የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 20ኛ ሳምንት ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች ሲገባደድ ኦሮሚያ ፖሊስ በኮልፌ ቀራኒዮ ተሸንፎ ከምድብ መሪው ጋር ያለውን ርቀት አስፍቷል። ወልዲያ ደግሞ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በተቆጠረ ግብ ድል አስመዝግበዋል።
ረፋድ ሦሰት ሰዓት ላይ በኦሮሚያ ፖሊስ እና ኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከተማ መካከል በተደረገ ጨዋታ ኮልፌ ቀራኒዮ 1ለ0 በሆነ ውጤት አሸንፏል።
ጨዋታው እንደተጀመረ ወደግብ የሮጡት ኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከተማዎች በሁለተኛው ደቂቃ የማዕዘን ምት አግንተው የተሻማውን ኳስ ዋቸሞ ጳውሎስ በግንባሩ ገጭቶ በማቀበል ፍርደአወቅ ሲሳይ በድጋሚ በግንባሩ ገጭቶ መረብ ላይ አሳርፎ ኮልፌ ቀራኒዮ በመምራት ጨዋታውን ጀምሯል።
ኦሮሚያ ፖሊስ ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ወደፊት ገፍተው የሚወሰዷቸውን ኳሶች ወደግብ መቀየር ተስኗቸዋል። በ14ኛው ደቂቃ የኮልፌ ቀሪኒዮው አቤል ታምራት በኦሮሚያ ፖሊሱ መስዑድ ታምሩ ላይ በሰራው ጥፋት ፍፁም ቅጣት ምት ለኦሮሚያ ፖሊስ ተሰጥቶ ዳንኤል ዳርጌ አምክኖታል። በተደጋጋሚ ኳስ ይዘው ወደተቃራኒ ቡድን የገቡ ቢሆንም አስቆጪ የሚባሉ አጋጣሚዎችን ሳይጠቀሙ የመጀመሪያው አጋማሽ ተገባዶ ወደመልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ጨዋታው ከእረፍት ሲመለስ ኦሮሚያ ፖሊስ ጠንከር ብሎ ገብቶ ጫና በማሳደር እንዲሁም በርከት ያሉ የተጫዋቾች ቅያሪ አድርገው በዚህም ጥሩ እንቅስቃሴ ኳስ በማድረግ የሚያገኙትን አጋጣሚ በሙሉ ወደግብነት ለመቀየር የሚያደርጉትን አጋጣሚ ጥሩ ሆኖ የዋለው የኮልፌ ቀራኒዮውው ግብ ጠባቂ በግሩም ሁኔታ ኳሶችን ሲመልስባቸው ተስተውሏል። በተለይም ዳንኤል ዳርጌ ላይ መዳረሻቸው ያደረጉ ከባባድ ሙከራዎች ቢያደርጉም ከመረብ ጋር ማገናኘት ተስኗቸዋል። ኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከተማ በሁለተኛው አጋማሽ ሙሉ ወደኋላ አፈግፍገው ነጥባቸውን ለማስጠበቅ በመከላከሉ ረገድ የተሳካ ሁለተኛ አጋማሽ አሳልፈዋል። ኦሮሚያ ፖሊስ አስቆጪ ሚባለውን ሙከራ በ84ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው ኤፍሬም ሌጋሞ ከመስዑድ ታምሩ ጋር ባደረጉት ቅብብል ቢያደርግም ኳሷ ለትንሽ ከፍ ያለችበት ሙከራ ይታወሳል። በዚህም ጨዋታው በኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከተማ አንድ ለምንም በሆነ ውጤት አሸናፊነት ሊጠናቀቅ ተገዷል።
የሳምንቱ ማሳረጊያ የሆነው ጨዋታ ይርጋጨፌ ቡናን ከወልዲያ አገናኝቶ ወልዲያ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ባስቆጠሩት ግብ ባለድል ሆኗል።
ቀዝቃዛ የጨዋታ እንቅስቃሴ ባስመለከተው በዚህ ጨዋታ በሁለቱም ቡድኖች መካከል እምብዛም የግብ ሙከራ ያላስመለከተና አሰልቺ አጨዋወት የታየበት ጨዋታ ነበር። ሁለቱም ቡድኖች ወደፊት በመግባት ግብ ለማስቆጠር ጥረት ከማድረግ ይልቅ ወደኋላ እያሉ ረጃጅም ኳሶችን የተጫወቱበት የመጀመሪያ አጋማሽ ሲያሳልፉ የተሳካ የኳስ ቅብብልም ማድረግ ተስኗቸዋል። ወልዲያ ከተማ ከተጋጣሚው የተሻለ ሙከራ ያደረገ ቡድን ሲሆን በ30ኛው ደቂቃ ላይ ሚካኤል ሀሲሳ ከበድሩ ኑሪሁሴን ጋር ባደረጉት ቅብብል ሚካኤል ሀሲሳ የመታት ኳስ የግብ አግዳም መልሶበታል።እንዲህ እያለም የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ ወደ እረፍት አምርተዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታው ትንሽ የተሻለ እንቅስቃሴ ይዞ የተመለሰ ቢሆንም ልክ እንደመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች የግብ ማግባት ሙከራ ሲያደርጉ አልተስተዋሉም። ኳሶን ከመሃል ሜዳ ለማሳለፍ ሁለቱም ቡድኖች ጥረት ቢያደርጉም ኳሶች ስኬታማ ባልሆኑ ቅብብል ሲቀሙና ኳሶችን ወደግብ ክልል ማድረስ ሲሳናቸው ተስተውለዋል። የተሻለ የግብ ማግባት ሙከራ በወልዲያ በኩል የተስተዋለ ሲሆን የተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ አንዳንድ ሙከራዎችን ቢያደርጉም በደካማ አጨራረስ ኳሶችን ሲያመክኑ ጨዋታው ወደመገባደጃው ደርሷል። ሆኖም ግን መደበኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ሊጠናቀቅ ሽርፍራፊ ሰከንዶች ሲቀሩት ወልዲያዎች ግብ አስቆጥረዋል። በ89ኛው ደቂቃ በንከክ የተገኘውን ኳስ በተደጋጋሚ ሙከራ ሲያደርግ የነበረው በድሩ ኑሩሁሴን ግብ ጠባቂ የመለሳትን ኳስ ተዘጋጅቶ ጠብቆ ኳስና መረብ አገናኝቶ ወልዲያን ባለድል አድርጓል።