ፌዴሬሽኑ ሀምበርቾ ላይ ከባድ ቅጣትን አስተላልፋለሁ ብሏል

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ሀምበርቾ በተጫዋቾቹ ላይ ከፍተኛ በደል የፈፀመ ክለብ ነው በማለት ለሌሎች ክለቦች የሚያስተምር ቅጣትን እጥላለሁ ብሏል።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ የሆነው እና በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ የሚገኘው የሀምበርቾ እግር ኳስ ክለብ በተጫዋቾቹ ላይ እያደረሰ ባለው እንግልት ፌዴሬሽኑ ከባድ ቅጣት ለመጣል እገደዳለሁ ብሏል። እንደ ኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን ገለፃ በኢትዮጵያ እግርኳስ ውስጥ ከየትኛውም ጊዜ በተለየ መልኩ እግርኳስ ተጫዋች ላይ ከፍተኛ የሆነ በደል በመፈፀም ላይ እንደሚገኝ በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ ተጫዋቾች የደረሱን ቅሬታዎች ያሳያሉ ብሏል።

ሀምበርቾ በዓመቱ መጀመሪያ ከተጫዋቾች ጋር በገባው ውል መሠረት የደመወዝ ከፍያ አለመፈፀሙን አንዱ ማሳያ ክለቡ በተለያዩ ጊዜያት ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽ/ቤት ጋር ባደረጋቸው የገፅ ለገፅ ውይይቶች እንዲሁም በደብዳቤ ክፍያ አለመፈፀሙን አምኖ በቀጣይ ጊዜያት እንደሚከፍል የገለፀበት  ነው ያለው ፌዴሬሽኑ ፤ በተጨማሪም ክፍያ አለመፈፀሙን ከክለቡ ተጫዋቾች በሚደርሱን ተደጋጋሚ ቅሬታዎች አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡ እንዲሁም ክለቡ የሚጠበቅበትን ክለባዊ ግዴታን ሳያሟላ የደመወዝ ክፍያ ጥያቄን ያነሱ ተጫዋቾችን ላልተወሰነ ጊዜ ያገዳቸው መሆኑን በደብዳቤ ለተጫዋቾቹ ማሳወቁንም ፌዴሬሽኑ ጠቅሷል፡፡ ደብዳቤው በግልባጭ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እንደደረስ ለማስመሰል የተሞከረበትም አካሄድ እንደ ተቋም ክለቡ ላይ እምነት እንዳይኖረን አድርጓል በማለት ተከታዩን ውሳኔ ፌዴሬሽኑ ይፋ አድርጓል።

በውሳኔውም ይህ ተግባር በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፍፁም ተቀባይነት የሌለው ስለሆነ ከለቡ በአስቸኳይ ይህንኑ ተረድቶ የተጫዋቾቹን ክፍያ አጠናቆ እንዲከፍል እና ይህም በአምስት ቀናቶች ውስጥ እንዲሆን እንዲሁም ለተጫዋቾቹ የፃፈውን የእግድ ደብዳቤ በመሻር ደመወዛቸውን በአስቸኳይ በመክፈል ወደ ስራ እንዲመልስ እና በሪፖርት ለፌዴሬሽኑ እንዲያሳውቅ በጥብቅ አሳስቧል።  ይህ ተግባራዊ ሳይሆን ቢቀር የኢትዮጵያ አግርኳስ ፌዴሬሽን ለሌሎችም ክለቦች አስተማሪ የሆነን እርምጃ በክለቡ ላይ የሚወስድ መሆኑን አረጋግጧል።

ክለቡ ነገ ከሲዳማ ቡና ጋር ላለበት የ27ኛ ሳምንት መርሀግብር ልምምዱን ዛሬ ይጀምራል።