መረጃዎች | 107ኛ የጨዋታ ቀን

የሊጉ ውድድር ከቀናት ዕረፍት በኋላ በወሳኝ የመጨረሻ ሳምንታት ጨዋታዎች ነገ ይመለሳል ፤ ነገ የሚደረጉ ሁለት ተጠባቂ መርሃግብሮችን የተመለከቱ መረጃዎች በተከታዩ መልክ ቀርበዋል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ባህር ዳር ከተማ

አራት ሳምንታት ብቻ በሚቀሩት ሊጉ የሊጉን ክብር ለመቀዳጀት የላቀ ዕድል ይዘው የሚቀርቡት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በእጃቸው ያለውን የአምስት ነጥብ ልዩነት የማስጠበቅ ጥረታቸውን ነገ የሚጀምሩ ይሆናል ፤ በተለያየ አግባብ በወረቀት ደረጃ ፈታኝ ጨዋታዎች የሚጠብቋቸው ንግድ ባንኮች ይህን ፈተና የጣና ሞገዶቹን በመግጠም ይጀምራሉ።

በጠንካራ ወቅታዊ ብቃት ላይ የነበሩት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ሊጉ ዳግም ሲመለስ የቀደመውን ብቃታቸውን በፍጥነት መልሰው ማግኘት የግድ ይላቸዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተጋጣሚ ባህር ዳር ከተማ በ45 ነጥቦች በሰንጠረዡ 3ኛ ደረጃ ላይ ሲገኙ በመቻል ነጥብ መጣል ላይ የተጠንጠለጠለ ቢሆንም በሊጉ 2ኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቅን ያልማሉ።

ረዘም ላሉ ጊዜያት በዘለቀ ሽንፈት አልባ ጉዞ ላይ የሚገኙት ባህር ዳር ከተማዎች በነገው ጨዋታም ለተጋጣሚያቸው ብርቱ ፈተና እንደሚደቅኑ ይጠበቃል ፤ በሊጉ ለሁለተኛ ጊዜ ሁለቱን ቡድኖች የሚያገናኘው ጨዋታ በዋንጫ ፉክክክሩ ላይ ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ይጠበቃል።

በጣና ሞገዶቹ በኩል የቸርነት ጉግሳ እና የያሬድ ባየህ መመለስ መልካም ዜና ሲሆን ከሙጅብ ቃሲም በስተቀር ሌሎቹ የቡድን አባሎች ለጨዋታው ዝግጁ መሆናቸው ታውቋል።

ወልቂጤ ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና

በአስራ ስድስት ነጥቦች 14ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ወልቂጤ ከተማዎች በታችኛው የሰንጠረዡ ክፍል ትልቅ ትርጉም በሚኖረው ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡናን ይገጥማሉ። ሰራተኞቹ ስድስት ተከታታይ ጨዋታዎች ሽንፈት አስተናግደዋል፤ ቡድኑ ከበታቹ ያሉት ቡድኖች በተመሳሳይ ነጥብ አለመሳካታቸውን ተከትሎ የደረጃ ማሽቆልቆል ባይገጥመውም የነጥብ ልዩነቱ ግን ወደ ሁለት ጠቧል።

ሰራተኞቹ በሊጉ የመትረፍ ዕድላቸው በእጃቸው ቢገኝም በተከታታይነት ያስመዘገቡት ደካማ ውጤት ከቅርብ ተቃናቃኝቸው ሻሸመኔ ከተማ መሻሻል ጋር ተደምሮ ስጋት ውስጥ ይከታቸዋል።

ባለፉት ጨዋታዎች በርካታ ግቦች ያስተናገደው የቡድኑ የተከላካይ ክፍል በነገው ዕለት ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ብቻ አስር ግቦች ካስቆጠረው የቡና ጠንካራ የፊት መስመር ለሚገጥመው ፈተና የሚቋቋምበት መንገድም የጨዋታውን ውጤት ይወስነዋል። ከዚ በተጨማሪ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ኳስና መረብ ያላገናኘው የቡድኑ የፊት ጥምረት በጨዋታው የሚኖረው ብቃት ከወራጅ ቀጠናውን ለመሸሽ በሚያደርጉት ጉዞ ወሳኝ ነው።

በአርባ አራት ነጥቦች 4ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኢትዮጵያ ቡናዎች የደረጃ መሻሻልን እያለሙ ወደ ሜዳ ይገባሉ። ቡናማዎቹ አስር ግቦች ባስቆጠሩባቸው ተከታታይ ሦስት ድሎች የአፈፃፀም ክፍተታቸው ቀርፈዋል።  ቡድኑ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለመውሰድ ጠንካራ  ፍልሚያ እንደሚኖረው በሚጠበቀው በነገው ጨዋታ ፈታኝ የማጥቃት አደጋዎች ይገጥሙታል ብሎ ለመገመት ቢያዳግትም በአንዳንድ መርሀ-ግብሮች የሚታየበት  ያልታሰበ የመከላከል ድክመት ማረም ይጠበቅበታል።

ከዚህ በተጨማሪ ተጋጣሚያቸው ከአደጋው ክልል ለመራቅ ከጨዋታው ተስፋ የሚያሰንቀውን ወሳኝ ነጥብ ፍለጋ ላይ ያለ መሆኑም ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ የሚቀርብበት ዕድልም አለ ።

በኢትዮጵያ ቡና በኩል አብዱልሃፊዝ ቶፊቅ በነገው ጨዋታ ላይ በሕመም ምክንያት የማይኖር ተጫዋች ነው ፤ በወልቂጤ ከተማ የ5 ወራት ደመወዝ አልተከፈለንም በሚል ክለቡን የከሰሱት ተመስገን በጅሮንድ ፣ ተስፋዬ መላኩ ፣ ሳምሶን ጥላሁን ፣ ሙሉዓለም መስፍን ፣ ጋዲሳ መብራቴ ፣ መሳይ አያኖ ፣ ጌቱ ሀይለማርያም ፣ ዳንኤል ደምሱ እና ፋሪስ ዓላዊ ከክለቡ ጋር አለመገኘታቸውን ተከትሎ ከነገው ጨዋታ ውጭ ሲሆን ይህም ወልቂጤ ከተማ የነገውን ጨዋታ ያለ ሁለቱ ተቀዳሚ ግብ ጠባቂዎቹ እንዲያደርጉ የሚያስገድድ ይሆናል።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ባደረጓቸው 7 ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ቡና 6 በማሸነፍ ከፍተኛ የበላይነት ሲኖረው አንዱን አቻ ተለያይተዋል። ቡና 12፣ ወልቂጤ 6 ጎሎች አስቆጥረዋል።