ከትናንቱ ሽንፈት ማግስት ባህር ዳር ከተማዎች አንድ ተጫዋቹ ካረፉበት ሆቴል እንዲገለል ትዕዛዝ ማስተላለፋቸው ተሰምቷል።
በአስራ አራተኛ ሳምንት መርሃግብር ባህር ዳር ከተማ በሀድያ ሆሳዕና 1ለ0 በሆነ ውጤት ከተረቱበት ጨዋታ መጠናቀቀ በኋላ የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ደግዓረግ ይግዛው ከሱፐር ስፖርት ጋር በነበራቸው ቆይታ በመስመር አጥቂው ፍፁም ጥላሁን ዙርያ ተከታዮን አስተያየት ሰጥተው ነበር።
” ከሁለቱ ቅያሪዎች አንደኛው ጉዳት ነው። የፍፁም ተቀይሮ መውጣት ግን ጉዳት ነው ለማለት አልችልም ፤ ከመጫወት ፍላጎት ማነስ ነው። ሜዳ ውስጥ ካሉ ተጫዋቾች ጋር ተነጋገረ ትኩረት አድርገህ ፣ ጠንከር አድርገህ ተጫወት በማለት ጓደኞቹ መልዕክት ቢያስተላልፉለትም እርሱ ግን ያንን ለማድረግ ፍቃደኛ አይደለም።እንዲህ ያለ ነገር ቡድንህ ውስጥ ሲኖር በጣም አስቸጋሪ ነው። ሜዳ ውስጥ የሚጫወቱትን ልጆች ሞራል ይገላል፣ እንደ ቡድንም ያጎልሀል። በተለይ እንደኛ የቡድን ስብስቡ ጠባብ በሆነ ቡድን ላይ እንዲህ ያሉ ነገሮች ያልጠበቅናቸው ናቸው ለእርሱ ደግሞ የዕርምት እርምጃ እንወስዳለን ብዬ አስባለው።”
ይህን ተከትሎ ክለቡ ፍፁም ጥላሁንን ትናንት ማምሻውን ከሆቴል ለቆ እንዲወጣ እና ባህር ዳር በመሄድ ለክለቡ ፅህፈት ቤት ሪፖርት እንዲያደርግ ትዕዛዝ ማስተላለፉን ሰምተናል። በዚህ መነሻነት በተፈጠረው ጉዳይ ዙርያ ማብራሪያ የጠየቅነው ፍፁም ጥላሁንን ተከታዮን ሀሳብ ሰጥቷል።
” ከሆቴል እንድወጣ እና ባህር ዳር ሄደህ ሪፖርት አድርግ ብለውኛል። አንዳንዴ ጉዳት ላይ ስትሆን ማንም አይረዳህም። እኔ ጉዳት አጋጥሞኝ ነው ተቀይሬ የወጣሁት ፤ በጭራሽ ከፍላጎት ማነስ የተነሳ አይደለም የወጣሁት” በማለት ይናገራል።
ተጫዋቹ በዚህ ሰዓት ቡድኑ ካረፈበት ሆቴል የወጣ ሲሆን ክለቡ ለጊዜው ተጫዋቹ ከሆቴል በመልቀቅ ወደ ባህር ዳር በመሄድ ሪፖርት እንዲያደርግ ይወስን እንጂ ከዚህ የተለየ አዳዲስ ውሳኔዎች ካሉ ተከታትለን ወደ እናንተ የምናደርስ ይሆናል።