ያለፉትን ሦስት ዓመታት በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እየተጫወተ ያለው ኤርትራዊው አጥቂ ወደ አፍሪካ ክለቦች አልያም ወደ ስካንዲኒቪያ ሀገሮች የሚያደርገውን ዝውውር ለማጠናቀቅ ከጫፍ መድረሱን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ባህር ዳር ከተማን ከሦስት ዓመት በፊት በመቀላቀል ራሱን ከሊጉ ጋር ያስተዋወቀው እና ከባለፈው ዓመት አንስቶ በሀዋሳ ከተማ እያገለገለ የሚገኘው ኤርትራዊው አጥቂ ዓሊ ሱሌማን በዘንድሮ የውድድር ዓመት አስደናቂ ጊዜ እያሳለፈ ይገኛል።
የሊጉን ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት በአስራ ስድስት ጎሎች እየመራ የሚገኘው ኤርትራዊው አጥቂ በዚህ ዓመት ካሳየው ብቃት አንፃር ስሙ ከተለያዩ ክለቦች ጋር እየተነሳ ይገኛል። ከፈላጊ ክለቦች መካከል የታንዛኒያዎቹ ያንግ አፍሪካንስ እና ሲንባ እንዲሁም የግብፁ ክለብ እስማኤልያ መሆናቸውን ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።
የተጫዋቹን የዝውውር ሂደት እያሳለጠ የሚገኘው ወኪል አዛርያስ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፀው ከሆነ በዋናነት ሁለቱ የታንዛንያ ክለቦች ዓሊን የማስፈረም ከፍተኛ ፍላጎት በማሳየት ድርርድሩ በአብዛኛው መልኩ ከስምምነት የደረሰ መሆኑን ሲገልፅ የግብፁ እስማኤልያ በተመሳሳይ እጁ ወደ ዝውውሩ መግባቱን አመላክቷል።
ሆኖም ዝውውር ውጤታማ መሆን የሚችለው ዓሊ ሱሌማን ከሀዋሳ ከተማ ጋር ቀሪ የአንድ ዓመት ኮንትራት ያለው በመሆኑ ከክለቡ ጋር በሚደረግ ድርድር በሚደረስ ስምምነት የሚወሰን ሲሆን ከሀዋሳ ከተማ ከሚመለከታቸው ኃላፊዎች ጋር የዝውውሩን ሂደት አስመልክቶ ውይይት መደረጉን እና የዚህ ዓመት ውድድር ሲጠናቀቅ ጉዳዩ የሚታወቅ መሆኑን ተጠቅሷል።
በተያያዘ ዜና ከሌሎች ምንጮቻችን እንዳገኘነው መረጃ ከሆነ ዓሊ ሱሌማንን የማስፈረም ፍላጎት ካሳዩት ከአፍሪካ ክለቦች አልፎ ለጊዜው የክለቡን ስም ማግኘት ባልቻልነው በስካንዲኒቪያ የውስጥ በሚገኙ ክለቦች መካከል አንዱ ዓሊን ለመውሰድ የሚያደርገው ዝውውር ወደ መጠናቀቁ መድረሱን ሰምተናል።
በዓሊ ሱሌማን ዝውውር ዙርያ የሚኖሩ አዳዲስ ነገሮች ካሉ ተከታትለን የምናቀርብ ይሆናል።