሁለቱም ቡድኖች በ13ኛው ሳምንት ሽንፈት ካስተናገዱበት ጨዋታቸው ሲዳማ ቡና የሁለት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ ለዛሬው ጨዋታ ቀርበዋል። ሲዳማ ቡና ሙሉቀን አዲሱን በአቤኔዘር አስፋው ፣ ቡልቻ ሹራን በይገዙ ቦጋለ ሲተኩ ንግድ ባንኮች በበኩላቸው ቅጣት ባስተናገዱት ፍሬው ጌታሁን እና ሱለይማን ሀሚድ ምትክ ፓልክ ቾል እና ገናናው ረጋሳን እንዲሁም ብሩክ እንዳለ እና ቢኒያም ጌታቸውን በእንዳለ ዮሐንስ እና አቤል ማሙሽ ለውጠው ቀርበዋል።
የሳምንቱ የመክፈቻ ጨዋታ በሁለቱ ቡድኖች መካከል ሲደረግ የመጀመሪያዎቹ ሀያ የጨዋታ ደቂቃዎች የፉክክር መንፈሱ በእጅጉ ወረድ ያለ መልክን ተላብሶ የታየበት ቢሆንም ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በተሻለ ጨዋታውን ለመቆጣጠር ባደረጉበት ቅፅበት ጎልን አስቆጥረዋል። 12ኛው ደቂቃ ላይ አዲስ ግደይ ከራስ ሜዳ በረጅሙ የደረሰውን ኳስ ከግራው የሜዳው ክፍል ሰበር አድርጎ ያሻገረለትን ኳስ በረከት ግዛው በፍጥነት ሾልኮ የሲዳማ ተከላካዮች መሐል ለነበረው አቤል ማሙሽ ሰጥቶት ወጣቱ አጥቂ በቀላሉ መረብ ላይ ኳሷን አሳርፏታል። ጎል ካስተናገዱ በኋላ ከተከላካይ ጀርባ በሚጣሉ ረጃጅም ኳሶች ይገዙ ቦጋለን የትኩረት ማዕከል በማድረግ ሲዳማ ቡናዎች ለመንቀሳቀስ ቢጥሩም የንግድ ባንክን ጥቅጥቅ ያለ የመከላከል መዋቅርን አልፈው የጠሩ አጋጣሚዎችን በመፍጠሩ ግን ዕድለኞች አልነበሩም።
ቀዝቀዝ ባለ እንቅስቃሴ ውስጥ ሆኖ ጨዋታው ቀጥሎ ንግድ ባንኮች በፍጥነት ከራስ ሜዳ በሚደረጉ ንክኪዎች ሁለቱን ኮሪደሮች በመለጠጥ በጥልቀት የመስመር ተጫዋቾቻቸው ተጠቅመው ተጨማሪ ጎልን ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርጉ ቢስተዋልም 27ኛው ደቂቃ ላይ የተጫዋች ለውጥን ሲዳማ ቡናዎች ካደረጉ በኋላ በይበልጥ ወደ ጨዋታ የገቡበትን መንገድ መመልከት ተችሏል። አቤኔዘር አስፋውን በበዛብህ መለዩ ቡናማዎቹ ከተኩ በኋላ ከርቀት ከተደረጉ ሙከራዎቻቸው መልስ ወደ አቻነት ተሸጋግረዋል። 43ኛው ደቂቃ ላይ የንግድ ባንኩ ተከላካይ ገናናው ረጋሳ ኳስን ከቀኝ የሜዳው ክፍል ለማውጣት በጣረበት ወቅት ኳሷ አቅጣጫዋን ቀይራ ተቀይሮ የገባው በዛብህ መለዩ ጋር ደርሳ ተጫዋቹም በአስደናቂ ብቃት በውጪ እግሩ በመምታት ወደ ጎልነት ለውጧት ጨዋታው 1ለ1 ሆኗል። ሜዳ ላይ ከሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በስተቀር በሙከራዎች ረገድ እምብዛም መድመቅ ያልቻለው አጋማሽ ወደ መልበሻ ክፍል ተጨማሪ ጎሎችን ሳያስመለክተን አምርቷል።
ከዕረፍት ጨዋታው ሲመለስ ንግድ ባንኮች መሐል ሜዳውን ለማሻሻል ያለመ ቅያሪን አድርገዋል። በለውጡም ካሌብ አማንክዋህ ወጥቶ ሀብታሙ ሸዋለምን ቢተኩም ሲዳማ ቡናዎች የጨዋታ ብልጫን በመውሰድ በድግግሞሽ ዕድሎችን ሲፈጥሩ ተስተውሏል። ሲዳማ ቡናዎች ከራስ ሜዳ መነሻቸውን አድርገው አልያም ደግሞ የንግድ ባንክ ተጫዋቾች ኳስ በሚይዙበት ወቅት በማስገደድ የሚነጥቋቸውን ኳሶች ተጠቅመው ቀላል የማይባሉ አጋጣሚዎችን መፍጠር ችለው የነበረ ቢሆን የዕለቱ ሁለተኛ ረዳት ዳኛ ሸረፈዲን አስረኪና አወዛጋቢ በሆነ መንገድ በተደጋጋሚ ከጨዋታ ውጪ በማለት ሲያነሱ ተመልክተናል።
58ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ የባንክ የሜዳ ክፍል ከይገዙ ጋር ተቀባብሎ ያሳለፈውን ኳስ ብርሀኑ በቀለ ባልተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ የመታት ኳስ የግቡን ቋሚ ታካ ኳሷ ወጥታለች። በአጋማሹ በእጅጉ ተዳክመው የቀረቡት ንግድ ባንኮች ሲሞን ፒተር እና ታምራት መኮንን ቀይረው በማስገባት የቡድኑን ሚዛን ለመጠበቅ ጥረት አድርገው የነበረ ቢሆንም ቡድኑ የሲዳማ የግብ ክልል ደርሶ ልዩነት መፍጠር ግን በእጅጉ ተስኖታል። ጨዋታውን ይቆጣጠሩት እንጂ የሚገኙ ጥሩ አጋጣሚዎችን ከጎል ጋር ማገናኘት የከበዳቸው ሲዳማ ቡናዎች 58ኛው ደቂቃ ላይ በቡልቻ ሹራ ያለቀለትን የግብ ዕድል አግኝተው ተጫዋቹ ሊጠቀምባት አልቻለም።
በእንቅስቃሴ ከመዳከማቸው በተጨማሪ ሙከራዎችን ለማድረግም ደካማ ሆነው በአጋማሹ የታዩት ንግድ ባንኮች 85ኛው ደቂቃ ላይ ሲሞን ፒተር ከቀኝ ወደ ውስጥ አሻምቶ አዲስ ግደይ ኳሷን ጨርፏት የግቡ ቋሚ ብረትን ገጭታ ኳሷ የተመለሰችበት በአጋማሹ የቡድኑ ጥራት ያላት ብቸኛ ሙከራ ነበረች። ጨዋታውን አሸንፎ ለመውጣት የመጨረሻዎቹን አስር ደቂቃዎችን ተጭነው የተጫወቱት ሲዳማ ቡናዎች በጭማሪ አምስት ደቂቃዎች ውስጥ አሸናፊ ያደረጋቸውን ግብ ወደ ካዝናቸው ከተዋል። 90+3′ ላይ ተቀይሮ የገባው ጋናዊው አጥቂ ማይክል ኪፖሩል መሐል ሜዳ ላይ የደረሰውን ኳስ ሁለቱን የባንክ ተከላካዮች ፈቱዲን እና እንዳለን አልፎ ወደ ግብ እየገፋ ገብቶ በግራ እግሩ ኳሷን ከመረቡ ጋር ቀላቅሏት በመጨረሻም ጨዋታው በሲዳማ ቡና 2ለ1 ድል አድራጊነት ተጠናቋል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የንግድ ባንኩ አሰልጣኝ በጸሎት ልዑልሰገድ አጀማመራቸው ደህና የነበረ ቢሆንም የመጀመሪያው አጋማሽ ወጣ ገባ የነበረ ሲሆን በዕረፍት ሰዓት ቅያሪ አድርገው ለማስተካከል ቢሞክሩም ከሌላው ጊዜ አኳያ ተጫዋቾቻቸው ላይ መደንዘዝ እንደነበር እና አየሩም ምቹ እንዳልነበር ጠቁመዋል ከሌላው ጊዜም ቡድናቸው የተቀዛቀዘ ስለመሆኑ አልሸሸጉም። የሲዳማ ቡናው አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው መልካም ጨዋታ እንደነበር ጠቁመው ጨዋታው ሲጀመር ጥሩ እንዳነበሩ ተናግረው ለእነርሱ የመሐል ሜዳ ብልጫ ፈቅደው መስመሩን በመቆጣጠር እና በተደረጉ ማስተካከሎች ድሉ መምጣቱን ጠቁመው በመጨረሻም ውጤታማ መሆን መቻላቸውን ገልፀዋል።