በሀዋሳ ከተማ ሁለተኛ የጨዋታ ሳምንቱ ላይ በደረሰው ሊጉ ነገ የሚደረጉ የ24ኛ ሳምንት የመክፈቻ መርሃግብሮች ዙርያ ተከታዩን ፅሁፍ አሰናድተናል።
ፋሲል ከነማ ከ ባህር ዳር ከተማ
የጨዋታ ሳምንቱ ጅማሮውን የሚያደርገው በብዙዎች ዘንድ በጉጉት በሚጠበቀው የፋሲል ከነማ እና ባህር ዳር ጨዋታ ይሆናል።
ፋሲል ከነማ በ36 ነጥቦች በሰንጠረዡ 6ኛ ደረጃ ላይ ሲገኙ በአንፃሩ የነገው ተጋጣሚያቸው ባህር ዳር ከተማ ደግሞ ከመሪው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ7 ነጥቦች ርቀው በሰንጠረዡ 40 ነጥቦችን በመሰብሰብ 3ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ከጨዋታ ጨዋታ ከባለልምዶቹ ይልቅ በወጣት ተጫዋቾቻቸው ተዓምር ነጥቦችን መሰብሰብ የተያያዙት ፋሲል ከነማዎች ባለፈው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ ጃቢር ሙሉ የጨዋታው ልዩነት ፈጣሪ ነበር።ከዚህ ቀደም በተለያዩ አጋጣሚዎች በሊጉ 269 ደቂቃዎች መጫወት ችሎ የነበረው ወጣቱ አማካይ ቡድኑ ሀዲያ ሆሳዕናን ሲረታ ቡድኑን ወደ ጨዋታ የመለሰች የአቻነት ግብ ማስቆጠር ችሏል።
በዘንድሮ የውድድር ዘመን በርከት ያሉ ወጣት ተጫዋቾችን ለዋናው ቡድን እያበቁ የሚገኙት ፋሲል ከነማዎች በቋሚዎቹ መካከልም እጅግ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ሚክኤል ሳማኪ እና ይድነቃቸው ኪዳኔ ባሉበት ስብስብ ለሁለተኛ ተከታታይ ጨዋታ ተሰልፎ መጫወት የቻለው ዮሀንስ ደርሶ ሌላኛው የዘንድሮ የውድድር ዘመን ስኬት ይመስላል።
እርግጥ ቡድኑ ከውድድሩ ጅማሮ አስቀድሞ ከተጠበቀበት አንፃር አሁንም በሚፈለገው ደረጃ ባይገኝም በቀጣይ ቀሪ የሊጉ መርሃግብሮች በሊጉ የተሻለ ስፍራን ይዞ ለማጠናቀቅ ጥረት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
ከሰሞኑ በተሻለ የውጤታማነት ጉዞ ላይ የሚገኙት ባህር ዳር ከተማዎች ተደጋጋሚ የተጫዋቾች ጉዳት ግን ቡድኑ ላይ ተፅዕኖ እንዳይፈጥሩ ስጋትን ያጫረ ሆኗል ፤ ያሬድ ባየህ እና ሙጂብ ቃሲምን ከዚህ ቀደም በጉዳት ያጣው ስብስቡ በ23 የጨዋታ ሳምንት ድሬዳዋ ከተማን ድል ሲያደርጉ የዘንድሮ የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች የሆነውን ቸርነት ጉግሳን በሁለተኛው አጋማሽ በጉዳት ምክንያት መጠቀም ሳይችሉ ቀርዋል።
በተከላካይ መስመሩ ያሬድ ባየህ በሌለባቸው ጨዋታዎች እጅግ አስደናቂ ብቃቱን እያሳየ የሚገኘው ወጣቱ ተከላካይ የብዙዎችን ትኩረት ማግኘት የቻለ ሲሆን ፊት መስመሩ ላይ የተፈጠረውን ክፍቶተት ማን በሚገባ ይጠቀማል የሚለው ጉዳይ ይጠበቃል።
በዐፄዎቹ በኩል ረዘም ሌላ ጊዜ ጉዳት ላይ ከሚገኙት አማኑኤል ገብረሚካኤል እና አፍቅሮተ ሰለሞን በተጨማሪ ይሁን እንዳሻው እና ናትናኤል ገብረጊዮርጊስም በጉዳት ምክንያት ጨዋታው የሚያመልጣቸው ሲሆን የጉንፋን ሕመም ላይ የሚገኘው ጌታነህ ከበደ መግባትም አጠራጣሪ ነው። በጣና ሞገዶቹ በኩልም ረዘም ላለ ጊዜ ጉዳት ላይ ከሚገኘው ሙጅብ ቃሲም ውጪ ፍሬው ሰለሞን በጉዳት ምክንያት አይኖርም።
በሁለቱ ክለቦች ደጋፊዎች ዘንድ እጅግ ላቅ ያለ ትኩረት በሚሰጠው በዚህ ጨዋታ ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም በሊጉ ለዘጠኝ ያክል ጊዜያት የተገናኙ ሲሆን በስድሰት ጨዋታዎች ነጥብ በመጋራት ሲፈፅሙ ፋሲል ሁለት ጊዜ እንዲሁም ባህር ዳር ደግሞ አንድ ጊዜ ባለድል መሆን ሲችሉ በጨዋታዎቹ ዐፄዎቹ ስምንት ጎሎችን እንዲሁም የጣናው ሞገድ ደግሞ አራት ጎሎችን አስቆጥረዋል።
ድሬዳዋ ከተማ ከ አዳማ ከተማ
የዕለቱ ሁለተኛ መርሃግብር ድሬዳዋ ከተማን ከአዳማ ከተማ የሚያገናኝ ይሆናል።
የአሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለው ስብስብ አሁንም ግምቶችን ማፋለሱን ቀጥሏል ፤ በብልጫም ማሸነፍ የሚያውቅበት ስብስብ እንደ ሻሸመኔ ከተማው ድል ደግሞ በተበለጠበት ጨዋታ በጥቂት ዕድሎች ነጥቦችን ይዞ መውጣትንም ጠንቅቆ እንደሚያውቅ በተደጋጋሚ እየተመለከትን እንገኛለን።
ፊት መስመር ላይ በዘጠኝ ግቦች የክለቡ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የሆነውን ዮሴፍ ታረቀኝን ለሙከራ ወደ አውሮፓ ማምራቱን ተከትሎ የአዳማ ማጥቃት ሌላ ጀግናን ይፈልጋል ፤ ባለፈው ጨዋታ ተቀይሮ የገባው ኒቢል ኑሪ ለቡድኑ መፍትሄ የሰጠ ሲሆን በቀጣይነትም የዮሴፍን ክፍተት በግለሰቦች ሆነ እንደ ቡድን ያለን የማጥቃት አቅም በማሳደግ መሸፈን የአሰልጣኝ ይታገሱ ቀዳሚ የቤት ስራ ነው።
በ33 ነጥቦች 8ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ድሬዳዋ ከተማዎች ደግሞ ከሽንፈት በፍጥነት ለማገገም የነገው ጨዋታ በከፍተኛ ትኩረት እንደሚያደርጉት ይጠበቃል።
ቡድኑ ከሰሞኑ በካርሎስ ዳምጠው የግል ብቃት ጨዋታዎችን እያሸነፈ ቢጓዝም በጨዋታዎች ላይ በቂ ዕድሎችን መፍጠር ሆነ ግቦችን ማስቆጠር ላይ ውስንነቶች እንዳሉበት ይስተዋላል ፤ በሊጉ ካደረጓቸው የመጨረሻ 10 ጨዋታዎች በሁለቱ ብቻ ሁለት ግቦችን ያስቆጠሩት ድሬዎች በቀሩት ስምንት ጨዋታዎች ከአንድ በላይ ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዋል።
በአዳማ ከተማ በኩል ቅጣት ላይ ከሚገኘው ታዬ ጋሻው ውጭ የተቀረው ስብስብ ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ነው።
ረዘም ያለ የግንኙነት ታሪክ ያላቸው ሁለቱ ቡድኖች በአጠቃላይ በሊጉ 23 ጊዜ ሲገናኙ አዳማ ከተማዎች 12 ጊዜ ባለድል በመሆን የበላይ ሲሆኑ ድሬዳዋ ከተማዎች ደግሞ በ6 ይከተላሉ የተቀሩት 5 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት የተቋጩ ነበሩ። በጨዋታዎቹ አዳማዎች 27 ሲያስቆጥሩ ድሬዎች በአንፃሩ 19 ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል።