በነገው ዕለት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን በሜዳዋ የምትገጥመውን ጊኒ ቢሳው የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አጠናክረናል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለ2026 የዓለም ዋንጫ ለማለፍ እየተካሄደ ባለው የማጣርያ ውድድር ሦስተኛ ጨዋታውን ለማከናወን ጊኒ ቢሳው ደርሷል ፤ ሶከር ኢትዮጵያም የዋልያዎቹን ተጋጣሚ የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አሰናድታዋለች።
በማጣርያ ውድድሩ ያስመዘገቡት ውጤት
ባለፈው መጋቢት ውሉን ባጠናቀቀው ባሲሮ ካንዴ ምትክ የቀድሞ የስፖርቲንግ ሊዝበን፣ አርሰናል፣ ፉልሀምና ሳውዝሀምፕተን ተጫዋች ሉዊስ ቦአ ሞርቴ አሰልጣኝ አድርገው የቀጠሩት ጊኒዎች በአሰልጣኙ ስር የመጀመርያ የነጥብ ጨዋታቸውን ነገ ያከናውናሉ።
ጊኒዎች ካካሄዷቸው ሁለት ጨዋታዎች አራት ነጥቦች በመሰብሰብ በግብ ክፍያ ተበልጠው በሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። በምድቡ የመጀመርያ ጨዋታ ከቡርኪናፋሶ ጋር ነጥብ ተጋርቶ በሁለተኛው ጨዋታ ጅቡቲን አንድ ለባዶ ማሸነፍ የቻለው ቡድኑ ሁለቱም መርሀ-ግብሮች ከሜዳው ውጭ ማከናወኑን ተከትሎ ኢትዮጵያና ግብፅን በሜዳው ያስተናግዳል። የዱር ውሾቹ በሰንጠረዡ የላይኛው ክፍል ተከታትለው የተቀመጡት ግብፅና ቡርኪናፋሶ ካይሮ ላይ መገናኘታቸውን ተከትሎ ደረጃቸውን የማሻሻል ዕድል ያላቸው ቢሆንም በአፍሪካ ዋንጫና አቋም መፈተሻ ጨዋታዎች ላይ አምስት ተከታታይ ሽንፈቶች ቀምሶ 13 ግቦች ያስተናገደው መጥፎ አቋማቸው ማስተካከል ይጠበቅባቸዋል።
አዲሱ አሰልጣኝ የተመለከቱ መረጃዎች
ከአስር ዓመታት በላይ ከዘለቀው የተጫዋችነት ሂወቱ በኋላ ሲንትረንሴ በተባለ በፖርቹጋል አራተኛ ዲቪዝዮን በሚሳተፍ ቡድን በዋና አሰልጣኝነት ከመስራቱ በስተቀር አብዛኛው የአሰልጣኝነት ሂወቱ የታዳጊ ቡድኖች በማሰልጠን ያሳለፈው የአርባ ስድስት ዓመቱ አሰልጣኝ በቅርብ ዓመታት በኤቨርተንና ፉልሀም የአሰልጣኝ ማርኮ ሲልቫ ምክትል ሆኖ ሰርቷል። አሰልጣኙ ኢትዮጵያን በመግጠም ከዓመታት በኋላ ወደ ዋና አሰልጣኝነት መንበር የሚመለስ ሲሆን ዋነኛ ዕቅዱ ሞሮኮ ለምታዘጋጀው የቻን ውድድር ማለፍ እንደሆነ ጠቅሶ “የዓለም ዋንጫው የማጣርያ ውድድር ከባድ ቢሆንም የተቻለንን እናደርጋለን” የሚል አስተያየት ሰጥቷል።
በሀገሪቱ ሊግ ባለው አናሳ እውቀት ምክንያት ተጫዋቾቹ በሚኒስተሩ ኤሚልያኖ ቴ አማካኝነት እንደተመረጡ በይፋዊ የፌርማ ስነ-ስርዓቱ ላይ የገለፀው አሰልጣኙ በቱርኩ ሁለተኛ ዲቪዝዮን ክለብ ኢዩስፖር የአካል ብቃት አሰልጣኝ የሆነውን አኔክስ ፔሬራን በአሰልጣኞች ቡድኑ ውስጥ አካቶታል።
የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋቾች
ጊኒዎች ከማንቸስተር ሲቲው እህት ክለብ ትኽዋ (Troyes) በውሰት ወደ ኦሎምፒክ ሊዮን አምርቶ የውድድር ዓመቱን ባገባደደው ማማ ሳምባ ባልዴ ትልቅ ተስፋ ጥለዋል። በሊዮን ቆይታው 23 ጨዋታዎች ተሰልፎ 2 ግቦች በማስቆጠር 3 ግብ የሆኑ ኳሶች ማቀበል የቻለው ይህ ፈጣን ተጫዋች የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች ነው። በመሰመር እንዲሁም በፊት አጥቂነት መጫወት የሚችለው የሀያ ስምንት ዓመቱ ሁለገብ ተጫዋች የመልሶ ማጥቃት ዋነኛ መሳርያ ነው። ተጫዋቹ በውድድር ዓመቱ 28 ድሪብሎች ሲያደርግ ከዛ ውስጥ 11ዱ የተሳኩ (take ons)ናቸው ፤ ዋልያዎቹ በውድድር ዓመቱ በጨዋታ በአማካይ 4.68 ድሪብሎች ያደረገውን ተጫዋች ለማቆም ልዩ ትኩረት ማድረግ ይኖርባቸዋል።
በቅርቡ ሀገሩን ማገልገል የጀመረው፤ ከዴንማርኩ ክለብ ሚችላንድ ጋር ጥሩ የውድድር ዓመት ያሳለፈውና በዓመቱ 17 ግቦች አስቆጥሮ ስድስት ግብ የሆኑ ኳሶች አመቻችቶ ያቀበለው ወጣቱ የፊት አጥቂ ፍራንኩሊኖ ዲዡም ከአንጋፋው አጥቂ ያልተናነሰ ልዩ ትኩረት ሊደረግበት የሚገባ ተጫዋች ነው። ከሳይፕረሱ አፖል ኔኮስያ ጋር የሊግ ዋንጫ ያሳካው አጥቂው ዳላስዮ ጎሜዝም ሳይረሳ። የዱር ውሾቹ በፈረንሳይ ሊግ 2 በሀያ ሁለት ጎሎች የሊጉ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ የጨረሰውን አሌክሳንደር ሜንዲ በስብስባቸው ማካተት አልቻሉም። ባለፉት ሦስት የውድድር ዓመታት በክለብ እግር ኳስ ሀምሳ ሰባት ግቦች ማስቆጠር የቻለው ይህ አጥቂ ለሀገሩ ሰባት ጨዋታዎች አከናውኗል።
ጊኒዎች ከወራት በፊት ሀያ ሺ ተመልካቾች በሚያስተናግደው ብሄራዊ ስታዲየማቸው ‘ሴፕተምበር 23’ ጨዋታዎች እንዲያከናውኑ ከካፍ ፍቃድ ማግኘታቸውን ተከትሎ ሁለቱን የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታዎች ለማስተናገድ ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል። የካፍ መስፈርቶች አሟልተው ጨዋታ ለማስተናገድ ብቁ ከሆኑ 26 ስቴድየሞች ውስጥ ዝቅተኛ የጥራት ደረጃ አላቸው ተብለው በዝርዝሩ ከተጠቀሱት የመጨረሻ ሦስት ስቴድየሞች አንዱ የሆነውና በ1989 ለአገልግሎት ክፍት የሆነው ስቴድየም ከዘጠኝ ወራት በኋላ የብሄራዊ ቡድን ጨዋታ ያስተናግዳል።