“የዛሬው ጨዋታ በወጣቶች ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለብን ያሳያል።” አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ
“በዛሬው ጨዋታ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በኩል ከፍ ያለ የማሸነፍ ፍላጎት ነበር።” አሰልጣኝ ሌስሊ ኖትሲ
ዋልያዎቹ ሌሶቶን 2ለ1 ካሸነፉ በኋላ የሁለቱም ቡድኖች አሰልጣኞች ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ተከታዩን መልስ ሰጥተዋል።
አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ – ኢትዮጵያ
ስለ ጨዋታው…
“ጨዋታው ጥሩ ነው። ዛሬ ከባለፈው በተሻለ ሁኔታ ቀርበናል። አንደኛ ለውጥ አድርገናል ፤ ብዙ ተጫዋቾችን ቀይረን ነው የገባነው። ሁለተኛ አቀራረባችን ፍላጎታቸውም ስሜታቸውም ጥሩ ነበር ምንም እንኳን በጎል ብንቀደምም ከዛ በኋላ ተነስቶ ለማሸነፍ ያደረጉት ጥረት እንደ አጠቃላይ ስናየው ጥሩ ነው።”
ስለ ተጋጣሚያቸው አቀራረብ…
“ተጋጣሚያችን አጠቃላይ ጨዋታቸው ረጅም እና ካውንተር አታክ ጨዋታዎች በአብዛኛው የሚጠቀሙበት ነው። ይሄን ለመቋቋም አስቸጋሪ ነበር። ምክንያቱም አንድም ባለፈው አሸንፈውን ስለነበር ዛሬ ማሸነፍ አለብን ብለን ነው ያሰብነው። ከዛ አንጻር በሙሉ አቅማችን ወደፊት ለመጫወት ስናስብ እየተጋለጥን ነበር። ይህን ከመጀመሪያውም እናውቀው ስለነበር ጥንቃቄ እንድናደርግ ተጫዋቾቻችንን መክረናል። በካውንተር የሚመጡ እና የሽሚያ ኳሶች ይጥሉብን ነበር ፤ እነዚህ አደገኛ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ ነበር። ከዛ ውጪ ግን እንደ አጠቃላይ ይህንን አውርዶ ተጫውቶ ማሸነፍ መቻል በራሱ ጥሩ ነው።”
በሁለቱ ጨዋታዎች ከቡድናቸው ስለታዘቡት ነገር…
“ሁለቱም የተለያየ ቡድን ነው። የባለፈው ከዕረፍት በኋላ ጥሩ ነበር ፤ ዛሬ ደግሞ እንደ አጠቃላይ ጥሩ ነው። አሁን ሂደት ላይ ነው ቡድኑን ለመገንባት የምናስበው በወጣቶች ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለብን ያሳያል የዛሬው ጨዋታ። ስለዚህ ጣል ጣል የምናደርጋቸው ተጫዋቾች ይኖራሉ ከዛ ውጪ ግን ወጣቶቹ ፕሮሚሲንግ ናቸው። ዛሬም ያሳዩት በጣም ጥሩ ነው ወደፊት ደግሞ ጊዜ ስናገኝ እየገነባን እንሄዳለን።”
የአቤል ያለው ቅያሪ ለፕረሲንግ ነበር ማለት ይቻላል…?
“እሱን ለመሥራት አይደለም። በተለያዩ ተጫዋቾች ላይ የድካም ስሜት ስለነበር የግድ መቀየር ነበረብን። 90 ደቂቃ ሙሉ ፕሬስ ማድረግ አይቻልም። ሀይ ፕረስ ስትጫወት እንደነ አቤል እና ቢኒያም ዓይነት አጥቂዎች ሀይ ፕረስ ላይ በጣም ፍሬያማ ናቸው ማለት አይቻልም ነገር ግን እንዴት ማድረግ እንዳለባቸው በሂደት እየተንቀሳቀሱ ሌሎቹ እየተኳቸው በጋራ ፕረስ የምናደርግበት መንገድ ነበር የፈጠርነው ነገር ግን ያው በተወሰኑ ተጫዋቾች ላይ ድካም ይታይ ስለነበር በተወሰኑ ተጫዋቾች ላይ ለመቀየር ያደረግነው ጥረት እንጂ ፓርቲኩላርሊ ፕረሲንጉን ተፈጻሚ ለማድረግ አይደለም የገባው።”
በባለፈው ጨዋታ ላይ የነበረው ግብ ጠባቂው ሰዒድ ሀብታሙ ዛሬ በፍሬው ጌታሁን መተካቱ ከሞራል አንጻር ወይስ…
“እዚህ ላይ ምንም የሞራል ጥያቄ አይነሳም። ሁሉንም ማየት ስላለብን እንጂ በቀደም ሰዒድ ስላጠፋ ወይም ስህተት ስለፈጸመ አይደለም የቀየርነው ፤ ሌሎቹንም ማየት ስላለብን ነው ወደፊትም ሌሎቹ የተሻለ የሚሠሩ እንደዚህ እየቀያየርን ስናያቸው ነው ፤ ያው ሰዒድ አልተሳሳተም አልልም ነገር ግን ከስህተቱ እንዲማር ደግሞ ማሳረፍም ያስፈልጋል።”
ከባለፈው ጨዋታ የዛሬው በምን የተለየ ነው…?
“ካለፈው ጨዋታ ዛሬ የተለየው እንደ ቡድን በፍላጎት የመጫወት አቅማቸው በጣም ጥሩ ነው። ሙሉ አቅማቸውን አውጥተው መጫወታቸው ጥሩ ነው። አብዛኞቹ በወጣትነት ዕድሜ ላይ ያሉ እና ለብሔራዊ ቡድኑ ፍሬሽ በመሆናቸው ራሳቸውን ማሳየት ይፈልጋሉ። ከዛ አንጻር ያሳዩት ብቃት ይሄንን ያሳያል።”
ስለ ያሬድ ካሳዬ…
“በአንድ ቀን ብዙ ማለት ያስቸግራል ፤ ነገር ግን ዛሬ በጣም ጥሩ ነው ፐርፎርም ያደረገው።”
አሰልጣኝ ሌስሊ ኖትሲ – ሌሶቶ
“ሁለቱን ጨዋታዎች ለማድረግ ወደዚህ ስንመጣ ተፎካካሪ ለመሆን አቅደን ነው ከዚህ አንፃር በጣም ረክተናል ፤ ከሁለቱ ጨዋታዎች የምንወስዳቸው ብዙ መልካም ነገሮች አሉ። በዛሬው ጨዋታ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በኩል ከፍ ያለ የማሸነፍ ፍላጎት ነበር ፤ ለእኛም ለወደፊት የመራናቸውን ጨዋታዎች ለማስጠበቅ መሥራት ስለሚገቡን ነገሮች ትምህርት የወሰድንበት ነው።”