የዋልያዎቹ አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ
በዓለም ዋንጫ ማጣርያ ከጊኒ ቢሳው እና ጅቡቲ ጋር ያከናወናቸውን ጨዋታዎች አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የመሰብሰቢያ አዳራሽ አመሻሽ ላይ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የመግቢያ ንግግራቸውን ያደረጉት አሰልጣኙ ቡድኑ ለሁለቱ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ዝግጅቱን የ26 ተጫዋቾች በመጥራት ለመጀመር አስቦ የነበረ ቢሆንም ሦስት ተጫዋቾች በጉዳት መቅረታቸውን ተከትሎ አንድ ተጫዋች በመተካት ዝግጅታቸውን ሲያደርጉ ቆይተው አድካሚውን ጉዞ በማድረግ ወደ ማላቦ እንዳቀኑ ጠቅሰው እዛ ከደረሱ በኋላ የነበረው ከፍተኛ ሙቀት ተፅዕኖ እንዳደረገባቸው አንስተው ሆኖም ይሄን ልጆቹ ይህን ሰብረው እና ተቋቁመው ጥሩ መንቀሳቀሳቸውን ተናግረው በመቀጠል ረጅም የሆነውን ጉዞ ተጉዘን ቅዳሜ ከሰዓት ሞሮኮ እንደደረሱ እና የሚፈልጉትን ልምምድ እንዳይሰሩ መሰናክሎች እንደነበሩባቸው ተናግረው ከጁቡቲ ጋር የነበረውን ጨዋታ አስመልክቶ ተከታዩን ሀሳብ ሰጥተዋል።
“ ከጨዋታው በፊት የጅቡቲን ከሴራልዮን ጋር ያደረጉትን ጨዋታ ለመመልከት ችለናል። ጉልበት የተቀላቀለበትና በፍላጎት እንደሚጫወቱ አይተናል። ከእኛ ጋር በነበረው ጨዋታ ጉልበት የቀላቀለው አጨዋወታቸው እና በፍላጎት የመጫወት ነገራቸው እንዳለ ሆነ በጥልቀት የመከላከል አቅም ፈጥረው አይቻለው። በተጨማሪም ከውጭ ሀገር ገዝተው ዜግነት ሰጥተው የሚያጫውቷቸው ተጫዋቾች አሉ ፤ ትንሽ እኔ በፊት ከማቃቸው ለውጥ አይቼባቸዋለው። ዞሮ ዞሮ በጣም ከባድ ነበር። የነበረውን የኃይል አጨዋወት ዳኛው ከቁጥጥሩ ውጪ በሆነ ሁኔታ ሊዳኝ አልቻለም። የዲሲፒሊን ቅጣት አይሰጥም ነበር። የእኛ ልጆች በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ብዙ ተጭነው ለመጫወት ጥረት አድርገናል። በጥልቀት ይከላከሉ ስነበረ ይህን ለማስከፈት ሰብሮም ለመግባት ተችሏል። ግን ያገኘናቸውን አጋጣሚዎች የመጠቀም ችግር ነበር። እንደ አጠቃላይ ኢትዮጵያ ማግኘት የሚገባትን ሦስት ነጥብ አጥታለች። ጠቅለል ብዬ ሳየው ቡድናችን ቶሎ ብሎ ተጋጣሚ ግብ ክልል የመግባት ነገር ይታይበታል። የመጨረስ ችግር እራሱን የቻለ ችግር ነው። ከጊዜ ወደ ጊዜ ቡድኑ ለውጥ አለው ብዬ አስባለው። በቀጣይ ዕጣ ፈንታችን ምን ሊሆን እንደሚችል እናያለን። እንደ አጠቃላይ ጉዞው አድካሚ እና አሰልቺ ቢሆንም እንደ ቡድን ግን ተስፋ የሚሰጥ ነው”
አሰልጣኝ ገብረመድኅን በተጨማሪ የሰጧቸውን ሌሎች ሀሳቦችን በቀጣይ ይዘን እንመለሳለን።