የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ወልቂጤ ከተማ ተጫዋቾቹ የጠየቁትን ካልፈፀመ ለሌሎች ክለቦች አስተማሪ የሆነ ቅጣትን አስተላልፋለሁ ብሏል።
በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ የሚወዳደረው ወልቂጤ ከተማ በዘንድሮው የሊግ ጉዞው እንዳለፈው ዓመት ሁሉ ላለመውረድ እየታገለ ይገኛል። በተደጋጋሚ ለተጫዋቾቹ ወርሀዊ ደመወዛቸውን ባለመክፈሉ በፌዴሬሽኑ በተለያዩ ጊዜያት ቅጣት ሲጣልበት የነበረው ይህ ክለብ አሁንም ለዘጠኝ ተጫዋቾች ክፍያን ባለ መፈፀሙ ለቀረበበት ክስ ዕልባት ካልሰጠ ከባድ ውሳኔ ሊተላለፍበት እንደሚችል ታውቋል። የ5 ወራት ደመወዝ አልተከፈለንም በሚል ተመስገን በጅሮንድ ፣ ተስፋዬ መላኩ ፣ ሳምሶን ጥላሁን ፣ ሙሉዓለም መስፍን ፣ ጋዲሳ መብራቴ ፣ መሳይ አያኖ ፣ ጌቱ ሀይለማርያም ፣ ዳንኤል ደምሱ እና ፋሪስ ዕላዊ ያቀረቡትን የይከፈለን ጥያቄን ተንተርሶ ፌዴሬሽኑ በደብዳቤ እንዲህ ሲል ገልጿል።
“ክለቡ ወቅቱን ጠብቆ ደመወዝ ካለ መፈፀሙ በተጨማሪ ይባስ ብሎ ክለቡ ውድድር በብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች ምክንያት በተቋረጠበት ጊዜ አስፈላጊውን የትራንስፖርት ወጪ በመሸፈን ወደ መጡበት መሸኘት እንዲሁም አስፈላጊ ክፍያዎችን በመፈፀም ለዝግጅት መጥራት ሲገባው ተጫዋቾቹን ደመወዝ ካለመክፈል ጋር በተያያዘ ለተፈጠረባቸው የሥነ-ልቦና እና የኢኮኖሚ ችግር ትኩረት ባለመስጠት ወደ ዝግጅት እንዲገቡ ጥሪ የተደረገበት መንገድ አግባብነት አለው ብለን አናምንም ፤ በመሆኑም ክለቡ ለተጫዋቾቹ ያልከፈላቸው ደመወዝ በአምስት ቀናት ውስጥ በአስቸኳይ እንዲፈፀም እያሳሰብን ፤ ይህ ተግባራዊ የማይደረግ ከሆነ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ክለቡ ላይ ለሌሎችም ክለቦች ማስተማሪያ የሆነ ከባድን እርምጃን የሚወስድ መሆኑን እናሳውቃለን፡፡” በማለት ፌድሬሽን ጠንካራ መልዕክት አስተላልፏል።