የ19ኛ ሳምንት ነገ ፍፃሜውን የሚያገኝ ሲሆን እኛም የነገዎቹን ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎች በተከታዩ ፅሁፋችን አቅርበናል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ድሬዳዋ ከተማ
የዕለቱ የመጀመርያ ጨዋታ ከመሪው ጋር ለመስተካከል የሚጥሩትን ኢትዮጵያ ንግደ ባንኮችን ወደ አውንታዊ ውጤት በፍጥነት ለመመለስ ከሚያልሙት ድሬዳዋ ከተማዎች ያገናኛል።
በ36 ነጥቦች 3ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች በግብ ተንበሽብሸው ካሳኳቸው ድሎች መልስ 4 ነጥብ ለመጣል ቢገደዱም መሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥብ መጣሉን ተከትሎ ዳግም ወደ መሪነት የሚመለሱበት ዕድል አግኝተዋል።
ለሳምንታት ከዘለቀው ወጥነት ያለው ብቃት በኋላ በውስን መልኩ የውጤት መዋዥቅ የገጠማቸው ንግድ ባንኮች በሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ነጥብ ጥለው ወርቃማውን ዕድሉን ላለማባከን ሙሉ ነጥብ ያስፈልጋቸዋል።
ባንክ ካለፉት ስድስት ጨዋታዎች ድል ማድረግ የቻለው በሁለቱም ብቻ ነው። ቡድኑ በተጠቀሱት ጨዋታዎች አስራ አንድ ነጥቦች ጥሏል። በዋንጫ ፉክክሩ ውስጥ የተሻለ ስፍራን ይዞ እንዲዘልቅም ተጨማሪ ነጥቦችን መጣል አይኖርበትም።ሀምራዊ ለባሾቹ በቅርብ ሳምንታት ከውጤት ባለፈ የፊት መስመራቸውም ተቀዛቅዟል።ቡድኑ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች በተከታታይ ነጥብ ከመጣሉም በዘለለ ኳስና መረብ ማገናኘት ተስኖታል። አሰልጣኝ በፀሎት የቡድኑ ጠንካራ ጎን የሆነው የፊት መስመር እንቅስቃሴ ወደ ቀድሞው ብቃቱ የመመለስ የቤት ስራ ይጠብቃቸዋል።
ከተከታታይ ስድስት ሽንፈት አልባ ሳምንታት በኋላ በሀዋሳ ከተማ ሽንፈት የገጠማቸው ድሬዳዋ ከተማዎች ወደ ድል ጎዳና ቶሎ ለመመለስ መሪነት ለመረከብ ከሚያልመው ንግድ ባንክ ከባድ ትንቅንቅ ይጠብቃቸዋል።
በመጨረሻው ሳምንት ጨዋታ በአንፃራዊነት ወረድ ያለ እንቅስቃሴ ያሳዩት ብርቱካናማዎቹ ምንም እንኳ በጨዋታው ጥቂት በማይባሉ ደቂቃዎች ብልጫ መውሰድ ቢችሉም እንቅስቃሴው በጠሩ የግብ ዕድሎች የታጀበ ፍሬያማ ነበር ለማለት ያስቸግራል። ቡድኑ ተከታታይ ድሎች ባስመዘገበበት ወቅትም መሰል የፊት መስመር የውጤታማነት ክፍተት ነበረው ፤ ለዚህ እንደ ማሳያ የሚሆነው የቡድኑ የቅርብ ሳምንታት የግብ መጠን ማየት በቂ ነው።
በተከታታይ ጨዋታዎች ባሳየው እንቅስቃሴ በድንቅ የውህደት ደረጃ የነበረው የብርቱካናማዎቹ የተከላካይ ጥምረት በሀዋሳው ጨዋታ ከባድ ፈተና አስተናግዶ ከስድስት ሳምንታት በኋላ በጨዋታ ከአንድ ግብ በላይ ቢያስተናግድም አሁንም የቡድኑ ምሰሶ ነው። በነገው ጨዋታም በተከታታይ ጨዋታዎች ግብ ካላስቆጠረው የንግድ ባንክ የፊት መስመር የሚያደርጉት ፍልሚያም የጨዋታውን ውጤት ይወስናል ተብሎ ይገመታል።
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ጉዳት ላይ ያለው ብሩክ እንዳለ ባለማገገሙ አይሰለፍም። በድሬዳዋ ከተማ በኩል ደግሞ ቀላል ጉዳት ያስተናገደው ሙህዲን ሙሳ፤ በግል ጉዳይ ምክንያት ላለፉት ቀናት ልምምድ ያልሰራው አሰጋሀኝ ጴጥሮስ እንዲሁም ረዘም ላለ ጊዜ ጉዳት ላይ ያለው
አብዱልፈታህ ዓሊ በጉዳት ምክንያት አይሰለፉም። ሆኖም ቅጣታቸውን የጨረሱት ኤልያስ አህመድ እና እያሱ ለገሰ እንዲሁም በቤተሰብ ችግር ምክንያት ከቡድኑ ጋር ያልነበረው ዳዊት እስጢፋኖስ ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ናቸው።
ሲዳማ ቡና ከ ሻሸመኔ
ሲዳማ ቡና ከተከታታይ አቻ ውጤቶች ሻሸመኔ ከተማ ደግሞ ከተከታታይ ሽንፈት ለመላቀቅ የሚያደርጉት ጨዋታ ደግሞ የጨዋታ ሳምንቱ ማሳረጊያ መርሃግብር ነው።
ከተከታታይ ሽንፈቶች አገግመው ሁለት የአቻ ውጤቶች ያስመዘገቡት ሲዳማ ቡናዎች ላለፉት ስድስት ሳምንታት ከቆዩበት ስፍራ ለመላቀቅ ተከታታይ ድሎች ማስመዝገብ ይጠበቅባቸዋል።
ሲዳማ ቡናዎች በመጨረሻው ሳምንት ጨዋታ ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው ነጥብ ነበር ያስመዘገቡት፤ ቡድኑ ከዐፄዎቹ ጋር አንድ ነጥብ ተካፍሎ ከመውጣቱም በላይ በጨዋታው ወደ ግብ ማስቆጠሩ ተመልሷል። ከወሳኙ ጨዋታ በፊት በተካሄዱት ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ኳስና መረብ ማገናኘት ተስኖት የነበረው ቡድኑ ግብ ማስቆጠር መጀመሩ እንደ አንድ በጎ ጎን የሚታይ ቢሆንም የዘላቂነቱ ጉዳይ ግን አጠያያቂ ነው።
በአስራ ሁለት ነጥቦች 14ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሻሸመኔ ከተማዎች ወላይታ ድቻን ካሸነፉ በኋላ ባካሄዷቸው ሁለት ጨዋታዎች በተከታታይ ሽንፈት አስተናግደዋል። ሻሸመኔዎች በዝውውር መስኮቱ አራት ተጫዋቾች አስፈርመው ቡድናቸውን ለማጠናከር ጥረት ቢያደርጉም በሚፈለገው ደረጃ ውጤት ማምጣት አልቻሉም። በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱ በብዙ ረገድ መሻሻል የሚገባው ቡድኑ በተለይም አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ ቡድኑን ተረክበው ባደረጓቸው የመጀመርዎቹ ጨዋታዎች ጥሩ የመከላከል መዋቅር መገንባት ቢችሉም ጥንካሬያቸው ይዘው መዝለቅ አልቻሉም። በተለይም በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች አምስት ግቦች ማስተናገዳቸው የክፍሉ መቀዛቀዝ ማሳያ ነው። ሌላው ለውጥ የሚሻ ክፍል የፊት መስመሩ ነው፤ ቡድኑ ምንም እንኳ በወራጅ ቀጠናው ካሉ ቡድኖች የተሻለ የግብ መጠን ቢያስመዘግብም የቅርብ ሳምንታት እንቅስቃሴያቸው ግን አሰልጣኙ ብዙ ስራዎች እንዳሉበት ማሳያ ነው።