አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ከዛሬው ጨዋታ በፊት ምን አሉ ?
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ከዛሬው ጨዋታ በፊት ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የሚድያ ክፍል ጋር ቆይታ አድርገዋል። የብሄራዊ ቡድኑ አባላት በጥሩ ሁኔታ ላይ እንዳሉ በመግለፅ የዛሬውን ጨዋታ ለማሸነፍ ጥረት እንደሚያደርጉ የገለፁት አሰልጣኙ የመርሀ-ግብር መጣበቡ ነገሮች አስቸጋሪ እንዳደረገባቸው አንስተዋል። አሰልጣኙ ጨምረውም በቡድኑ መሻሻሎች እንዳሉ፤ ለውጡ ግን በቂ እንዳልሆነ ጠቅሰው የሚገኙትን ዕድሎች ወደ ግብነት የመቀየር ክፍተት እንዳለ ገልፀዋል። የጨዋታ እቅዱን ለመተግበር የሚደረግ ጥረት ቢኖርም ሙሉ ለሙሉ የተዋጣለት እንዳልሆነ በመጥቀስም ቡድኑ ሁለቱም የሽግግር ወቅቶች ጥሩ እንደተንቀሳቀሰና በተለይም የመከላከል አደረጃጀቱ ጥሩ እንደነበር ተናግረዋል።
አሰልጣኙ ለዛሬው ጨዋታ ስለ ተደረገው ዝግጅት ተጠይቀው በሰጡት ምላሽም ጅቡቲን ለማሸነፍ ወደ ሜዳ እንደሚገቡና ተጫዋቾቹም ይህንን ለማሳካት በጥሩ ስነ-ልቦና እንደሚገኙ ጠቅሰው ለተጋጣሚያቸው ዝቅተኛ ግምት ባለመስጠት ጨዋታውን አሸንፎ መውጣት እንደሚገባ አንስተዋል። ” ደረጃ የሚፈጥረው የተወሰነ ነገር ቢኖርም ግን መገለጫ አይደለም፤ የሂሳብ ስራ አይደለም። ለቡድኑ ዝቅተኛ ደረጃ ባለመስጠት ጨዋታውን አሸንፈን መውጣት እንዳለብን ነው የተነጋገርነው፤ እስካሁን ድረስ መጥፎ ነገር አላየሁም ተነሳሽነታቸው፣ አንድነታቸውና ስነ-ስርዓታቸው ጥሩ ነው። ይሄ ራሱ አንድ ነገር ይነግረናል ቢያንስ ግማሽ መንገድ ተጉዘናል” ብለዋል።
ከቡድን ዜና ጋር በተያያዘም በመጨረሻው ጨዋታ ቢንያም ፍቅሬ ዘግይቶ ከመምጣቱ ውጭ ምንም አይነት ጉዳት እንዳልነበራቸው ገልፀው በዛሬው ጨዋታም በተመሳሳይ ቡድኑ ከጉዳት ነፃ እንደሆነና ፉዐድ ፈረጃ ከመጠነኛ ጉዳት አገግሞ በጥሩ ሁኔታ እንዳለ አስረድተዋል።