በ25ኛ ሳምንት ሁለተኛ የጨዋታ ቀን የሚደረጉ ሁለት መርሀ ግብሮች የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል።
ሀምበሪቾ ከ ባህርዳር ከተማ
የዕለቱ ቀዳሚ መርሃግብር በሰንጠረዡ ሁለት ፅንፍ በሚገኙ ቡድኖች መካከል ይደረጋል።
በስምንት ነጥቦች የሊጉ ግርጌ ላይ የተቀመጡት ሀምበሪቾዎች ለቀጣይ ጨዋታዎቻቸው መነሳሻ የሚሆኑ ሦስት ነጥቦችን ፍለጋ ወሳኝ የሆነው ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።
ከሦስት ተከታታይ ሽንፈቶች ለማገገም የጣና ሞገዶቹን የሚገጥሙት ሀምበሪቾዎች በሊጉ የመቆየት ተስፋቸው ለማለምለም በቀሩት ስድስት መርሃግብሮች ተከታታይ ድሎች ማስመዝገብ ይኖርባቸዋል። ቡድኑ በተከታታይ በዋንጫ ፉክክሩ ያላቸውን ተስፋ አሟጠው ለመጠቀም የሚሞክሩ ቡድኖች መግጠሙ ጨዋታዎቹን ይበልጥ የሚያከብድባቸውም ይሆናል። ፋሲል ከነማ ላይ ሁለት ግቦች ካስቆጠሩ በኋላ ባከናወኗቸው ሦስት ጨዋታዎች ኳስና መረብ ማገናኘት ያልቻለው ቡድኑ የፊት መስመርና የመከላከል አቅሙን ማጎልበት ግድ ይለዋል።
በተለይም ኳስና መረብ ካገናኘ 270 ደቂቃዎች ያስቆጠረው የፊት መስመር ጠንካራውን የባህርዳር ከተማ የኋላ ክፍል ሊፈትን በሚችል አቅም ወደ ጨዋታው መቅረብ የግድ ይለዋል።
ከሁለት ተከታታይ ድሎች በኋላ ከፋሲል ከነማ ጋር ነጥብ ተጋርተው የወጡት የጣና ሞገዶቹ ነገ በዋንጫ ፉክክሩ ላይ ሊያቆያቸው የሚችለውን ድል ፍለጋ ወደ ሜዳ ይገባሉ።
ባህርዳር ከተማዎች አሁንም በመከላከል ጥንካሬያቸው ገፍተውበታል፤ ከመጨረሻዎቹ ስድስት ጨዋታዎች በሁለት አጋጣሚዎች ብቻ ግቡን ያስደፈረው ቡድኑ ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት መገንባት ቢችልም ተደጋጋሚ ጉዳቶች
አማራጮችን ያሳጣው ቢመስልም ባለፉት ጨዋታዎች የታየው የአፈፃፀም ክፍተትም ለተቆጠሩት ግቦች ማነስ የራሱ ድርሻ ተወጥቷል።
የጣና ሞገዶቹ ከአስከፊው ጉዞ ተላቀው ላለፉት አስር ሳምንታት ከሽንፈት መራቃቸው እንደ አንድ ጠንካራ ጎን የሚነሳላቸው ቢሆንም በዋንጫ ፉክክሩ ለመቆየት ከአቻ ውጤቶች መላቀቅ ግድ ይላቸዋል።
ሀምበሪቾዎች በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች የለም፤ ሆኖም ከደሞዝ ጋር በተያያዘ በርከት ያሉ ተጫዋቾች ጨዋታው ላይ እንደማይሳተፉ ሰምተናል። በባህር ዳር ከተማ በኩል ልምምድ የጀመረው ፍሬው ሰለሞን መሰለፍ አጠራጣሪ ሲሆን ቸርነት ጉግሳ ግን ነገም ከጉዳቱ ባለማገገሙ የነገው ጨዋታ የሚያልፈው ይሆናል።
በመጀመርያው ዙር በታሪካቸው ለመጀመርያ ጊዜ የተገናኙት ሁለቱም ቡድኖች ጨዋታቸው ያለ ግብ ማጠናቀቃቸው ይታወሳል።
ድሬዳዋ ከተማ ከ ኢትዮጵያ መድን
የዕለቱ ሁለተኛ መርሃግብር ደግሞ በስድስት ነጥቦች የሚበላለጡ ቡድኖች የሚያገናኘው
የድሬዳዋ ከተማ እና ኢትዮጵያ መድን ጨዋታ ነው።
በ34 ነጥቦች 9ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ድሬዳዋ ከተማዎች በሀዋሳ ቆይታቸው የመጀመርያው ድላቸውን ለማሳካት እና ደረጃቸውን ለማሻሻል ወደ ሜዳ ይገባሉ።
ብርቱካናማዎቹ በተከታታይነት ካስመዘገቧቸው ድሎች በኋላ በወጥነት መዝለቅ ባይችሉም ጠንካራው የመከላከል አደረጃጀታቸው አብሯቸው አለ፤ ሆኖም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዳከመ የመጣውና ባለፉት አራት ጨዋታዎች ሦስት ግቦች ብቻ ያስመዘገበው የፊት መስመራቸው የቡድኑ ዋነኛ ክፍተት ነው። ስብስቡ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪው ቻርለስ ሙሴጌን ጨምሮ ሌሎች የፊት መስመር ተሰላፊዎች ከጉዳት መልስ ማግኘቱን ተከትሎ በቅርብ ሳምንታት በጎ ለውጦች ያመጣል ተብሎ ቢገመትም በሚፈለገው ደረጃ ተሻሽሏል ብሎ ለመናገር ግን አያስደፍርም።
ቡድኑ በርከት ያሉ ግቦች እያስቆጠረ ጨዋታዎቹን በማሸነፍ የሚገኘውን መድንን በሚገጥመበት ዕለት ጠንካራ የመከላከል አቅሙ እጅግ አስፈላጊው ነው፤ የብርቱካናማዎቹ የኋላ ክፍል ባለፉት አራት ጨዋታዎች ስምንት ግቦች ያስቆጠረውን የኢትዮጵያ መድንን የማጥቃት ክፍል የሚቆጣጠርበት መንገድም የጨዋታው ውጤት ከሚወስኑ ፍጥጫዎች አንዱና ዋነኛው ነው።
ባለፉት አራት ጨዋታዎች አስራ ሁለት ነጥቦችን የሰበሰቡት መድኖች የውድድር ዘመኑ ምርጥ አቋማቸው ላይ ይገኛሉ። ከወራጅ ቀጠናው በመላቀቅም ወደ ሰንጠረዡ አጋማሽ እያደረጉት ያሉትን ጉዞ ለማሳመር ነገ ሙሉ ሦስት ነጥብን ማሳካት በእጅጉ አስፈላጊያቸው ይሆናል።
ብርቱካናማዎቹ ቀለል ያለ ጉዳት የገጠማቸውን
ያሬድ ታደሰ እና ሄኖክ ሀሰንን በነገው ጨዋታ የማይጠቀሙ ሲሆን በኢትዮጵያ መድን በኩል ረዘም ላለ ጊዜ በጉዳት ከሜዳ ከራቀው ንጋቱ ገ/ስላሴ በተጨማሪ በአጋማሹ የዝውውር መስኮት ቡድን ከተቀላቀለ በኃላ ጥሩ ብቃት ላይ ይገኝ የነበረው አቡበከር ሳኒ በጉዳት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጭ የመሆኑ ጉዳይ ትልቁ ዜና ነው።
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም 7 ጊዜ ሲገናኙ ብርቱካናማዎቹ 3 እንዲሁም ኢትዮጵያ መድን ደግሞ 2 ጊዜ ሲያሸንፉ የተቀሩት 2 ግንኙነቶች በነጥብ መጋራት የተደመደሙ ነበሩ ፤ በጨዋታዎቹ ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ 7 ግቦችን አስቆጥረዋል።