👉 “ረጅም ጉዞ ነው ምን አልባት ከልምምድ ውጭ ሊያደርገን ይችላል”
👉 “ብዙ ጊዜ ከኳስ ጋር መቆየትን የተላመዱ ተጫዋቾች ስላሉ ከዚህ ለማውጣት ጊዜ የሚፈልግ ይመስለኛል“
👉 “ከዚህ እንዲወጡ የተለያዩ ሥራዎች እየሠራን ነው ፤ እያስገደድን ማለት ነው”
👉 “ፊፋ አንዴ ያወጣሁትን ፕሮግራም መቀየር አልችልም በማለት ምላሽ እንደተሰጠ ነው”
የዋልያዎቹ አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ከፊታቸው ከሚጠብቃቸው የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ዙሪያ አጭር ጋዜጣዊ መግለጫ በፌዴሬሽኑ መሰብሰቢያ አዳራሽ ተከናውኗል። አሰልጣኙ በመግቢያ ንግግራቸው ላለፉት ሰባት ቀናት ሲያደርጉት ስለቆዩት ዝግጅት ገለፃ አድርገው ሦስተኛ እና አራተኛ የማጣሪያ ጨዋታ ለማድረግ ወደ ጊኒ ቢሳው እና ጂቡቲን ለመግጠም ወደ ሞሮኮ እንደሚሄዱ እና ለዚህ ጨዋታ እንዲረዳቸው ለ26 ተጫዋቾች ጥሪ ቢያደርጉም ወሳኝ ተጫዋቾቻቸው ያሬድ ባዬ፣ ቸርነት ጉግሳ እና ሄኖክ አዱኛን በጉዳት ሊያገኟቸው እንዳልቻሉ ገልፀው ከእነዚህ ውስጥ በተለይ አንደኛው ያሬድ የመሐል ተከላካይ ስለሆነ የሄኖክን አለመኖርም ተከትሎ ማሸጋሸግ አስፈላጊ ሆኖ ስለተገኘ ፍቅሩ ዓለማየሁን ወደ ቀኝ መስመር አምጥቶ አንድ የመሐል ተከላካይ በመተካት ለጊዜው አሁን 24 ተጫዋቾች ይዘው እንደሚገኙ ተናግረዋል። ወደ ቦታው ከመጓዛቸው አስቀድሞ አንድ ተጫዋች በመቀነስ 23 ተጫዋች በመያዝ እንደሚጓዙ አክለው ተናግረዋል።
በመቀጠል በስፍራው ከተገኙ ጥቂት የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች አሰልጣኝ ገብረመድኅን ምላሽ ሰጥተዋል ፤ ከተነሱ ሃሳቦች መካከል
ከዚህ ቀደም ከብሔራዊ ቡድኑ የወዳጅነት ጨዋታዎች ምን ጠቃሚ ነገር ወሰዳችሁ?
“አንደኛው የወዳጅነት ጨዋታ ከዩጋንዳ ጋር ድሬዳዋ ላይ ነው ያደረግነው። ይህም ተስፋ ቡድን የሆነ ለቀጣይ ዋናውን ቡድን ይተካሉ ብለን ለረጅም ጊዜ የሚወስድ ስልጠና እየሰጠን በሂደት መተካት በሚለው መርህ መሠረት ያዘጋጀናቸውን ልጆች ያየንበት ጨዋታ ነበር። ይህ ጨዋታ ጥሩ ነው የሆነ ነገር የሰጠን ይመስለኛል። ከዚህ በኋላ የነበረው ከሌሴቶ ጋር በአዲስ አበባ ስታዲየም ያደረግነው ሁለት የወዳጅነት ጨዋታ ነው አንዱን አሸንፈናል አንዱን ተሸንፈናል። ከዚህ ጨዋታ ምን ተገኝቷል ከተባለ ጥሩ ነገሮች ተገኝተዋል። የወዳጅነት ጨዋታ ትርጉም ተጫዋቾችን በየቦታቸው ለማየት የሚያስችል የአቋም መለኪያ ነው። ሁልጊዜ በልምምድ ብቻ በማድከም ብዙም ውጤታማ አይኮንም። ብዙ ጊዜ የወዳጅነት ጨዋታ ማግኘት በእኛ ሀገር አልተለመደም ፌዴሬሽኑ ይህን አመቻችቶልናል በዚህም ጨዋታ ተስፋውን እና ዋናውን ቡድን አቀላቅለን ለመጫወት ነው የሞከርነው ጥሩ ነው። በተለይ ሁለተኛው ጨዋታ ላይ ጥሩ ምላሽ አግኝተናል። ወጣቶቹ ከዛ ጨዋታ በኋላ ጥሩ እየመጡ ነው አሁን ወደ ሃምሳ ፐርሰንት በዋናው ቡድን ይገኛሉ። የቀሩትም ቢሆን ካልሆኑ በቀር ልምድ ያላቸው አብዛኛው ብዙ ጨዋታ በብሔራዊ ቡድን ያልተጫወቱ ጥቂት የማይባሉ ወጣት ተጫዋቾች ቡድኑ ውስጥ አሉ። ከመተካካት አንፃር በወዳጅነት ጨዋታው ጥሩ ምላሽ አግኝተንበታል።
የዝግጅታችሁ የትኩረት ማዕከል ምን ላይ ነበር?
“እኛ ምን ጊዜም ቢሆን የምንጫወተው የራሳችን የምንከተለውን ጨዋታ መሞከር ነው። ምንድነው ከዚህ በፊት እንዳልኳችሁ ወደ ፊት የሚጫወት በፈጣን እንቅስቃሴ ውስጥ ወደ ፊት የሚገባ ቡድን መሥራት ነው። አሁንም በቂ የሆነ ፈጣን የኳስ ዝውውር እየተደረገ አይደለም እስካሁን ይቀረናል። ከዚህ ቀደም ረጅም ጊዜ ይጫወቱበት የነበረው መንገድ ብዙ ጊዜ ከኳስ ጋር መቆየትን የተላመዱ ተጫዋቾች ስላሉ ከዚህ ለማውጣት ጊዜ የሚፈልግ ይመስለኛል። ንኪኪዎችን በመቀነስ በፈጣን እንቅስቃሴ መግባት ያስፈልጋል። አብዛኛዎቹ ማለት ይቻላል ብዙዎቹ ኳስን ካልያዙ መጫወት የሚያስችል አቅም የላቸውም። ከዚህ እንዲወጡ የተለያዩ ስራዎች እየሰራን ነው ፤ እያስገደድን ማለት ነው። አንዳንዶቹ ቶሎ የመረዳት ነገር አላቸው አንዳንዶቹ አዝጋሚ ነው የመረዳት አቅማቸው።ስለዚህ ትኩረታችን በፈጣን እንቅስቃሴ ውስጥ እንዲገቡ የኳስ ንኪኪያችን ፈጣን እንዲሆኑ ለማሳደግ ጥረት እያደረግን ነው።
ስለ ሁለቱ ተጋጣሚ ሀገሮች ምንያህል በቂ መረጃ አላችሁ? ቡድኑስ ከስነልቦና አንፃር ለጨዋታው ተዘጋጅቷል?
“የመጀመርያው ተጋጣሚያችን ጊኒ ቢሳው በአብዛኛው ሁለም ማለት ይቻላል ከአውሮፓ የመጡ ተጫዋቾች ስብስብ ነው። በሙሉ ከአውሮፓ ስለመጡ በእኛ ስነ ልቦና ላይ የሚፈጥረው ነገር የለም። ሴራሊዮን ፣ ቡርኪናፋሶ ሌሎቹም ቢሆኑ ተመሳሳይ ነው ይህን መላመድ ያስፈልጋል። እነርሱ ፕሮፌሽናል እንደሆኑ ሁሉ የእኛም ውጭ ሄደው ባይጫወቱም ፕሮፌሽናል ናቸው። ይሄ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማድረግ ስነ ልቦና ላይ መስራት ነው። ከዚህ ውጭ ስነ ልቦናችን ጥሩ ሆኖ የአሸናፊነት ስሜት እንዲገኝ ለማድረግ ጥረት እያደረግን ነው። ከጊኒ ቢሳዋ ጋር ሜዳው ላይ ነው የምንጫወተው በሜዳው መጫወቱ የተወሰነ እገዛ ይኖረዋል የደጋፊ አቅም፣ ከሜዳው ጋር መላመድ እና የአየር ሁኔታ ሊወስዱብን ይችላሉ በተቻለ መጠን ይህን
ለመቀየር እየሰራን ነው”
ኢትዮጵያ መድንን እያሰለጠኑ በአሁን ወቅት ውጤታማ እየሆኑ ነው። ይህ ለብሔራዊ ቡድኑ ምን ያህል ጠቀሜታ አለው?
“የመጀመርያው እና ሁለተኛው የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታ የኔ መቀጠር አካካቢ ስለነበር ጨዋታው በተለይ ከመድን ውጤት መጥፋት ጋር ተያይዞ መላመድ ባለመቻል አስቸጋሪ ሁኔታ ነበር። እውነት ለመናገር ቡድናችን መድን ውጤታማ ባለመሆኑ ትንሽ አስቸጋሪ ነበር። አሁን መድን በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል። ተከታታይ ጨዋታ በማሸነፍ ወደ ሪከርድ እየሄደ ነው። ጥሩ እገዛ ይኖረዋል የአሸናፊነት አእምሮ በተጨዋቾች ላይ በራስ መተማመን ይጨምራል። ይህ በተጫዋቾች ብቻ ሳይሆን በአሰልጣኙም ላይ የአሸነፊነት ስነ ልቦና ያሳድጋል። የመድን በዚህ ሁኔታ መኖር ለብሔራዊ ቡድን የሚሰጠው በራስ መተማመን አለ። በማንኛውም መንገድ ከተሰራ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ማሳያ ነው። መድን በጣም መሰረታዊ ለውጥ ነው ያመጣው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም መሰረታዊ ለውጥ ያመጣል ብዬ አስባለው። የነበረው አጨዋወታችን ትንሽ ከዛ እየወጣን ነው። እውነት ለመናገር ሁለተኛ እና የመጀመርያ ጨዋታ መጥፎ የሚባል አልነበረም ጥሩ ነገሮች ነበሩ።”
የሱራፌል ዳኛቸው እና የአቤል ያለው አለመካተት ?
“ሱራፌል ባለፈው ባደረግነው ሁለት የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ወቅት ጥሩ አቋም ካሳዩ ቁልፍ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነበር። ወደ አሜሪካ ከሄደ በኋላ አሁን የት ጋር እንዳለ ማወቅ አልቻልንም። ምን ላይ እንዳለም አይታወቅም። ብዙ ጥረት ተደርጓል ግን በቡድን ደረጃ በጨዋታ እንቅስቃሴ ያለበትን ወቅታዊ አቋሙን ማግኘት ስላልተቻለ ለጊዜው ተዘሏል። ለወደፊቱ ግን በቅርብ ውድድር የሚያደርግ ከሆነ ጥሩ ነው። ልጁ በጣም አጋዥ ነው ቡድኑንም ያግዛል ብዬ አስባለው። የአቤል ያለውም ተመሳሳይነት አለው። ግብፅ ነው የሚጫወተው ባለፉት ጊዜያቶች ለመከታተል ሞክሬ ነበር። የተጫወተባቸው ጊዜያቶች የሉም። አንድ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተጫወተባቸው ጥቂት ደቂቃዎች ናቸው። ስምንት ደቂቃ፣ በተቀያሪ ሰዓት ካልሆነ በቀር ከዚህ ውጭ ምንም አልተጫወተም። ስለዚህ አለመጫወቱ በራሱ ተፅዕኖ አለው። እንደዛም ሆኖ አምጥተነው ነበር በወዳጅነት ጨዋታ ጥሩ ስላልነበረ አስተካክሎ መምጣት አለበት በሚል ነው የዘለልነው። እነዚህን ልጆች ማጣት ለጊዜው በተወሰነ መልኩ ተፅእኖ ማድረጉ አይቀርም። ነገር ግን ሌሎቹ ወጣት ተጫዋቾች በጊዜ ሂደት እየተላመዱ ሲሄዱ ጥሩ ነገር ሊፈጠር ይችላል።”
ቡድኑ መቼ ይሄዳል? ጨዋታውንስ መቼ ያከናውናል?
ወደ ጊኒ ቢሳዎ የምንሄደው ሰኞ ነው። ትንሽ የጉዞው ሁኔታ አስቸጋሪ ነው። ረጀም ጉዞ ነው ምን አልባት ከልምምድ ውጭ ሊያደርገን ይችላል ቀኑን ሙሉ ማለት ነው። ረጅም ጉዞ ስለሆነ። የምንጫወተው ከጊኒ ጋር ሐሙስ ነው። ከዛ መንገድ አለ ከጁቡቲ ጋር የምንጫወተው ደግሞ እሁድ ነው። ትንሽ የፕሮግራም አወጣጡ ከጉዞ ጋር ግምት ውስጥ የገባ አይደለም። ፊፋ አንዴ ያወጣሁትን ፕሮግራም መቀየር አልችልም በማለት ምላሽ እንደተሰጠ ነው ከፌዴሬሽን የነገሩኝ ባለው ጠባብ ጊዜ የሚቻለውን እናደርጋለን።”