በሳምንቱ ትልቅ ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአዲስ ግደይ ግብ ፋሲል ከነማን 1ለ0 በማሸነፍ መሪነቱን ወደ አምስት ነጥብ አስፍቷል።
በሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ንግድ ባንኮች በ25ኛው ሳምንት ወላይታ ድቻን 5ለ0 ያሸነፉበትን አሰላለፍ ሳይለውጡ ለጨዋታው ሲቀርቡ ዐፄዎቹ በአንጻሩ ወልቂጤ ከተማን 1ለ0 ካሸነፉበት አሰላለፍ ኢዮብ ማቲያስ ፣ አቤል እንዳለ እና ዓለምብርሃን ይግዛውን አስወጥተው መናፍ ዐዎል ፣ ጃቢር ሙሉ እና አፍቀሮተ ሰለሞንን አስገብተዋል።
09፡00 ሲል በፌዴራል ዳኛ ሄኖክ አበበ መሪነት በተጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች በመረጡት ጥንቃቄ የተሞላበት አጨዋወት ምክንያት እጅግ የተቀዛቀዘ የነበር ሲሆን የተሻለው የግብ ዕድልም 16ኛው ደቂቃ ላይ በንግድ ባንኮች አማካኝነት ሲፈጠር ኤፍሬም ታምራት ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ነጻ ሆኖ ያገኘው ኪቲካ ጅማ በግንባር ገጭቶ ያደረገው ሙከራ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ወጥቶበታል።
መሃል ሜዳ ላይ በተወሰነው ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች የጠሩ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲቸገሩ 40ኛው ደቂቃ ላይ የፋሲሉ ጌታነህ ከበደ ከሳጥን አጠገብ ካደረገው ኃይል የለሽ ሙከራ እና 41ኛው ደቂቃ ላይ የንግድ ባንኩ ፉዓድ ፈረጃ ከሳጥን ውጪ አክርሮ መትቶት በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ከወጣበት ኳስ ውጪ ተጠቃሽ እንቅስቃሴዎች አልነበሩም።
ከዕረፍት መልስ ሁለቱም ቡድኖች ቅያሪዎችን በማድረግ እንቅስቃሴያቸውን ለማሻሻል ቢጥሩም ንግድ ባንኮች አልፎ አልፎ ከሚያደርጓቸው የማጥቃት ሽግግሮች እና በኳስ ቁጥጥሩ ከሚደረጉ ፉክክሮች ውጪ ሳጥን አካባቢ እጅግ ደካማ እንቅስቃሴ እየተደረገበት ረዘም ላሉ ደቂቃዎች ዘልቋል።
በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በመጠኑ ግለቱ እየጨመረ በመጣው ጨዋታ 81ኛው ደቂቃ ላይ ጋቶች ፓኖም ሱሌይማን ሀሚድ ላይ በሠራው ጥፋት በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ ሲወገድ ያን የቅጣት ምት ፉዓድ ፈረጃ ከቀኝ መስመር አሻምቶት ተቀይሮ የገባው አዲስ ግደይ በግሩም ሁኔታ ግንባር በመግጨት መረቡ ላይ አሳርፎታል። በቀሪ ደቂቃዎች ፋሲሎች የአቻነት ግብ ፍለጋ ቢታትሩም ሳይሳካላቸው ቀርቶ ጨዋታው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎም ንግድ ባንክ አራት ጨዋታዎች እየቀሩ ሊጉን በ5 ነጥቦች ልዩነት መምራት ጀምሯል።
ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የንግድ ባንኩ አሰልጣኝ በጸሎት ልዑልሰገድ ድል ቢያሳኩም በእንቅስቃሴ ደረጃ ወርደው የታዩበት ጨዋታ እንደነበር እና ደስተኛ እንዳልነበሩ ጠቁመው ብዙ ማስተካከል ያለባቸው ነገር እንዳለ በመግለጽ የባንኩ ሥራ አስፈጻሚ አቶ አቤ ሳኖ ለቡድኑ የጀርባ አጥንት መሆናቸውን አበክረው በመናገር ዛሬ በሜዳ ላይ በመገኘታቸው ደስተኛ እንዳደረጓቸው ሀሳባቸውን ሰጥተዋል። የፋሲል ከነማው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በበኩላቸው ጋቶች ፓኖም በሁለተኛ ቢጫ የወጣበት አጋጣሚ ልክ እንዳልነበር በመጠቆም ከሜዳው እና ከጨዋታው ግለት አንጻር ጃቢር ሙሉን ቀይረው እንዲያስወጡት ምክንያት እንደሆናቸው በመግለጽ ንግድ ባንክ ወደ ዋንጫ መቃረቡን ተናግረዋል።