የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ | መሪው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በሀዋሳ ተረቷል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 13ኛ ሳምንት ዛሬ በተደረጉ ሦስት ጨዋታዎች ተጠናቅቆ መሪው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በሀዋሳ ከተማ ሲሸነፍ ንግድ ባንክ አሸንፏል። አርባምንጭ ከተማ እና ቦሌ ክ/ከተማ ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል።

ረፋድ 3:00 ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ከይርጋጨፌ ቡና ያገናኘው ጨዋታ በንግድ ባንክ የበላይነት ተጠናቋል።


በመጀመሪያው አጋማሽ ንግድ ባንኮች በኳስ ቁጥጥር በልጠው በርከት ያሉ የግብ ሙከራዎችን አድርገዋል። ይርጋጨፌ ቡና በአንፃሩ ወደኋላ አፈግፍገው ግብ እንዳይቆጠርባቸው ሲከላከሉ ተስተውለዋል። በዚህም የጨዋታ ብልጫ የወሰዱት ንግድ ባንኮች ምንም እንኳን ግብ የማግባት ሙከራ ቢያደርጉም አንደኛውን አጋማሽ ጠንካራ ሆኖ የቆየውን የይርጋጨፌ ቡናን ተከላካይ መስመር አልፈው ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው ያለ ግብ ወደመልበሻ ክፍል ለመመለስ ተገደዋል።

ከዕረፍት መልስ ጠንከር ብለው በገቡት ንግድ ባንኮች በኩል ገና አጋማሹ እንደተጀመረ መዲና ዐወል በመስመር በኩል ኳስን እየገፋች በመሄድ የመጀመሪያ ግብ ማስቆጠር ችላለች። ግብ አስቆጥረው ወደ ጨዋታ የተመለሱት ንግድ ባንኮች ተጨማሪ ግቦችን ለማስቆጠር ተጋጣሚዎቻቸው ላይ ጫና ፈጥረው ሲጫወቱ ለመመልከት ተችሏል። ሌላ ግብ ለማስቆጠር አስር ደቂቃ ብቻ የጠበቁት ንግድ ባንኮች ሴናፍ ዋቁማ እና ሰናይት በእርስ በርስ ቅብብል ወደ ይርጋጨፌ ቡና ግብ ክልል ተጠግተው ሰናይት ቦጋለ አክርራ በመምታት በጥሩ አጨራረስ ኳስና መረብ አገናኝታ 2ለ0 እንዲሆኑ አድርጋለች።

ይርጋጨፌ ቡና በሁለተኛው አጋማሽ ደካማ እንቅስቃሴ ያደረጉ ሲሆን በመከላከሉ ዘርፍ ግን ተጨማሪ ግብ ላለማስተናገድ ጥሩ ተከላክለዋል። ንግድ ባንክ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ቢጥሩም ሌላ ግብ ሳያስቆጥሩ ጨዋታው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 2ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ተመጣጣኝ በበረው የ8:00 ጨዋታ አርባምንጭ ከተማ ከቦሌ ከተማ ጋር ተገናኝተው ነጥብ ተጋርተዋል።

ጥሩ ፉክክር በታየበት በዚህ ጨዋታ ሁለቱ ቡድኖች በመልሶ ማጥቃታ ጥቃት ሲያደርሱ ለመመለከት ተችሏል። ቦሌ ክ/ከተማ በርከት ካለ ግብ ሙከራ በኋላ ቀዳሚ መሆን የቻሉበት ግብ አስቆጥረዋል። 8ኛው ደቂቃ ላይ ሜላት አሊሙዝ ከግብ ክልል ውጪ ሆና ቀለል አድርጋ የመታችውን ኳስ ትዕግሥት ወርቄ ምትመታ አስመስላ የአርባምንጯን ግብ ጠባቂ ወደሌላ አቅጣጫ በመላክ ኳሱ ወደ ግብነት ተቀይሯል።

የአቻነት ግብ ለማስቆጠር አስር ደቂቃ የጠበቁት አርባምንጮች ጫና ፈጥረው የግብ ሙከራ ካደረጉ በኋላ በ18ኛው ደቂቃ ፎዚያ መሐመድ በራሷ ጥረት ኳስ ይዛ በመግባት ከመረብ ጋር አገናኝታ አቻ አድርጋለች። ግብ አስቆጠረው ወደ ጨዋታ የተመለሱት አርባምንጮች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር የሁለት ደቂቃ ልዩነት ብቻ ነበር የጠበቁት። በ20ኛው ደቂቃ የቦሌ ክ/ከተማ ተጫዋቾች በተዘናጉበት ወቅት ሰርካለም ባሳ ርቀት ላይ አክርራ የመታችው ኳስ ግብ ሆኖ እረፍት እየመሩ እንዲወጡ አድርጋለች።

በሁለተኛው አጋማሽም ጨዋታው ግለቱ ጨምሮ ሲቀጥል አርባምንጭ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ኳስ መስርተው በመጫወት በጫና ሲጫወቱ ለመመለከት ተችሏል። እንዲሁም ቦሌዎችም በአጫጭር ኳሶች ወደ ተቃራኒ ቡድን ግብ ክልል ሰብረው እየገቡ ጥቃት ሲያደርሱ ተስተወሏል። በ52ኛው ደቂቃ ሜላት ጌታቸው ከግብ ክልል ውጪ ሆና አክርራ መትታ ባስቆጠረችው ግብ አቻ ሆነዋል። አቻ ከሆኑ በኋላ ሁለቱ ቡድኖች ሌላ ግብ ፍለጋ በሚያደርጉት ርብርብ ጨዋታው ድምቀቱ ጨምሯል። ሆኖም ግን ሌላ ተጨማሪ ግብ ሳያስመልክቱ ጨዋታው ተገባዷል።


ተጠባቂ በነበረው ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ መሪው ኢትዮ ኤሌክትሪክን አሸንፏል። በርካታ ተመልካቾች በታደሙበት ጨዋታ በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ ብልጫውን ወስደው መንቀሳቀስ የቻሉት ሀዋሳ ከተማዎች የመሪነት ጎልን ማግባት የቻሉት 14ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። በግምት 35 ሜትር ርቀት ላይ የተገኘን የቅጣት ምት እፀገነት ግርማ በግሩም ሁኔታ ማርታ በቀለ መረብ ላይ አስቀምጣ ዕንስት ሀይቆቹን ቀዳሚ ማድረግ ችላለች። ጫና በሚፈጥሩ ፈጣን ተሻጋሪ ኳሶች ተጨማሪ ጎልን ለማስቆጠር የጣሩት ሀዋሳ ከተማዎች በእፀገነት ግርማ በድጋሚ ለግብ የቀረበን ሙከራ ሰንዝረው የግቡ አግዳሚ ብረት መልሶባታል። ወደ አቻነት ለመምጣት በተወሰነ መልኩ ወደ ጨዋታ የገቡት ኤሌክትሪኮች በየምስራች ያለቀለት አጋጣሚ አግኝተው ግብ ጠባቂዋ ቤቴልሔም ዮሐንስ ካዳነች ከሁለት ደቂቃ በኋላ 35ኛ ደቂቃ ላይ ሀዋሳዎች በአንድ ሁለት ማራኪ ቅብብል ቤዛዊት ተስፋዬ የመጨረሻ ኳስን አቀብላት ሰለማዊት ጎሳዬ በቀድሞው ክለቧ ላይ ግብን አስቆጥራ ጨዋታው ወደ 2ለ0 ሽግግር አድርጓል።

ከዕረፍት ጨዋታው ተመልሶ ሲቀጥል ተመጣጣኝ የሚመስል መልክን በጨዋታው ያስተዋልን ቢመስልም በአጋማሹ የተጫዋች ለውጥ በማድረግ በተሻለ ብልጫን ይዘው ኤሌክትሪኮች ተንቀሳቅሰው የነበረ ቢሆንም የሚያገኟቸውን ነፃ ኳሶች ከመረብ ማገናኘት ከብዷቸው 65ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታው እንደደረሰ ሀዋሳ ሦስተኛ ጎልን አክለዋል። በመልሶ ማጥቃት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል የደረሱት ሀዋሳዎች እፀገነት ግርማ ወደ ግብ ክልል ያሳለፈችውን ኳስ ተከላካዩዋ ዘለቃ አሰፋ ለማውጣት ስትጥር በእሙሽ ዳንኤል ተነጥቃ አጥቂዋ መጀመሪያ የመታችውን ኳስ ማርታ በቀለ ስትተፋው አጥቂዋ በድጋሚ አግኝታ በማስቆጠር ጨዋታው በሀዋሳ 3ለ0 ድል አድራጊነት ተጠናቋል።