ሪፖርት | የሊጉ መሪ ከመመራት ተነስቶ ነጥብ ተጋርቷል

በመጀመሪያው አጋማሽ በባህር ዳር በተቆጠሩበት ጎሎች እስከ 85ኛው ደቂቃ ድረስ 2ለ0 ሲመራ የነበረው ንግድ ባንድ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ባስቆጠራቸው ጎሎች አቻ ተለያይቷል።

በ27ኛ ሳምንት የመጀመሪያ እና እጅግ ተጠባቂ ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በ26ኛው ሳምንት ፋሲል ከነማን 1ለ0 ካሸነፉበት አሰላለፍ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገዋል። በዚህም ሐብታሙ ሸዋለም እና ኤፍሬም ታምራት ወጥተው ብሩክ እንዳለ እና አዲስ ግደይ ገብተዋል። የጣና ሞገዶቹ በአንጻሩ ከወላይታ ድቻ ጋር ያለግብ ሲለያዩ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ባደረጉት የሦስት ተጫዋቾች ፍጹም ፍትሕአለው ፣ ፍቅረሚካኤል ዓለሙ እና ዓባይነህ ፊኖ ወጥተው ያሬድ ባዬህ ፣ በረከት ጥጋቡ እና ጸጋዬ አበራ ተተክተው ገብተዋል።

ተጠባቂው ጨዋታ የመጀመሪያውን ሙከራ ከመዓዘን ምት አስተናግዶ ነበር። በዚህም ንግድ ባንክ በባሲሩ ዑመር አማካኝነት ጥሩ ኳስ ወደ ግብ ልኮ ዒላማውን ስቶበታል። በአቀራረብ ረገድ በመከላከሉም በማጥቃቱም የተሻሉት ባህር ዳሮች በተለይ የመሀል ሜዳው ላይ ያለውን ፍልሚያ በማሸነፍ ጨዋታውን ወደ ራሳቸው ለማድረግ ሞክረዋል። በተቃራኒው ባንኮች ከዚህ በፊት የማይታይባቸው የወረደ የኳስ ቁጥጥር ለተጋጣሚ ምቹ ሁኔታን ፈጥሮ ታይቷል።

ጨዋታው 30ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ባህር ዳር ከተማን በውድድር ዓመቱ አጋማሽ የተቀላቀለው ፀጋዬ አበራ ከፍፁም ጥላሁን የደረሰውን ኳስ በጥብቅ ምት የግቡን አግዳሚ አጋጭቶ መረብ ላይ አሳርፎ ቡድኑን መሪ አድርጓል። በፈጠራው ረገድ የተዳከሙት ንግድ ባንኮች ለተቆጠረባቸው ጎል አፀፋዊ ምላሽ ይሰጣሉ ተብሎ ቢጠበቅም ጠጣሩን የባህር ዳር የኋላ መስመር መስበር ቀላል አልሆነላቸውም።

ስል የሆኑት ባህር ዳሮች በ38ኛው ደቂቃ እጅግ ፈጣን የመልሶ ማጥቃት ሰንዝረው መሪነታቸውን ወደ ሁለት ከፍ አድርገዋል። በዚህም በተቃራኒ የፍፁም ቅጣት ምት ክልል አዲስ ግዳይ የተቀማውን ኳስ የጣናው ሞገዶቹ በፈጣን ሽግግር ወደ ላይኛው ሳጥን ልከውን የዓብስራ ተስፋዬ በጥሩ ሁኔታ ፍሬው ጌታሁን ጀርባ የሚገኘው መረብ ላይ አሳርፎታል።

እንደ ቡድን የተቸገረው ንግድ ባንክ ገና የመጀመሪያው አጋማሽ ሳይገባደድ ሁለት ተጫዋቾችን በመቀየር ወደ ጨዋታው ለመመለስ ቢጥርም በቀሪዎቹ የአጋማሹ ደቂቃዎች ወዲያው ለውጡ ፍሬያማ ሳያደርገው ቀርቷል። አጋማሹም በባህር ዳር ሁለት ለምንም መሪነት ተጠናቋል።

በሁለተኛው አጋማሽ በአንፃራዊነት ሻል ብለው ወደ ሜዳ የገቡት የአሰልጣኝ በፀሎት ተጫዋቾች ቶሎ ቶሎ ባህር ዳር የግብ ክልል ሲደርሱ ነበር። በተለይ በ53ኛው ደቂቃ ኪቲካ ጅማ ከብሩክ የደረሰውን ኳስ ተጠቅሞ የሞከረውና ፔፔ ሰይዶ በጥሩ ቅልጥፍና ያዳነው አጋጣሚ በባንክ በኩል አስቆጪ ነበረ። ከአራት ደቂቃዎች በኋላም በሌላ አጋጣሚ ከግራ መስመር የተሻማን ኳስ ባሲሩ በግንባሩ ግብ ለማስቆጠር ሞክሮ ዳግም የግብ ዘቡ ፔፔ ከልክሏቸዋል።

ባህር ዳሮች በሁለተኛው አጋማሽ ጫና በዝቶባቸው ያሳለፉ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜም በ60ኛው ደቂቃ ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር ፍሬውን ፈትነው ተመልሰዋል። ቡድኑ ግን የበለጠ ወደ ራሱ ግብ ሸሽቶ ለመከላከል ቅድሚያ በመስጠት ሲንቀሳቀስ ነበር። በዚህ ሂደት ቡድኑ ተደጋጋሚ ጥፋቶችን በራሱ የግብ ክልል አካባቢ በመስራት በቅጣት ምቶች ለባንክ የግብ ዕድል ማግኛ አማራጭ ቢሰጥም ባንክ መጠቀም አልቻለም።

ጨዋታው ሊጠናቀቅ ደቂቃዎች ሲቀሩት የባህር ዳሩ አምበል ያሬድ ባዬ ሳጥን ውስጥ ኳስ በእጅ በመንካቱ የፍፁም ቅጣት ምት ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተሰጥቷል። የፍፁም ቅጣት ምቱንም አዲስ ግዳይ ወደ ግብነት ቀይሮታል። በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች አሁንም ጫና ማሳደራቸውን የቀጠሉት ንግድ ባንኮች ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ተጠናቆ በተጨመረው 6 ደቂቃ መገባደጃ ላይ በአዲስ ግዳይ ሁለተኛ ጎል አቻ ሆነዋል። ጨዋታውም ሁለት አቻ ተፈፅሟል። ውጤቱን ተከትሎ እስከዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በዋንጫ ፉክክሩ ውስጥ የነበር ባህር ዳር ከተና በይፋ ከዋንጫው ፉክክር መውጣቱ ተረጋግጧል።

ከጨዋታው በኋላ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሠልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ አጀማመራቸው ትክክል እንዳልነበረ ተናግረው በሁለተኛው አጋማሽ ያሳዩት ብቃት ጥሩ እንደነበር በማመላከት ከትልቅ ቡድን ጋር እየተጫወቱ ከሁለት ለምንም ሁለት አቻ መለያየታቸው ጥሩ ነገር እንደሚያሳይ አስረድተዋል። እንደ ተጫዋቾቻችን እንቅስቃሴ ሦስት ነጥብ ይገባን ነበር ያሉት አሠልጣኝ ደግአረገ ይግዛው በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የነበራቸው የትኩረት ማጣት ውጤት እንዲያጡ እንዳደረገ ተናግረዋል።