ሪፖርት | ኃይቆቹ በዓሊ ሱሌይማን ሦስት ግቦች ብርቱካናማዎቹን ረተዋል

ታፈሰ ሰለሞን እና ዓሊ ሱሌይማን በደመቁበት ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ ድሬዳዋ ከተማን 3ለ1 አሸንፏል።

በዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማ እና ሀዋሳ ከተማ ተገናኝተው ኃይቆቹ በ17ኛው ሳምንት ሻሸመኔን 3ለ1 ሲያሸንፉ የተጠቀሙበትን አሰላለፍ ሳይለውጡ ለጨዋታው ሲቀርቡ ብርቱካናማዎቹ በአንጻሩ ኢትዮጵያ ቡናን 2ለ1 ካሸነፉበት ስብስብ ከቅያሪ ወንበር በሁለት ቢጫ በተወገደው አቤል አሰበ ምትክ አሜ መሐመድን ወደ ቋሚ አሰላለፍ አካተዋል።


10 ሰዓት ሲል በዋና ዳኛ ኢያሱ ፈንቴ መሪነት በተጀመረው ጨዋታ እጅግ ማራኪ በነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ ጨዋታውን በጥሩ እንቅስቃሴ መጀመር ችለው የነበሩት ድሬዎች 3ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያውን የግብ ዕድል ፈጥረው ዳግማዊ ዓባይ ከቀኝ መስመር ወደ ውስጥ የቀነሰውን ኳስ ያገኘው ዘርዓይ ገብረሥላሴ ያደረገውን ሙከራ ሲሳይ ጋቾ መልሶበታል። ሆኖም የመጀመሪያ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ግን በሀዋሳዎች ተደርጎ ኢዮብ ዓለማየሁ ከቅጣት ምት ባመቻቸለት ኳስ ተባረክ ሄፋሞ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው አብዩ ካሳዬ መልሶበታል።

በሁለቱም በኩል ዕረፍት የለሽ እንቅስቃሴ እየተደረገበት በቀጠለው ጨዋታ የድሬዳዋው ሱራፌል ጌታቸው 10ኛው ደቂቃ ላይ ዳግማዊ ዓባይ በቀኝ መስመር ከማዕዘን ባሻገረው ኳስ በግንባር ገጭቶ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ሲይዝበት በሴኮንዶች ልዩነት ደግሞ ከረጅም ርቀት አክርሮ የመታው ኳስ በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል። ሆኖም ብርቱካናማዎቹ 12ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ራሱ ሱራፌል ጌታቸው ከያሬድ ታደሰ በተቀበለው ኳስ ያደረገውን ሙከራ በረከት ሳሙኤል በግሩም ሸርታቴ አግዶበታል።

ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው በመመለስ እና በፈጣን ሽግግሮች በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል የደረሱት ሀዋሳዎች 17ኛው ደቂቃ ላይ ያለቀለት የግብ ዕድል ፈጥረው ታፈሰ ሰለሞን በድንቅ ዕይታ የሰነጠቀለትን ኳስ ከማቀበል አማራጭ ጋር ያገኘው ተባረክ ሄፋሞ ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ ሲያባክነው ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ግን ኃይቆቹ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ታፈሰ ሰለሞን በድንቅ ዕይታ በሰነጠቀለት ኳስ በሳጥኑ የግራ ክፍል የደረሰው ዓሊ ሱሌይማን በቀኝ እግሩ ከግብ ጠባቂው ከፍ አድርጎ (ቺፕ) በመምታት አስቆጥሮታል።

ጨዋታውን መምራት ከጀመሩ በኋላ በተሻለ የራስ መተማመን ፈታኝ የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን የቀጠሉት ሀዋሳ ከተማዎች 25ኛው ደቂቃ ላይም በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ተጨማሪ ግብ አስቆጥረዋል። ዓሊ ሱሌይማን በተመሳሳይ ሂደት ከታፈሰ ሰለሞን በተሰነጠቀለት ድንቅ ኳስ ፈጥኖ በመውጣት እና ተቆጣጥሮ በመግፋት ከግብ ጠባቂው ከፍ አድርጎ በተረጋጋ አጨራረስ ኳሱን መረቡ ላይ አሳርፎታል።

የተጋጣሚያቸውን ፈጣን የማጥቃት ሽግግር መቆጣጠር ያልቻሉት ድሬዳዋ ከተማዎች 38ኛው ደቂቃ ላይ ጥሩ እንቅስቃሴ አድርገው አሜ መሐመድ ከቀኝ መስመር በግራ እግሩ ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ቻርለስ ሙሴጌ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ጽዮን መርዕድ ይዞበታል። ይህም የአጋማሹ የተሻለ የመጨረሻ ትዕይንት ሆኖ ወደ ዕረፍት አምርተዋል።

ከዕረፍት መልስ ብርቱካናማዎቹ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ተጭነው ለመጫወት ጥረት ሲያደርጉ 50ኛው ደቂቃ ላይም ከሳጥን ውጪ ሙከራ አድርገው ግብ ጠባቂው ጽዮን መርዕድ አስወጥቶታል። በአንጻሩ ሀዋሳዎች 64ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ዓሊ ሱሌይማን በቀኝ መስመር ሄኖክ ሀሰንን በማለፍ ወደ ሳጥን ገብቶ ከማቀበል አማራጭ ጋር ወርቃማ የግብ ዕድል ቢያገኝም ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

ደቂቃዎች በሄዱ ቁጥር ድሬዳዋ ከተማዎች በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ መውሰድ ቢችሉም የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ጨዋታው እየተቀዛቀዘ ሲሄድ 77ኛው ደቂቃ ላይ በኃይቆቹ በኩል ተቀይሮ የገባው እስራኤል እሸቱ የተሻገረለትን ኳስ በግራ እጁ በመቆጣጠር እና ወደፊት በመግፋት ጥሩ የግብ ዕድል ፈጥሮ ግብ ጠባቂውን አብዩ ካሳዬን ለማለፍ ቢሞክርም ግብ ጠባቂው ሲያቋርጥበት ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ግን ግብ አስቆጥረዋል። እስራኤል እሸቱ ከተባረክ ሄፋሞ የተቀበለውን ኳስ ወደ ውሰጥ ቀንሶ ለዓሊ ሱሌይማን ሲያመቻችለት ዓሊም በደካማ አጨራረስ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ሲመልስበት የተመለሰውን ኳስ ራሱ በድጋሚ አግኝቶት ማስቆጠር ችሏል። ግቡም ለራሱም ሆነ ለቡድኑ ሦስተኛ ግብ ሲሆን የግብ አስቆጣሪዎችን ደረጃም በ10 ግቦች መምራት ጀምሯል።

ጨዋታው ሊጠናቀቅ በተጨመሩ 8 ደቂቃዎች ውስጥ በተጋጋለው ጨዋታ ድሬዎች 90+2ኛው ደቂቃ ላይ ለባዶ ከመሸነፍ ያዳነቻቸውን ግብ አግኝተዋል። እንየው ካሳሁን ኤፍሬም አሻሞ ላይ በሠራው ጥፋት ከሳጥኑ የቀኝ ጠርዝ ላይ የተሰጠውን የቅጣት ምት መሐመድ አብዱለጢፍ በግሩም ሁኔታ ማስቆጠር ችሏል። 90+4ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ የኃይቆቹ የመስመር ተከላካይ እንየው ካሳሁን ሰዓት አባክሃል በሚል በአምስት ደቂቃዎች ልዩነት በተሰጡት ሁለት ቢጫ ካርዶች ከሜዳ ተወግዷል። ጨዋታውም በሀዋሳ ከተማ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የድሬዳዋ ከተማው አሰልጣኝ ሽመልስ አበበ በመጀመሪያው አጋማሽ ባልጠበቁበት ሁኔታ ግብ ማስተናገዳቸው ጨዋታውን እንዳከበደባቸው ገልጸው ታፈሰ ሰለሞን እና ዓሊ ሱሌይማንን መቆጣጠር አለመቻላቸውን በመጠቆም በጥቃቅን ስህተቶች እንደተሸነፉ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል። የሀዋሳ ከተማው አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ በበኩላቸው በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ፈልገው እንደጀመሩ እና ጎል ካስቆጠሩ በኋላ ግን ኳስ ይዘው መጫወትን እንደመረጡ በመናገር ዓሊ ሱሌይማን ከጨዋታ ጨዋታ እየተሻሻለ እንደመጣ እና እንደሚያደንቁትም በመግለጽ ከቆሙ ኳሶች ግብ እያስተናገዱ በመሆኑ እዛ ላይ መሥራት እንደሚፈልጉ ጠቁመዋል።