ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከፋሲል ከነማ የሚያደርጉት የሳምንቱ ታላቅ ጨዋታን ጨምሮ በ26ኛ ሳምንት ሦስተኛ የጨዋታ ዕለት የሚደረጉ መርሃግብሮችን አስመልክተን ያሰናዳናቸው መረጃዎች እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ፋሲል ከነማ
የጨዋታ ሳምንቱ ተጠባቂ መርሃግብር መሪውን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በተጠበቀበው ልክ ለመገኘት ከተቸገረው ፋሲል ከነማ ጋር ያገናኛል።
በሀምሳ ሦስት ነጥቦች ሊጉን በመምራት ላይ የሚገኙት ንግድ ባንኮች የነጥብ ልዩነቱን ከፍ አድርገው ለዋንጫ የሚያደርጉት ጉዞ ለማደላደልና ከወዲሁ የዋንጫውን አንድ እጀታ ለመጨበጥ የነገውን ወሳኝ መርሃግብር ያከናውናሉ።
በቅርብ ተፎካካሪያቸው መቻል ከደረሰባቸው ሽንፈት ወዲህ ባደረጓቸው ሰባት ጨዋታዎች አራት ነጥቦች ብቻ በመጣል አስራ አምስት ነጥቦች የሰበሰበው ቡድኑ በቅርብ ሳምንታት ከአንድ ለዋንጫ የሚፎካከር ቡድን የሚጠበቅ ወጥነትና ብልጫ አሳይቶ ጨዋታዎቹን በማሸነፍ መሪነቱን አጥብቆ ይዟል። ቡድኑ በተጠቀሱት ሰባት መርሃግብሮች ካሳየው አመርቂ እንቅስቃሴ በተጨማሪ ያስቆጠራቸው አስራ ሰባት ግቦች የቡድኑን አሁናዊ ሁኔታ ማሳያዎች ናቸው።
በሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው መቻል ቀደም ብሎ ነጥብ መጣሉ የዚህን ጨዋታ ዋጋ ይበልጥ ከፍ ያደርገዋል፤ ንግድ ባንክ በዚሁ መንፈስ ለመቀጠል አሁንም ሙሉ ነጥብ ሰብስቦ ልዩነቱን ማስፋት ዋና ዓላማው መሆኑ ባያጠያይቅም ከዐፄዎቹ ቀላል ፈተና እንደማይጠብቃቸው እሙን ነው።
ንግድ ባንክ ኳስን በተሻለ መንገድ ለመቆጣጠር የሚሻ ቡድን ቢሆንም ጠንከር ባሉ ጨዋታዎች ላይ ለመልሶ ማጥቃት እንዲሁም ለቀጥተኛ አጨዋወት የቀረበ የጨዋታ መንገድን ሲከተል ይታያል፤ በቅርብ ሳምንታት ያስመዘገቧቸው ግቦች መነሻቸውም ይህ ነበር። በነገው ጨዋታም ተመሳሳይ የጨዋታ መንገድ ይከተላሉ ተብሎ ሲገመት ከተጋጣሚያቸው አቀራረብ በመንተራስ ለፈጣን ጥቃቶች የተመቹ ቅፅበቶችን የማግኘት ዕድል ይኖራቸዋል ተብሎም ይታሰባል።
በአርባ ነጥቦች 7ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ዐፄዎቹ ከነገው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ማግኘት የደረጃ መሻሻል ያስገኝላቸዋል።
በቅርብ ሳምንታት በርከት ያሉ የአቻ ውጤቶች ያስመዘገቡት ፋሲል ከነማዎች በመጨረሻው መርሃግብር ወልቂጤ ከተማን አሸንፈው ወደ ወሳኙ ጨዋታ እንደመቅረባቸው ቡድኑ በተሻለ የማሸነፍ ስነ ልቦና እንዲገኝ ይረዳዋል ተብሎ ይገመታል።
ወጥነት የጎደለው የተጫዋቾች ብቃት፤ ተደጋጋሚ የግል ስህተቶች፤ ጉዳት እንዲሁም የወሳኝ አማካያቸው ሱራፌል ዳኛቸው ሁነኛ ተተኪ አለማግኘት በውድድር ዓመቱ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳደረባቸው ዐፄዎቹ በቅርብ ሳምንታት በአንፃራዊነት የተሻለ የመከላከል አወቃቀር መገንባታቸው ከዚህ ጨዋታ አውንታዊ ነገር እንዲጠብቁ ያስገድዳቸዋል። ካለፉት አምስት ጨዋታዎች በሦስቱ መረቡን ያላስደፈረው ቡድኑ በቅርብ ሳምንታት ግቦች እያዘነበ እዚህ የደረሰውን ቡድን ለመግታት የመከላከል ጥንካሬውን ማስቀጠል ግድ ይለዋል። በተለይም የተጋጣሚው ዋነኛ የማጥቅያ መንገድ ለሆኑት የመስመር አጨዋወትና ለፈጣን ሽግግሮች ልዩ ዝግጅት ማድረግ ይኖርባቸዋል።
ይህ ጨዋታ ያለው ትርጉም ይበልጥ ለንግድ ባንክ ከፍ ያለ መሆኑም ዐፄዎቹ በተሻለ ነፃነት ወደ ጨዋታው እንዲገቡ የሚያደርጋቸው ጉዳይ ሲሆን በተጋጣሚያቸው የማሸነፍ ግዴታ መነሻነት ሊፈጠሩ ከሚችሉ ተደጋጋሚ የጥቃት ጫናዎች ለመቋቋም ግን ከወዲሁ ጫንቃቸውን ማደላደል ሳይኖርባቸው አይቀርም።
ንግድ ባንኮች ከጉዳትም ሆነ ከቅጣት ነፃ የሆነውን ስብስባቸውን ይዘው ወደ ጨዋታው ሲቀርቡ በዐፄዎቹ በኩል በረዥም ጊዜ ጉዳት ላይ ካለው አማኑኤል ገብረሚካኤል በተጨማሪ በቅጣት ምክንያት የሽመክት ጉግሳን ግልጋሎት በነገው ጨዋታ አያገኙም።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ከዚህ ቀደም በአራት አጋጣሚዎች ተገናኝተዋል፤ ንግድ ባንክ 3 ድል በማስመዝገብ የበላይነቱም ሲይዝ ፋሲል ከነማ አንድ ጨዋታ አሸንፏል። ባንክ 9፣ ፋሲል 4 ጎሎችን ማስቆጠርም ችለዋል።
ሲዳማ ቡና ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ
ከድል ጋር ለመታረቅ ወደ ሜዳ የሚገቡት ፈረሰኞቹና ከሽንፈት ቶሎ ለማገገም ከሚያልሙት ሲዳማ ቡናዎች የሚያገናኘው የዕለቱ ሁለተኛ መርሃግብር በሁለቱም ቡድኖች የድል ረሀብ ምክንያት ማራኪ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይገመታል።
በሰላሣ አንድ ነጥቦች 12ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሲዳማ ቡናዎች በአዳማ ከተማ ከደረሰባቸው ሽንፈት ለማገገም ወደ ሜዳ ይገባሉ።
ብልጫ ወስደው ካሸነፉበት የወላይታ ድቻው ጨዋታ ወዲህ ውስን መቀዛቀዞች የተስተዋለባቸው ሲዳማ ቡናዎች በመጨረሻዎቹ ሁለት የሊግ ጨዋታዎች ያሳኩት አንድ ነጥብ ብቻ ነው።በአዳማ ከተማ ሲሸነፉ በጊዜ ሁለት ግቦችን ያስተናገደው ቡድኑ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ያደረጋቸው ጥረቶችና የፈጠራቸው ዕድሎች በአውንታዊነት የሚነሳለት ጉዳይ ነው። ቡድኑ በአንፃራዊነት ሲታይ እንደባለፉት ጊዜያት ጥሩ ባልተንቀሳቀሰባቸው ጨዋታዎች ጭምርም አደጋ የሚፈጥሩ የግብ ዕድሎች የመፍጠር አቅሙ ይዞ መዝለቁ ለፈረሰኞቹ ፈተና ነው። ይህ እንዲሳካ ግን የሚገኙ አጋጣሚዎችን በስልነት መጠቀም ይኖርባቸዋል። ከዚህ በተጨማሪ በመጨረሻው መርሃግብር ቡድኑ በመከላከል ረገድ የነበሩባቸው የመከላከል ድክመቶች መቅረፍ ይጠበቅባቸዋል።
ሰባት ድል አልባ ጨዋታዎች ያሳለፉት ፈረሰኞቹ ከበርካታ ጊዜያት በኋላ የደረጃ መሻሻል የሚያስገኝላቸውን ድል ፍለጋ ወደ ሜዳ ይገባሉ።
በመጨረሻው መርሃግብር ከተከታታይ ሦስት ሽንፈቶች በኋላ ከሀድያ ሆሳዕና ጋር ነጥብ ተጋርቶ የወጣው ቡድኑ አሁንም ከመከላከል ብርታቱ ጋር መዝለቁ ከሚነሳለት ጠንካራ ጎን በስተቀር በብዙ መለኪያዎች ተዳክሟል። በተለይም ጥራት ያላቸው የግብ ዕድሎች የመፍጠር ውስንነት የቡድኑ ዋነኛው ድክመት ነው።
በፈረሰኞቹ በኩል በእርግጥ ቡድኑ ጥሩ የፊት መስመር መዋቅር ካላቸው ቡድኖች ጋር ሲገናኝ በቀላሉ እጅ እንደማይሰጥ ቡድኑ በተዳከመባቸው ወቅቶችም ተመልክተናል፤ በአሁኑ ወቅት ጥሩ የፊት መስመር ጥምረት ከገነቡት ኢትዮጵያ መድንና ሀዋሳ ከተማ በገጠሙበት ጨዋታ የታየውም ይህ ነው። ሆኖም ጨዋታዎች የመቆጣጠር፣ ንፁህ የግብ ዕድሎች መፍጠር የሚያስችል የጨዋታ ዕቅድ ማበጀት እንዲሁም አጠቃላይ የቡድኑ መንፈስ የሚቀይሩ ውሳኔዎች ከአሰልጣኝ ደረጄ ተስፋዬና ረዳቶቻቸው የሚጠበቅ የቤት ስራ ነው።
በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ግን ቅጣት ላይ የሰነበተው ሞሰስ አዶ በነገው ጨዋታም አይሰለፍም።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 27 ጊዜ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 17 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነት ሲኖረው በአንፃሩ ሲዳማ ቡና ሁለት ጊዜ አሸንፏል። ስምንት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተጠናቋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ 38 ሲዳማ ቡና ደግሞ 12 ጎሎችን አስመዝግበዋል።