በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ ብርቱ ፉክክር በተደረገበት ጨዋታ ሲዳማ ቡና ወላይታ ድቻን 2ለ1 ረቷል።
በዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ሲዳማ ቡና እና ወላይታ ድቻ ተገናኝተው ሲዳማዎች በ22ኛው ሳምንት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1ለ0 ከተሸነፉበት አሰላለፍ ባደረጉት የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ አንተነህ ተስፋዬ፣ በዛብህ መለዮ እና ይገዙ ቦጋለ በጊት ጋትኮች ፣ ፍቅረኢየሱስ ተወልደብርሃን እና ቡልቻ ሹራ ተተክተው ገብተዋል። የጦና ንቦቹ በአንጻሩ ቅዱስ ጊዮርጊስን 1ለ0 ካሸነፉበት አሰላለፍ በግብ ጠባቂው ቢኒያም ገነቱ፣ በኬኔዲ ከበደ እና በጸጋዬ ብርሃኑ ምትክ አብነት ይስሃቅ፣ ኢዮብ ተስፋዬ እና ባዬ ገዛኸኝን በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ አካትተዋል።
9፡00 ሲል በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ በአምላክ ተሰማ መሪነት በተጀመረው ጨዋታ ጥሩ አጀማመር ያደረጉት ሲዳማ ቡናዎች 8ኛው እና 11ኛው ደቂቃ ላይ የተሻሉ የግብ ዕድሎችን ፈጥረው በሁለቱም አጋጣሚ ይስሃቅ ካኖ ያመቻቸለትን ኳስ ያገኘው ማይክል ኪፕሮቪ ያደረጋቸው ሙከራዎች ዒላማቸውን ሳይጠብቁ ቀርተዋል።
በተደጋጋሚ በቁጥር በዝተው ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በመድረስ ተጭነው መጫወታቸውን የቀጠሉት ሲዳማዎች 12ኛው ደቂቃ ላይ ንጹህ የግብ ዕድል አግኝተው በዛብህ መለዮ እና የድቻው ግብ ጠባቂ አብነት ይስሃቅ ተጋጭተው የመለሱትን ኳስ ያገኘው ይስሃቅ ካኖ ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ ሲያባክነው 21ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ብርሃኑ በቀለ ከሳጥን ውጪ በግራ እግሩ የመታው ኳስ የግቡን የቀኝ ቋሚ ገጭቶ ሲመለስ ኳሱን ሳይዘጋጅ ያገኘው በዛብህ መለዮ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
ጨዋታው 22ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ ግብ ተቆጥሮበታል። በሚያገኙት ኳስ ሁሉ ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ ጥረት ያደረጉት ሲዳማዎች ተሳክቶላቸው ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። በጥሩ የቡድን ሂደት የወሰዱትን ኳስ በመጨረሻም በዛብህ ለይስሃቅ ካኖ ሰንጥቆለት ይስሃቅም ከፍ አድርጎ (ቺፕ) በመምታት ኳሱን መረቡ ላይ አሳርፎታል።
ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ በመጠኑ የተነቃቁት ወላይታ ድቻዎች 24ኛው ደቂቃ ላይ በአብነት ደምሴ 28ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ በብሥራት በቀለ አማካኝነት ዒላማቸውን ያልጠበቁ ሙከራዎች ማድረግ ቢችሉም ተጨማሪ ንጹህ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲቸገሩ ተስተውሏል።
በአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች ግብ ማስቆጠር የሚችሉባቸውን አጋጣሚዎች ፈጥረው በቅድሚያም 41ኛው ደቂቃ ላይ የድቻው ቢኒያም ፍቅሩ ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ ጥሩ ሙከራ አድርጎ በግቡ አግዳሚ ሲመለስበት በአራት ደቂቃዎች ልዩነት ደግሞ የሲዳማው ይስሃቅ ካኖ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታው ኳስ በተመሳሳይ በግቡ አግዳሚ ተመልሶበታል።
ወላይታ ድቻዎች ጨዋታው ወደ ዕረፍት ከማምራቱ በፊት ወደ ጨዋታው ለመመለስ ባደረጉት ጥረት 45+4ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ቢኒያም ፍቅሩ በግራ መስመር ከማዕዘን ያሻገረውን ኳስ ያገኘው አብነት ደምሴ ከነካው በኋላ በዛብህ መለዮ ከመስመር አግዶባቸዋል። ያው ኳስ በቀኝ መስመር ከማዕዘን ተሻምቶም አዛርያስ አቤል በግንባር ገጭቶ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው መክብብ ደገፉ ይዞበታል።
ከዕረፍት መልስም ጨዋታው ባለበት ግለት ቀጥሎ ብልጫ መውሰድ የቻሉት ሲዳማዎች 55ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ማይክል ኪፕሮቪ ከብርሃኑ በቀለ በተሰነጠቀለት ኳስ ከግብ ጠባቂ ጋር ቢገናኝም ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ ሲያባክነው 61ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ይስሃቅ ካኖ ከሳጥን ውጪ ያደረገው ሙከራ በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።
አልፎ አልፎ ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ የሚሞክሩት የጦና ንቦቹ 72ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ቢኒያም ፍቅሩ የግብ ጠባቂውን መውጣት ተመልክቶ የመታው ኳስ የግቡን የግራ ቋሚ ገጭቶ ተመልሶበታል።
ጨዋታውን መቆጣጠር የቻሉት ሲዳማ ቡናዎች 74ኛው ደቂቃ ላይ መሪነታቸውን አጠናክረዋል። ይገዙ ቦጋለ ያመቻቸለትን ኳስ ተከላካዮች ከጨዋታ ውጪ ብለው በተዘናጉበት ቅጽበት የተቆጣጠረው ማይክል ኪፕሮቪ በተረጋጋ አጨራረስ ግብ ጠባቂው በማታለል አስቆጥሮታል።
ወላይታ ድቻዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ በድጋሚ ተጭነው በመጫወት 85ኛው ደቂቃ ላይ ለባዶ ከመሸነፍ ያዳናቸውን ግብ አስቆጠረዋል። ከግራ መስመር የተነሳውን ኳስ በመጨረሻም አበባየሁ ሀጂሶ አመቻችቶለት ዘላለም አባተ በግሩም አጨራረስ አክርሮ በመምታት ኳሱን መረቡ ላይ አሳርፎታል። ጨዋታውም በሲዳማ ቡና 2ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የወላይታ ድቻው አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ የግብ ዕድሎችን የመፍጠር ችግር እንደነበረባቸው ጠቁመው የግብ ጠባቂያቸው ቢኒያም ገነቱ አለመኖር ጫና እንደፈጠረባቸው በመግለጽ የማጥቃት እንቅስቃሴያቸው ውጤታማ እንዳልነበር ተናግረዋል። የሲዳማ ቡናው አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው በበኩላቸው በውጤቱ ደስተኛ ይሁኑ እንጂ በእንቅስቃሴ ደረጃ በቡድናቸው ደስተኛ እንዳልነበሩ ጠቁመው ጎል ከተቆጠረባቸው በኋላ ከጨዋታው ውጥረት አንጻር በተጫዋቾች ላይ ስጋት እንደፈጠረ በመናገር ደጋፊዎቻቸውን በውጤት በመካሳቸው ደስተኛ መሆናቸውን በመጠቆም መልካም የትንሣኤ በዓል እንዲሆንላቸው ምኞታቸውን ገልጸዋል።