በ27ኛው ሳምንት ሁለተኛ የጨዋታ ዕለት የሚካሄዱ ሁለት መርሀ-ግብሮች አስመልክተን ያዘጋጀናቸው መረጃዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል።
ፋሲል ከነማ ከ መቻል
በዋንጫ ፉክክሩ ወሳኝነት ያለው ሌላው የጨዋታ ሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል።
በአርባ ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ፋሲል ከነማዎች ከአምስት ተከታታይ ሽንፈት አልባ ሳምንታት በኋላ በመሪው ንግድ ባንክ ከደረሰባቸው ሽንፈት ለማገገም በሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠውን መቻል ይገጥማሉ።
ፋሲል ከነማ ከባለፉት አምስት ጨዋታዎች በሦስቱ ግቡን ያላስደፈረና ሁለት ግቦች ብቻ ያስተናገደ ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ገንብቷል፤ ይህ ጠንካራ ጎኑም ከሊጉ ጥቂት ግቦች ካስተናገዱ ክለቦች ተርታ ያስመድበዋል። ሆኖም መሪው ንግድ
ባንክን በመገጠመት ጨዋታ ላይ ለረዣዥም ኳሶች እጅግ ተጋላጭ የነበረውና የተጋጣሚን ዋነኛ የማጥቅያ መስመር ያላገናዘበ የተከላካዮች የቦታ አያያዝ ክፍተት ከወዲሁ መታረም አለበት። ከዚ በተጨማሪ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው የግል ተጫዋቾች ስህተት አሁንም ያልተቀረፈ ችግር ሆኖ ዘልቋል፤ ቡድኑ በመጨረሻው መርሀ-ግብር በግልፅ የግል ስህተቶች ሁለት አደጋ የፈጠሩ ሙከራዎች ማስተናገዱ ሲታይ ችግሩ አንገብጋቢ መፍትሔ እንደሚያስፈልገው መገንዘብ ይቻላል።
የዐፄዎቹ ቡድን በእርጋታ ኳስን መስርቶ ለመውጣት የሚጥር ቡድን እንደሆነ አያጠያይቅም። ይህ ፍላጎት ቡድኑ ላይ ቢኖርም ግን ውህደቱ ጥሩ ኳስ ይዞ የሚጫወት ስብስብ ሳያስመስለው ቀርቷል። ቡድኑ ባለፉት አራት ጨዋታዎች ሦስት የተለያዩ የአማካይ ጥምረቶች አቀያይሮ መጠቀሙም ለውህደቱ መላላት እንደ አንድ ምክንያት ሊጠቀስ ይችላል። ከዚ በተጨማሪ የቡድኑ የፊት መስመር ለማጠናከር የመሀል ሜዳ ተጫዋቾቻቸውን ወደ ግብ ማቅረብ እና የግብ ማግባት ሂደቱን ማገዝ ከአሰልጣኙ የሚጠበቅ የቤት ስራ ነው።
በመጨረሻው ጨዋታ በዋንጫ ፉክክሩ አንድ እርምጃ ወደ ኋላ የሚያስቀራቸው ውጤት ያስመዘገቡት መቻሎች መሪው ንግድ ባንክ ነጥብ መጣሉን ተከትሎ በፉክክሩ ለመግፋት ሙሉ ነጥብ አስፈላጊያቸው ነው።
ጦሩ ባለፉት አራት ጨዋታዎች በብዙ መመዘኛዎች የተሻሻለና በተጠቀሱት መርሀ-ግብሮች አስር ግቦች ያስቆጠረ ውጤታማ የማጥቃት አጨዋወት ገንብቷል። ቡድኑ አማካዮቹን ማጥቃቱ ላይ ይበልጥ ከማሳተፍ በዘለለ የግብ ምንጮቹን ማስፋቱ አጨዋወቱን ውጤታማ አድርጎታል። ቡድኑ እርግጥ ፈጣን ጥቃት መሠንዘር ላይ አደገኛ ቢሆንም ተጋጣሚው ጥሩ የመከላከል አደረጃጀት ያለውና ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ ያስተናገደ መሆኑ ሲታይ ፈተናው ቀላል እንዳልሆነ መገመት አያዳግትም። ቡድኑ በነገው ጨዋታ መሐል ለመሐልና በመስመር ከሚሰነዝራቸው ጥቃቶች በተጨማሪ የግብ ዕድሎች መፍጠርያ መንገዶች ማብዛት እጅግ አስፈላጊው ነው።
ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ያስቆጠረው የዐፄዎቹ የማጥቃት አቀራረብ ለጦሩ የኋላ ክፍል የስጋት ነጥብ ይሆናል ብሎ በእርግጠኝነት መናገር ባይቻልም ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ብቻ አራት ግቦች ያስተናገደው የቡድኑ አደረጃጀት በቀጣይ መርሀ-ግብሮች የተጋጣሚን የመልሶ ማጥቃት ኳሶች የሚያቋርጥበትን መንገድ ማጤን የግድ ይለዋል።
ዐፄዎቹ በኩል እዮብ ማትያስ፣ አምሳሉ ጥላሁንና ይሁን እንደሻው በጉዳት፤ ዋና አሰልጣኙ ውበቱ አባተ ጨምሮ ጋቶች ፓኖምና ምኞት ደበበ ደግሞ በቅጣት ምክንያት የማይሰለፉ ተጫዋቾች ናቸው። የመቻልን የቡድን ዜና ለማግኘት ያደረግነው ጥረት የቡድኑ አባላት መረጃ ለመስጠት ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ማካተት አልቻልንም።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 12 ጊዜ ተገናኝተው ፋሲል ከነማ ስድስት ጨዋታ በማሸነፍ የበላይነት ሲኖራቸው መቻል ሦስት ጨዋታዎች አሸንፏል። ቀሪዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት የተፈፀሙ ናቸው። ፋሲል 16 ሲያስቆጥር መቻል 8 አስቆጥሯል።
ድሬዳዋ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ
በስድስት ነጥቦች የሚበላለጡና የመጨረሻው ሳምንት ድላቸው ለማስቀጠል ወደ ሜዳ የሚገቡት ቡድኖች የሚያገናኘው ጨዋታ አስመልክተን ያዘጋጀናቸው መረጃዎች እንደሚከተለው አቅርበናቸዋል።
ከሦስት ድል አልባ ሳምንታት በኋላ ወልቂጤ ከተማን ሦስት ለባዶ በማሸነፍ ወደ ድል የተመለሱት ብርቱካናማዎቹ ደረጃቸው ለማሻሻል አልያም ባሉበት ለመርጋት ሦስት ነጥብ ማግኘት ይኖርባቸዋል።
በቅርብ ሳምንታት ግቦችን በቀላሉ የማያስተናግድ ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት የነበራቸው ድሬዳዋ ከተማዎች በኢትዮጵያ መድን ከገጠማቸው አስከፊ ሽንፈት በፊት ባከናወኗቸው ስድስት ጨዋታዎች በጨዋታ በአማካይ 0.8 ግቦች ብያስተናግዱም በተጠቀሰው ጨዋታ የነበራቸው ደካማ የመከላከል አቅም አምስት ግቦች እንዲያስተናግዱ ምክንያት ሆኗል። ቡድኑ ወልቂጤ ከተማን ባሸነፈበት ጨዋታ የተለመደው ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ዳግም ከመመለሱም በተጨማሪ ከአስራ ሦስት ጨዋታዎች በኋላ በአንድ ጨዋታ ሦስት ግቦች አስቆጥሮ መውጣቱ ለነገው ጨዋታ ትልቅ የስነ-ልቦና ስንቅ ይሆነዋል ተብሎም ይገመታል፤ ሆኖም በነገው ዕለት በቀላሉ ለጥቃት የማይጋለጥ ዓይነት ቡድን እንደመግጠሙ የማጥቃት አቅሙን ከፍ አድርጎ መቅረብ ይጠበቅበታል።
በአርባ ሦስት ነጥቦች 5ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ፈረሰኞቹ በመጨረሻው መርሀ-ግብር ከሰባት ሳምንታት ጥበቃ በኋላ ከናፈቃቸው ድል ታርቀዋል።
ቡድኑ ሲዳማ ቡናን አንድ ለባዶ በመርታት ዳግም ወደ አሸናፊነት መመለሱ እንደ አንድ አወንታ የሚጠቀስለት ነጥብ ቢሆንም በእንቅስቃሴ ረገድ አሁንም ይበልጥ መሻሻል ይጠበቅበታል። በተለይም ግልፅ የግብ ዕድሎች ፈጠራ ላይ ያለበት ውስንነት አፋጣኝ መፍትሔ የሚያስፈልገው ክፍተት ነው፤ ቡድኑ አልፎ አልፎ ረዘም ያሉ ኳሶችን በመጣል ዕድሎች ለመፍጠር ጥረቶች ሲያደርግ ቢታይም በአጥጋቢ ሁኔታ ችግሩን የቀረፉለት አይመስልም። እምብዛም ውጤታማ ያልሆነው የቡድኑ ፊት መስመር ከተጋጣሚው የመከላከል ጥንካሬ አንፃር ካየነው በነገው ጨዋታ በብዙ መንገድ መስተካከል እንደሚኖርበት መገንዘብ ይቻላል። ከዚ በተጨማሪ አልፎ አልፎ የሚታየው ደካማ የግል ውሳኔዎች ማስተካከል የማጥቃት ሂደቱን የማሻሻል ሚናቸው ቀላል የሚባል አይደለም።
የቅዱስ ጊዮርጊስ የተከላካይ መስመር ቀደም ባሉ ሳምንታት የግብ ክልላቸው በቀላሉ እንዳይደፈር ማድረግ ላይ ስኬታማ መሆን ችለው ነበር፤ በቅርብ ሳምንታት ግን የቡድኑ የመከላከል አደረጃጀት ለጥቃቶች ተጋላጭ እየሆነ እንደመጣ የመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ጠቋሚ ናቸው። ቡድኑ በተጋጣሚዎች ደካማ የውሳኔ አሰጣጥ ችግር ከአንድ ግብ በላይ ማስተናገድ ባይችልም ክፍተቱን ቶሎ መቅረፍ ካልቻለ ዳግም በጨዋታዎች እጅ እንዲሰጥ ምክንያት ሊሆነው ይችላል።
ብርቱካናማዎቹ ያሬድ ታደሰ፣ ዳዊት እስጢፋኖስና ዘርአይ ገብረስላሴ በጉዳት፤ ካርሎስ ዳምጠው ደግሞ በቅጣት ምክንያት አያሰልፉም፤ የቻርለስ ሙሴጌ መሰለፍም አጠራጣሪ ነው። ፈረሰኞቹም የመስመር ተከላካዩ ሄኖክ አዱኛ ግልጋሎት አያገኙም።
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ለ23 ጊዜያት ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 14ቱን በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ 4ቱን አሸንፏል። ቀሪዎቹ አምስት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ፍፃሜያቸውን አግኝተዋል። ፈረሰኞቹ 38፣ ብርቱካናማዎቹ 19 ጎሎች አስቆጥረዋል።