የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ 8ኛ ሳምንት በመጀመሪያው ቀን በተደረገው አንድ ጨዋታ ቦሌ ክፍል ከተማ ሲዳማ ቡናን በማሸነፍ መሪነቱን አስቀጥሏል።
የሰዓት ለውጥ ተደርጎበት ረፋድ ሦስት ሰዓት ላይ በተደረገው በዚህ ጨዋታ ቦሌ ክ/ከተማ በመጀመሪያው አጋማሽ በፊት መስመር አጥቂያቸው በተቆጠረ ብቸኛ ግብ ሲዳማ ቡናን ሲያሸንፍ ብዙ ለግብ የተቃረቡ ዕድሎችን አግንተው ሳይጠቀሙ የቀሩት ሲዳማ ቡናዎች ለሽንፈት ተዳርገዋል።
ተመጣጣኝ የሚባል የጨዋታ እንቅሰቃሴ በታየው በመጀመሪያው አጋማሽ ቦሌ ክፍለ ከተማ የሚያገኙትን አጋጣሚዎችን በመጠቀም ግብ ለማስቆጠር ሙከራ ሲያደርጉ ተስተውለዋል። ሲዳማ ቡና በአንፃሩ በኳስ ቁጥጥር ከተጋጣሚው ተመጣጣኝ በሚባል ደረጃ እንቅስቃሴ ቢያደርግም ደካማ አጨራረስ በማድረግ ግብ ለማስቆጠር ሲቸገሩ ታይተዋል።
ግብ ሳይቆጠር የመጀመሪያ አጋማሽ ሊጠናቀቅ 5 ደቂቃዎች ሲቀሩ ቦሌዎች ኳስን ይዘው በአንድ ለአንድ ቅብብል ወደተቃራኒ ቡድን ግብ ክልል አከባቢ በመግባት ያገኙንት የመጀመሪያ አጋማሽ የመጨረሻ አጋጣሚ በመጠቀም በ40ኛው ደቂቃ ትዕግሥት ወርቄ ኳስን ከመረቅ ጋር አገናኝታ ወደ መልበሻ ክፍል በቦሌ ክፍለ ከተማ 1ለ0 መሪነት እንዲወጡ ሆኗል።
ከመልበሻ ክፍል መልስ በሁለተኛው አጋማሽ አንድ ላይ ብዙ የተጫዋቾች ቅያሪ ያደረገው ሲዳማ ቡና ግብ ለማስቆጠር ከአንደኛው አጋማሽ የተሻለ እንቅሰቃሴ አድርጓል። ሆኖም ግን እንደመጀመሪያው አጋማሽ ግብ ለማስቆጠር የተቸገሩበትን ሁለተኛ አጋማሽ አሳልፈዋል። ቦሌ ክ/ከተማ በአንፃሩ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር በመልሶ ማጥቃት የግብ ሙከራዎችን አድርጓል።
ለሲዳማ ቡና ለግብ የተቃረበ ሙከራ በ78ኛው ደቂቃ ተቀይራ የገባችው ሰናይት ኡራጎ ግብ ክልል ውስጥ ሆና የመታችው ኳስ ለትንሽ ከፍ ያለባት ኳስ ትታወሳለች። እንዲሁም በ85ኛው ደቂቃ ለቦሌ ትዕግሥት ወርቄ ከሲዳማ ቡና ግብ ጠባቂ ጋር ፊትለፊት ተገናኝታ በደካማ እግሯ ሞክራ የሳተችው አደገኛ ሙከራ ይታወሳል።
በሁለቱም ቡድኖች መካከል በርከት ያለ ሙከራ ቢደረገም ጨዋታው በመጀመሪያው አጋማሽ በተቆጠረ ብቸኛ ግብ በቦሌ ክፍለ ከተማ አሸናፊነት ተጠናቋል።