የኢትዮጵያ ዋንጫ መረጃዎች

የኢትዮጵያ ዋንጫ የሩብ ፍፃሜ ጨዋታዎች ነገም ይቀጥላሉ ፤ ፋሲል ከነማና ኢትዮጵያ ቡና ወደ ግማሽ ፍፃሜው ለማለፍ የሚያደርጉት ተጠባቂ ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አሰናድተናል።


ነቀምት ከተማና ደብረብርሀን ከተማን በማሸነፍ ወደ ሩብ ፍፃሜው የተሻገሩት ዐፄዎቹ በፕሪምየር ሊጉ ካስመዘገቡት ሁለት ተከታታይ የሽንፈትና የአቻ ውጤት መልስ ወደ ድል ለመመለስና በውድድሩ ለመሰንበት ኢትዮጵያ ቡናን ይገጥማሉ። በፕሪምየር ሊጉ ጠንካራ የተከላካይ ክፍል ካላቸው ክለቦች የሚጠቀሱት ዐፄዎቹ በኢትዮጵያ ዋንጫም ምንም ግብ አላስተናገዱም። በነገው ዕለትም በሁለት ጨዋታዎች ስድስት ግቦች ካስቆጠሩትና በጥሩ ወቅታዊ አቋም ከሚገኙት ኢትዮጵያ ቡናዎች ብርቱ ፉክክር ይጠብቃቸዋል ተብሎ ይገመታል። ፍቃዱ ዓለሙ ፋሲል ከነማዎች ካስቆጠሯቸው አራት ግቦች ውስጥ ሦስቱን በማስቆጠር ትልቅ ድርሻ የተወጣው ተጫዋች ነው።


ወልድያ ከተማን አራት ለባዶ ፤ ኮልፌ ቀራንዮን ሁለት ለባዶ አሸንፈው ወደ ግማሽ ፍፃሜው የተሻገሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች በፕሪምየር ሊጉ ያስመዘገቡት ውጤታማ ጉዞ ለማስቀጠልና ወደ ኢትዮጵያ ዋንጫ ሩብ ፍፃሜ ለመሻገር አልመው ወደ ሜዳ ይገባሉ። ኮልፌ ቀራንዮን በገጠሙበት ዕለት የመጀመርያ ጨዋታቸውን ያደረጉት አሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ በኢትዮጵያ ዋንጫ አሀዱ ብሎ የጀመረው ያለመሸነፍ ውጤታማ ጉዟቸው ለዘጠኝ ጨዋታዎች ዘልቋል። የአሰልጣኝነት መንበሩን ከተረከቡ ወዲህ ባደረጓቸው ጨዋታዎች በአማካይ 1.6 ግቦች በድምሩ ደግሞ አስራ አምስት ግቦች ያስቆጠረ የአጥቂ ጥምረት ያላቸው አሰልጣኙ በነገው ዕለት ጠንካራ የኋላ ክፍል ካለው ቡድን ጋር በሚደርጉት ጨዋታ ትልቅ ፈተና ይጠብቃቸዋል ተብሎ ይገመታል። በሁለት ጨዋታዎች ሦስት ግቦች ያስቆጠረው መሐመድኑር ናስር ከቡድኑ ተጠባቂ ተጫዋቾች አንዱ ነው።