👉“ሁልጊዜ አሰልጣኝ አምስት ከሃምሳ ውስጥ ይሄን ታደርጋለህ ብሎ ለአንድ ተጫዋች የቤት ስራ ሰጥቶት አያስገባም።”
👉“ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ማሳተፍ እውነት ነው ተገቢም ነው።”
👉“የአጨራረስ ችግርን በሁለት፣ በአንድ ሳምንት በአንድ ጊዜ አታመጣውም።”
አስቀድመን ባጋራናቹሁ መረጃ የብሔራዊ ቡድኑ አለቃ ገብረመድኅን ኃይሌ በዓለም ዋንጫ ማጣርያ ከጊኒ ቢሳው እና ጅቡቲ ጋር ያከናወኗቸውን ጨዋታዎች አስመልክቶ የሰጡትን የመግቢያ ንግግር አቅርበን ነበር። በማስከተል በቦታው የተገኙ የሚዲያ አካላት ካነሱላቸውን ጥያቄዎች ዋና ዋናዎቹን በመምረጥ የሰጡትን ምላሽ እንዲህ አቅርበናዋል።
ከጅቡቲ ጋር ባደረግነው ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ነው የደከመው ወይስ የጅቡቲ ጥንካሬ ነው ?
“ሁለቱም ነገር አለ። ጅቡቲ ላይ በተወሰነ መልኩ መሻሻል ታይቶባታል። የእነርሱ መሻሻል ግንዛቤው አንድ ነገር ሆኖ በጥልቀት ገብቶ የመከላከሉ ላይ ለውጥ አላቸው ፤ የእኛ ድክመት ብቻ ሳይሆን። የእኛ ድክመት የለም ለማለት አይቻልም። ለምሳሌ እኛ ቡድን ደካማ ሆኖ ጁቡቲን አላሸነፍ ማለት አልችልም። የተገኙ ዕድሎችን ያለመጠቀም ችግር ነበር። ማጥቃት ላይ ያለው ነገር ተስፋ ሰጪ ነው ብዬ የማስበው ከዚህ አንናፃር ብታዩት ጥሩ ነው። ከደረጃችን አንፃር አለማሸነፋችን ከደካማነት ተቆጠረ እንጂ ከጊኒ ቢሳው ጋር የነበረው ጨዋታ ጥሩ ነበርን። ጊኒ ቢሳው ከእኛ በደረጃም በርከት ያሉ ፕሮፌሽናል ተጫዋቾች ያሏቸው ናቸው። ልጆቻችን በሚችሉት አቅም ጥሩ ተንቀሳቀስሰዋል። ሁለተኛው ጨዋታ ላይ ድካም ታይቶባቸዋል።”
ከዚህ በኋላ ባሉ ቀጣይ ስምንት ወራት ዕረፍት ምን ለመስራት አስበሀል ?
“ስምንት ወር ጊዜ አለን ካዛም በፊት ጨዋታ ሊኖር ይችላል። አሁንም በቅርብ ጊዜ ጨዋታ ይኖራል። ቡድናችን በሂደት እየተገነባ ነው። ከዚህ በፊት ሰባት ስምንት ተጫዋቾች የሚቀየሩበት ሁኔታ ነበር። አሁን እንደዚህ ላይሆን ይችላል። ምክንያቱም ቡድኑ እየተገነባ በተወሰኑ ሰዎች ላይ ብቻ መስራት ይፈልጋል። ለምሳሌ አንዳንድ ተጫዋቾች የተመረጡት ወቅታዊ አቋማቸው ጥሩ ደረጃ ሳይሆን የተመረጡ አሉ። በሂደት ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር አብረው ሲሆኑ እያስተካከሉት የሚሄዱት ነገርን ታሳቢ በማድረግ ነው። አንዳንዶቹ በክለቦቻቸው ደካማ ነበሩ በስም መጥቀስ ይቻላል ግን አስፈላጊ ስላልሆነ ነው። እነዚህ ልጆች ግን ብሔራዊ ቡድን ሲመጡ ጥሩ ነበሩ። በአጠቃላይ በቀሪ ወራቶች ቡድኑ እየተላመዱ የመጡ ስድስት ወጣቶች አሉ ከእነዚህ ጋር ሎሎችን ጨመር አድርገን አዲስ ቡድን ከመንገባት አንፃር ጥሩ ሂደት ነው።”
በሁለቱ ጨዋታዎች የቡድኑ ጥንካሬ እና ድክመት እንዴት ተገመገመ ?
“በሁለቱም ጨዋታዎች የነበረው ድክመት በግልፅ የታየው የመጨረስ ችግር ነው። ምንም ጥርጥር የለውም። የአጨራረስ ችግርን በሁለት፣ በአንድ ሳምንት በአንድ ጊዜ አታመጣውም። ሂደት አንድ ነገር ነው። ወደ መጨረስ ለመግባት ጥረት ታደርጋለህ ። ሁልጊዜ አሰልጣኝ አምስት ከሃምሳ ውስጥ ይሄን ታደርጋለህ ብሎ አንድ ተጫዋች የቤት ስራ ሰጥቶት አያስገባም። ለረጅም ጊዜ ሊሰሩ የሚገቡ ነገሮች እንዳሉ አምናለው። ምክንያቱም ከታች ጀምሮ ወጣቶቹ ላይ ትኩረት ሊደረግበት የሚገባው አንዱ አጨራረስ ነው። እኔ ብዙ ስልጠናዎችን አያለው በጠባብ ጎል መጫወት እንጂ ከጎል ጋር ተያይዘው የሚሰሩ ስራዎች የሉም። ይሄ ደግሞ ከፍ ስንል እየጎዳን ነው። ሌላው ኳሶች የማባከን እንዲሁም ጥንካሬ የለንም። ይህ ችግር አለ ልምምዶቻችን በእጅ የመጫወት ያህል ቀላል ነው። በዚህም ኳሳችን ጥንካሬ የለውም። ለምሳሌ ግብጠባቂው ያዳናቸው ኳሶች ጥንካሬ የሌላቸው የከንዓን፣ የመስፍን በመሆኑ ነው። በአጠቃላይ ጠንከር ብሎ የመጫወት ችግር አለ ትኩረት ተደርጎ መሰራት አለበት። ረጅም ጊዜ የማየው ችግር ነው እየተንከባለለ የመጣ ነው።”
ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በመጠቀም ዙሪያ ?
“ከፌዴሬሽኑ ጋር እየተነጋገርኩ ነው። እውነት ለመናገር በጣም አስፈላጊ ነው። ብዙ አፍሪካውያን ቡድኖች የተቀየሩት የትውልድ ሀገራቸውን ተጫዋቾች በማምጣት ነው። ከእነርሱ ትምህርት በመውሰድ የእኛ ተጫዋቾች እንዲማሩ ማድረግ ያስፈልጋል ከሀገሪቱ ፖሊሲ ጋር ጥምር ዜግነት ያለቸው የሚሉ አንዳንድ ነገሮች አሉ። ነገር ግን አሁን ልንሰራበት ይገባል። በቀጣይ የአሜሪካ ጉዞ ይኖራል፣ ከዚህም በፊት የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያዎች ይኖራሉ። በአጠቃላይ ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ማሳተፍ እውነት ነው ተገቢም ነው። ለውጥ ለማምጣት አቅም ሊሰጡን የሚችሉ ልጆችን ማምጣት ያስፈልጋል።”