የ27ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ነገ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይቀጥላል፤ መርሀ-ግብሮቹን አስመልክተን ያነሳናቸው ነጥቦች እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።
ሀዋሳ ከተማ ከ አዳማ ከተማ
ሁለት ውጤታማ የማጥቃት ጥምረት ያላቸውን ቡድኖች የሚያገናኘውና በርከት ያሉ ግቦች ይቆጠርበታል ተብሎ የሚጠበቀው ጨዋታ የዕለቱ ቀዳሚ መርሀ-ግብር ነው። ከቡድኖቹ አሁናዊ የፊት መስመር ጥንካሬ በተጨማሪም በሁለቱም ክለቦች የግንኙነት ታሪክ በጨዋታ በአማካይ ከሁለት ግብ በላይ መቆጠሩም በነገው ጨዋታ በርከት ያሉ ግቦች እንድንጠብቅ ያደርጋል።
በጦሩ ከደረሰባቸው ሽንፈት በኋላ ሀድያ ሆሳዕና ላይ ድል ያደረጉት ሀይቆቹ በጨዋታው ወደ አሸናፊነት መንገድ ከመመለሳቸው ባለፈ የመከላከል አደረጃጀታቸው ላይ ውስን መሻሻሎች በማሳየት የተጋጣሚን ጥቃት በተሻለ መንገድ መመከት ችለዋል። ቡድኑ በመቻሉ ጨዋታ ሦስት ግቦች ካስተናገደ በኋላ በፊት መስመር ላይ ልዩነት ፈጣሪ የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾች ካካተተው ቡድን ጋር ገጥሞ በክፍት የጨዋታ እንቅስቃሴ ግብ ሳያስተናግድ መውጣቱም የመሻሻሉ ማሳያ ነው። በዋነኝነት የዐሊ ሱሌይማንን ፍጥነት ያማከለ የማጥቃት ሽግግር የሚያዘወትረው ቡድኑ በቅርብ ሳምንታት ወዲህ እንደከዚ ቀደም በርከት ያሉ የግብ ዕድሎች መፍጠር ሲያዳግተው ብንመለከትም ግቦች ከማስቆጠር ግን አልቦዘነም። በነገው ዕለትም በጥሩ የውጤታማነት መንገድ ላይ ያለው የአፈፃፀም ብቃት ማስቀጠል ቁልፍ ጉዳይ መሆኑ የማይቀር ነው።
በአርባ አንድ ነጥቦች 6ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት አዳማ ከተማዎች ከአስከፊው ሽንፈት ለማገገም ሀዋሳ ከተማን ይገጥማሉ።
እርግጥ ነው አዳማ ከተማ በመጨረሻው መርሀ-ግብር በኢትዮጵያ መድን የአራት ለአንድ አስከፊ ሽንፈት ደርሶበታል፤ ሆኖም ቡድኑ ባለፉት አስር ጨዋታዎች ጥሩ እንቅስቃሴ ከማድረግ በዘለለ በሁለት መርሀ-ግብሮች ብቻ ሽንፈት ማስተናገዱ ሲታይ በነገው ጨዋታ ቀላል ግምት እንዳይሰጠው ያስገድዳል። ከሽንፈቱ በፊት ባካሄዷቸው አምስት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ ያስተናገዱት አዳማዎቹ በነገው ጨዋታ ከዚ ቀደም የነበረውን ጠንካራ ጎን ማስቀጠል ዋነኛ አላማቸው ይመስላል። የነገው ተጋጣሚያቸው ጥሩ የአፈፃፀም ብቃት ያለው ሀዋሳ ከተማ እንደመሆኑም የኋላ መስመራቸው በድጋሚ እርጋታውን እንዳያጣ የሚያስችሉ ስራዎች መስራት ይጠበቅባቸዋል።
ሀዋሳ ከተማዎች በቅጣት ምክንያት የፀጋአብ ዮሐንስን ግልጋሎት አያገኙም፤ በአዳማ ከተማ በኩልም በቤተሰብ ጉዳይ ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጭ ከሆነው ጀሚል ያዕቆብ ውጭ የተቀሩት የቡድኑ አባላት ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ናቸው።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለ44 ጊዜያት ያህል ተገናኝተው ሀዋሳ 19 አዳማ ደግሞ 13 ጊዜ ሲያሸንፉ 12 ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርተዋል። ጎል በሚበረክትበት የሁለቱ ቡድኖች ፍልሚያ ሀዋሳ ከተማ 52፣ አዳማ ከተማ 48 ጎሎች አስቆጥረዋል።
ሀምበርቾ ከ ሲዳማ ቡና
በስምንት ነጥቦች ግርጌ ላይ የተቀመጡት ሀምበርቾዎችና ከተከታታይ ሁለት ሽንፈቶች ወደ ድል ለመመለስ የሚያልሙት ሲዳማ ቡናዎች የሚያደርጉት ጨዋታ የዕለቱ ሁለተኛ መርሀ-ግብር ነው።
ከኢትዮጵያ ቡናው የስድስት ለአንድ ሽንፈት መልስ ሲዳማ ቡናን የሚገጥሙት ሀምበርቾዎች የተሟጠጠውን የመትረፍ ተስፋቸው ይዘው ወደ ጨዋታው ይቀርባሉ።
የመጀመርያውን ዙር ሰባት ነጥቦች ይዞ ያጠናቀቀው ቡድኑ በሁለተኛው ዙር ይበልጥ ተዳክሞ ታይቷል፤ ከአስራ አንድ ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ በማሳካትም በዚህ ዙር ዝቅተኛው ነጥብ የሰበሰበ ቡድን ያደርገዋል።
ሀምበርቾ በመጨረሻው ጨዋታ ከሜዳ ውጭ ያሉ ጉዳዮች አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳሳደሩበት በሚያሳይ መልኩ በሁሉም ረገድ ተዳክሞ ታይቷል፤ ቡድኑ በጊዜ በጎዶሎ ተጫዋች ለመጫወት መገደዱ የጨዋታውን መልክ ቢቀይረውም ከአራት ተከታታይ ጎል አልባ ጨዋታዎች በኋላ ኳስና መረብ ከማገናኘት ባለፈ አወንታዊ ነገር አላስመለከተም። ሀምበርቾዎች አራት ጨዋታዎች ብቻ በሚቀሩት ውድድር የመጨረሻውን ተራፊ ቡድን ለመሆን እየታገለ ከሚገኘው ወልቂጤ ከተማ ጋር በስምንት ነጥቦች ልዩነት ርቀው ይገኛሉ፤ በነገው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ማግኘት የደረጃ ለውጥ ባያመጣላቸውም ከበላያቸው ወዳሉት ቡድኖች በነጥብ ቀርበው እስከ መጨረሻው ሳምንት ድረስ ላለመውረድ እንዲፋለሙና ጨርሶ ላልጠፋው የመትረፍ ተስፋቸው አስፈላጊ ነው። ሆኖም ቡድኑ ከነገው ጨዋታ በፊት ልምምድ ሳይሰራ ወደ ጨዋታ መግባቱ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ አይቀሪ ነው።
ሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች አስተናግደው ላለፉት ሦስት ጨዋታዎች ከድል ጋር የተራራቁት ሲዳማ ቡናዎች የውድድር ዓመቱን የተሻለ ደረጃ ይዘው ለማጠናቀቅ ከቀሩት መርሀ ግብሮች በአንፃራዊነት ቀላል ፉክክር ይጠብቃቸዋል ተብሎ ከሚገመተው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ይዘው መውጣት ይጠበቅባቸዋል።
ሲዳማ ቡናዎች ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ምንም እንኳ ሦስት ነጥብ ማሳካት ባይችሉም ከዛ በፊት ከተካሄዱ ሁለቱ ጨዋታዎች በአንፃራዊነት በሜዳ ላይ ተረጋግተው የታዩበት ነበር። ከሀዋሳ ከተማና አዳማ ከተማ ጋር ባካሄዷቸው ሁለት ጨዋታዎች የተጋጣሚዎች ጥቃት በመመከትም ሆነ የግብ ዕድሎች በመፍጠር ረገድ አመርቂ እንቅስቃሴ ማድረግ አልቻሉም፤ በሁለቱም ጨዋታዎች ተጋላጭ ከነበረው የመከላለል አደረጃጀት ባለፈ ያስቆጠሯቸው ሁለት ግቦችም መነሻቸው የቆመ ኳስ ነበር። ቅዱስ ጊዮርጊስን በገጠሙበት የመጨረሻው መርሀ-ግብር ግን ምንም እንኳ ሽንፈት ብያስተናግዱም በብዙ ረገድ ተሻሽለው ቀርበዋል። በተለይም የግብ ዕድሎች በመፍጠር በኩል የታየው ለውጥ በጉልህ ይጠቀሳል፤ በነገው ዕለትም በጨዋታው የታየው ትልቅ የአፈፃፀም ክፍተት መቅረፍ ይጠበቅባቸዋል።
ከጨዋታ ዕለቱ በፊት ልምምድ ያልሰሩት የሀምበሪቾ ተጫዋቾች አሁንም በተሟላ ሁኔታ ወደ ጨዋታው ላይቀርቡ እንደሚችሉ ሰምተናል፤ ከዚ በተጨማሪ በመጨረሻው መርሀ-ግብር በቀይ ካርድ ከሜዳ የወጣው ሙና በቀለ በቅጣት የማይሰለፍ ተጫዋች ነው። በሲድማ ቡና በኩል ግን በግል ጉዳይ ምክንያት በጨዋታ የመድረሱ ነገር አጠራጣሪ ከሆነው ይገዙ ቦጋለ ውጭ ሙሉ ስብስባቸውን ይዘው ወደ ጨዋታው ይቀርባሉ።
ሁለቱ ቡድኖች በታሪካቸው ለመጀመርያ ጊዜ ባካሄዱት ጨዋታ ሀምበርቾዎች የውድድር ዓመቱ ብቸኛው ድል አሳክተዋል።