መረጃዎች | 106ኛ የጨዋታ ቀን

የጨዋታ ሳምንቱ መገባደጃ መርሐግብሮችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አሰናድተናል።

ኢትዮጵያ ቡና ከ ሀምበርቾ

ተከታታይ ሁለት ድሎች አሳክተው ነጥባቸውን አርባ አንድ ያደረሱት ቡናማዎቹ በውድድር ዓመቱ ለሁለተኛ ጊዜ ከሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ሙሉ ነጥብ አግኝተው ደረጃቸውን ለማሻሻል ወደ ሜዳ ይገባሉ።

ኢትዮጵያ ቡና ከሁለት የአቻ ውጤቶች በኋላ ተከታታይ ድሎችን በማስመዝገብ ጥሩ ማንሰራራት ችሏል። ቡድኑ በጨዋታዎቹ ምንም እንኳ ከውጤት ባሻገር እንቅስቃሴው አመርቂ ባይሆንም ዕድሎች በመጠቀም ረገድ የነበረው አፈፃፀም መልካም የሚባል ነበር። በተለይም በቅርብ ጊዜ ያዳበሩት ውጤታማ የቆሙ ኳሶች አጠቃቀም ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ብቻ ሦስት ግቦች አስገኝቶላቸዋል። ቡድኑ የቆሙ ኳሶችን ጥቅም ላይ እያዋለ ያለበት ጥንካሬው በእንቅስቃሴ ብልጫ ቢወሰድበት እንኳን ሙሉ ሦስት ነጥብ አስክቶ መውጣት እንደሚያስችለው በሁለቱም ጨዋታዎች ተስተውሏል።

ሆኖም ባለፉት ጨዋታዎች ለተጋጣሚ ጥቃቶች ተጋላጭ ለነበረው የመከላከል አደረጃጀታቸው መፍትሔዎች ማበጀት ይኖርባቸዋል። በነገው ጨዋታ ፈታኝ የማጥቃት ፈተና ይገጥማቸዋል ተብሎ ባይገመትም የመስመር ተከላካዮቻቸው በማጥቃቱ እንዲሳተፉ በመፍቀዳቸው ምክንያት ለመስመር ጥቃት እጅግ ተጋላጭ እየሆነ ያለው እና ለበርካታ አደጋዎች መነሻ ለሆነው መስመር የተጋጣሚን የማጥቃት አቀራረብ መሰረት ያደረገ መፍትሔ ማበጀት አለባቸው።


ከቡና ይልቅ ውጤቱ አጥብቆ የሚያፈልገው ሀምበርቾ በስምንት ነጥቦች በወራጅ ቀጠናው የሚገኝ ሲሆን ከተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ ድልን ማጣጣም ከቻለ መጠነኛ እፎይታ አግኝቶ የነጥብ ልዩነት የማጥበብ ዕድል ይኖረዋል።

ካለፉት አስር ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ማሳካት የቻለው ቡድኑ የናፈቀውን ነጥብ አግኝቶ ልዩነቱን ለማጥበብ ዘርፈ ብዙ ማሻሻያዎች ማድረግ ይጠበቅበታል። በተለይም በቅርብ ጨዋታዎች ከኋላም ከፊትም የታየበትን ድክመት አርሞ ወደ ጨዋታው መቅረብ ግድ ይለዋል፤ ባለፉት አራት ጨዋታዎች ኳስና መረብ ያላገናኘው የቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት እንዲሁም በመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎች ሰባት ግቦች ያስተናገደው የመከላከል አደረጃጀት እንደ ከዚህ ቀደሙ በተመሳሳይ ቁመና የሚቀርብ ከሆነ ለተጋጣሚው ጠንካራ ጎን እጅ መስጠቱ አይቀሬ ነው። ይህ እንዳይሆን እና ያላቸውን የመትረፍ ጭላንጭል ለማሳካት ግን በሁለቱም የሜዳ ክፍሎች ያሉባቸውን ክፍተቶች አርመው መግባት ይኖርባቸዋል።

ቀሪ ጨዋታዎችን እንደ ፍፃሜ እየተመለከተ የማይቀርብ ከሆነ እና ሙሉ ነጥብ መሰብሰብ ካልቻለ በቀጣዩ ዓመት በፕሪምየር ሊጉ የመቆየት ተስፋ የሌለው ቡድኑ በነገው ዕለት ዘጠኝ ያክል ተጫዋቾቹ ከክፍያ ጋር በተያያዘ ከማጣቱ አንፃር ስናየው ክፍተቱ በቀላሉ ስለመሸፈኑ ለመናገር አስቸጋሪ ይሆናል።

በኢትዮጵያ ቡና በኩል ሁሉም ተጫዋቾች ለጨዋታው ዝግጁ ሲሆኑ ሀምበርቾዎች ግን ከክፍያ ጋር በተያያዘ የዘጠኝ ተጫዋቾችን ግልጋሎት እንደማያገኙ ሰምተናል።

በመጀመርያው ዙር በታሪካቸው ለመጀመርያ ጊዜ የተገናኙት ሁለቱ ቡድኖች ጨዋታቸውን ባዶ ለባዶ አጠናቀዋል።

ሀዲያ ሆሳዕና ከ ሀዋሳ ከተማ

በሁለት ነጥብ የሚለያዩ ክለቦችን የሚያገናኘውን ጨዋታ ለሁለቱም ክለቦች በተመሳሳይ የደረጃ መሻሻልን የሚያስገኝ እንደመሆኑ ብርቱ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ሻሸመኔ ከተማን ካሸነፉ በኋላ በመጨረሻው መርሐግብር ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ነጥብ ተጋተርው የወጡት ነብሮቹ ከነገው ጨዋታ ሙሉ ነጥቦች ማግኘት የአንድ ደረጃ መሻሻል ያስገኝላቸዋል። በሊጉ ዝቅተኛው የግብ መጠን (18) በማስተናገድ ጠንካራ የተከላካይ መስመር የገነባው ቡድኑ በነገው ጨዋታ ድንቅ የፊት መስመር ጥምረት ካለው ስብስብ እንደመገናኘቱ ተመሳሳይ ጥንቃቄ አዘል እንዲሁም በቀጥተኛ አጨዋወት በቶሎ ወደ ግብ የመድረስ መንገድን ይከተላል ተብሎ ሲገመት በፈጣን ተጫዋቾች የተገነባውን የተጋጣሚ የማጥቃት አጨዋወት መግታት ግን ቀላል ላይሆንለት ይችላል።

ሆኖም ወሳኝ ተጫዋቾቻቸው ዳዋ ሆቴሳና ብሩክ ማርቆስ ከቅጣት መልስ ማግኘታቸው የፊት መስመሩን ያጠናክርላቸዋል።


ከሦስት ሽንፈት አልባ ጨዋታዎች በኋላ በመቻል ሽንፈት ያስተናገዱት ሀዋሳ ከተማዎች በመቀመጫ ከተማቸው ያደረጉትን የመጀመርያ ጨዋታ በድል መወጣት ቢችሉም በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ነጥብ ጥለዋል።

መቻልን በገጠሙበት ጨዋታ ላይ የተለመደውን ጥሩ የማጥቃት እንቅስቃሴ አድርገው በሁለት አጋጣሚዎች ጨዋታውን መምራት ችለው የነበሩት  ኃይቆቹ በጨዋታው የነበራቸው ደካማ የመከላከል ውሳኔዎች ሦስት ግቦች እንዲያስተናግዱ አድርጓቸዋል። ከዚህ በተጨማሪም በተለይም ከግቦቹ በኋላ ጨዋታውን ለመቆጣጠር የጣሩበት መንገድ በከፍተኛ ተነሳሽነት ሲጫወቱ ለነበሩት መቻሎች እጅግ የተመቸ ነበር። በነገው ዕለት ግን ከመቻሉ ጨዋታ በፊት በተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች ያሳዩትን የተሻለ የመከላከል አቅም መልሰው ማግኘት ይኖርባቸዋል።

የጎል ቀበኛውን ዓሊ ሱሌይማን መሰረት ያደረገው ድንቅ የአጥቂ ጥምረት ውጤታማነቱን አስቀጥሏል፤ በነገው ዕለትም በሊጉ ጥሩ የመከላከል ቁጥሮች ካስመዘገቡት ቡድኖች በግምባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱት የነብሮቹ የተከላካይ ጥምረት ብርቱ ፉክክር ይጠብቃቸዋል።

ጨዋታው ጠጣር የተከላካይ ክፍል እና ውጤታማ የማጥቃት ጥምረት ያላቸው ሁለት ክለቦች ከማገናኘቱ ባለፈ በሁለቱ ክለቦች መሃከል ያለው የሁለት ነጥቦች ልዩነት ጨዋታውን ማራኪና ፉክክር የተሞላበት ያደርገዋል ተብሎም ይገመታል።

በሀዲያ ሆሳዕና በኩል መለሠ ሚሻሞ አሁንም በጉዳት አይኖርም። ሆኖም በጣምራ ስምንት ግቦች ያስቆጠሩት ዳዋ ሆቴሳ እና ብሩክ ማርቆስ ከቅጣት መመለሳቸው ለቡድኑ መልካም ዜና ነው።
በሀዋሳ ከተማ በኩል እንየው ካሳሁን በቅጣት ምክንያት የማይሰለፍ ተጫዋች ነው።

ክለቦቹ የተሰረዘውን የ2012 ውድድር ዘመን ሳይጨምር በሊጉ ዘጠኝ ጊዜ ተገናኝተዋል፤ ሀዋሳ 2 በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን ሆሳዕና 1 አሸንፏል። በቀሪ 6 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ሀዋሳ ከተማ 14፣ ሀዲያ ሆሳዕና 12 ጎሎችን ማስቆጠር ችለዋል።