ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ | አርባምንጭ ከተማ መሪነቱን አጠናክሯል

በምድብ “ለ” የሁለተኛው ዙር 17ኛ ሳምንት የሦስተኛ ቀን ውሎ ኦሜድላ፣ ቢሾፍቱ ከተማ እና አርባምንጭ ከተማ ድል ቀንቷቸዋል።

ረፋድ 3:00 ላይ በዕለቱ የመጀመሪያ ጨዋታ አዲስ ከተማ ክ/ከተማ በኦሜድላ 1-0 ተረቷል። የመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ የተመለከትን ሲሆን ኦሜድላ በተደጋጋሚ ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል ለመድረስ ቢሞክሩም ግብ ማስቆጠር ሲሳናቸው ተስተውሏል። አዲስ ከተማም በመልሶ ማጥቃት ግብ ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል። አጋማሹም በዚህ አጨዋወት ያለ ምንም ግብ ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።


ሁለተኛው አጋማሽ በኦሜድላ በኩል ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ እና የጨዋታ ብልጫ በመውሰድ ጨዋታውን ለመቆጣጠር ሲሞክሩ ተመልክተናል። በአንፃሩ አዲስ ከተማ ወደ ግባቸው ለማፈግፈግ ግብ እንዳይቆጠርባቸው ጥንቃቄ አብዝተው ተስተውለዋል። በ82ኛው ደቂቃ ኦሜድላ ከመስመር የተሻገረውን ኳስ ዘካሪያስ በየነ በግንባሩ አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ አድርጓል። ጨዋታውም በዚው ውጤት በኦሜድላ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከረፋድ 5:00 ላይ በተደረገው የምድቡ መሪ አርባምንጭ ከተማ ባቱ ከተማን 2-0 በመርታት መሪነቱን አጠናክሯል። የመጀመሪያው አጋማሽ ፈጣን እና ማራኪ እንቅስቃሴ ተመልክተናል። አርባ ምንጭ በኳስ ቁጥጥር ተሽለው የተገኙ ሲሆን በ13ኛው ደቂቃ ከመስመር የተሻገረውን ኳስ ዘካሪያስ ፍቅሩ በግሩም አጨራረስ አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ አድርጓል። ብዙም ሳይቆይ በ16ኛው ደቂቃ አርባምንጭ ከተማ ከረጅም ርቀት የተሻማውን ኳስ አህመድ ሁሴን በግንባሩ አስቆጥሮ የቡድኑን መሪነት አጠናክሯል። ከግቡ መቆጠር በኋላ ባቱ ከተማ ግብ ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርግም ምንም ግብ ሳያስቆጥር አጋማሹ ተጠናቆ እረፍት ወጥተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ባቱ ከተማ በጥሩ መንፈስ እና ተነሳሽነት ወደ ሜዳ በመግባት ግብ ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል። አርባ ምንጭ ከተማም የኋላ መስመሩን በማጠናከር ግብ እንዳይቆጠርበት ጥንቃቄ አድርጓል። ጨዋታውም ምንም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር ከረፍት በፊት በገቡት ግብ አርባምንጭ ከተማ 2-0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

ከዚህ ጨዋታ በመቀጠል 8:00 ላይ በተደረገው መርሀግብር ቢሾፍቱ ከተማ ቦዲቲ ከተማን በጠባብ ውጤት 1-0 አሸንፏል። የመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ የኳስ ፍሰት የነበረውና በሁለቱም ቡድኖች በኩል የመመጣጠን ሁኔታን ተመልክተናል። ነገር ግን ጥቂት የሚባሉ የግብ እድሎችን ተመልክተናል። በቦዲቲ ከተማ በኩል ረጃጅም እና ሚቆራረጥ የኳስ ፍሰት ተመልክተናል። በአጋማሹም ጥሩ የሚባል የግብ ሙከራ ሳይደረግ ወደ እረፍት አምርተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ቢሾፍቱ ከተማ ተሻሽለው በመግባት ቦዲቲ ከተማ ላይ ጫና መፍጠር ችለዋል። በ59ኛው ደቂቃ የቢሾፍቱ ከተማ ተጫዋች የሆነው ዳንኤል በሀይሉ ከርቀት አክርሮ በመምታት አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ አድርጓል። ከግቧ መቆጠር በኋላ ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ የተደረገ ቢሆንም ምንም ግብ ሳይቆጠር ጨዋታው በቢሾፍቱ ከተማ አሸናፊነት ተጠናቋል።