በዋንጫ ፉክክር ውስጥ እጅግ ተጠባቂ በነበረው መርሐግብር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር አንድ አቻ በመለያየት ወሳኝ ሁለት ነጥቦች መጣላቸውን ተከትሎ ከተከታያቸው መቻልም በአንድ ነጥብ ብቻ በልጠው ወደ መጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ያመራሉ።
ቅዱስ ጊዮርጊሶች በ27ኛ ሳምንት በድሬዳዋ ከተማ ከተሸነፈው ስብስብ ባደረጓቸው ሁለት ለውጦች አማኑኤል እንዳለ እና አማኑኤል ኤርቦን አስወጥተው በምትካቸው ቢኒያም እንዳለ እና ዳግማዊ አርዓያን ሲጠቀሙ በአንፃሩ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በተመሳሳይ በ27ኛ ሳምንት ከባህር ዳር ከተማ ጋር ነጥብ ከተጋራው ስብስብ ባደረጓቸው ሁለት ለውጦች ተስፋዬ ታምራት እና ብሩክ እንዳለን አስወጥተው በምትካቸው ኤፍሬም ታምራት እና ሀብታሙ ሸዋለምን በመተካት ለዛሬው ጨዋታ ቀርበዋል።
ተመጣጣኝ ፉክክር በታየበት የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ 15 ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች ምንም እንኳን ዒላማቸውን ሳይጠብቁ ቢቀሩም በሳይመን ፒተር እና የዓብስራ ተስፋዬ እጅግ ጥሩ የሚባሉ አጋጣሚዎችን መፍጠር ችለዋል።
በሂደት የጨዋታ ቁጥጥራቸውን እያሳደጉ የመጡት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በ17ኛው ደቂቃ ቀዳሚ ለመሆን ተቃርበው ነበር ፤ ባሲሩ ዑመር ከመሀል ሜዳ አካባቢ ከተከላካዮች ጀርባ የጣለለትን ኳስ ተጠቅሞ ፉዓድ ፈረጃ ያገኘውን አጋጣሚ ወደ ግብ ቢሞክርም ጥረቱ በባህሩ ነጋሽ መክኖበታል።
የውሃ ሰማያዊ ለባሾቹ የበላይነት እያየለ በመጣበት ጨዋታ በ20ኛው ደቂቃ ግን ፈረሰኞቹ ሳይጠበቁ መሪ መሆን ችለዋል ፤ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተጫዋቾች የቅብብል ስህተት መነሻውን ያደረገውን ኳስ ዳግማዊ አርዓያ ወደ ሳጥን ውስጥ ይዞ በመግባት ወደ ውስጥ ያሻማውን ኳስ ኤፍሬም ታምራት በራሱ ግብ ላይ በማስቆጠር ቅዱስ ጊዮርጊስን ቀዳሚ አድርጓል።
በመጠኑም ቢሆን በሂደት ግለቱ እየጨመረ በመጣው ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች ግቦችን ለማግኘት አውንታዊ ሆነው ሲጫወቱ ተመልክተናል ፤ በ27ኛው ደቂቃ ንግድ ባንኮች በረጅሙ የላኩትን ኳስ አማኑኤል ተርፉ በአግባቡ መከላከል አለመቻሉን ተከትሎ አዲስ ግደይ ያገኘውን ኳስ ከባህሩ ነጋሽ ጋር ተገናኝቶ አስቆጠረ ሲባል ወደ ግብ ያደረገውን ሙከራ ባህሩ በግሩም ሁኔታ ሲያድንበት በተመሳሳይ በ29ኛው ደቂቃ ደግሞ ፉዓድ ፈረጃ ከማዕዘን ምት ያሻማውን ኳስ ሳይሞን ፒተር በግንባሩ ገጭቶ ያደረጋትን አስደናቂ ሙከራ ጥሩ የጨዋታ ዕለት እያሳለፈ የነበረው ባህሩ ነጋሽ አድኖበታል።
አልፎ አልፎም ቢሆን ንግድ ባንኮች ላይ ስጋት መደቀናቸውን የቀጠሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በ35ኛው ደቂቃ ዳዊት ተፈራ በግሩም ሁኔታ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተከላካዮች መሀል ያሳለፈለት ኳስ ዳግማዊ አርዓያ ተቆጣጥሮ ወደ ግብ ቢሞክሩም ፍሬው ጌታሁን በግሩም ቅልጥፍና አድኖበታል።
የመጀመሪያ አጋማሽ ወደ መጠናቀቁ ሲቃረብ የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ጫና በስተመጨረሻም ፍሬ አፍርቷል ፤ በ41ኛው ደቂቃ ላይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ከማዕዘን ያሻሙትን ኳስ ሳይሞን ፒተር ያሸነፈውን የመጀመሪያ ኳስ ተከትሎ ባሲሩ ዑመር የሸረፋት ኳስ ባህሩ ነጋሽን አልፋ ከመረብ ተዋህዳለች።
በተሻለ መነቃቃት ጅማሮውን ያደረገ ይመስል የነበረው የሁለቱ ቡድኖች የሁለተኛ አጋማሽ ፍልሚያ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ቶሎ ቶሎ ወደ ማጥቂያው ሲሶ ለመድረስ ፍላጎት የነበራቸው ቢመስልም በማጥቃቱ ረገድ ሁለቱም ቡድኖች የነበራቸው አፈፃፀም እጅግ የተዳከመ ነበር።
በሙከራዎች ረገድ እምብዛም ያልታደለ በነበረው ሁለተኛው አጋማሽ በ76ኛው ደቂቃ ፈረሰኞቹ ተገኑ ተሾመ ከግራ መስመር ሰብሮ በመግባት ባስጀመረውን የማጥቃት ሂደት ተቀይሮ የገባው ረመዳን የሱፍ ግብ ቢያስቆጥርም ግቧ ከጨዋታ ውጭ በሚል ተሽሮባቸዋል።
በ78ኛው ደቂቃ ሙሉ ሶስት ነጥብ ይዘው ለመውጣት ከፍተኛ ጉጉት ውስጥ በነበሩት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በኩል ወሳኙ አጥቂያቸው ሳይሞን ፒተር ብሩክ ታረቀኝን በክርን በመማታቱ መነሻነት በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ የተወገደ ሲሆን ይህም ንግድ ባንክ ቀሪዎቹን ደቂቃዎች በጎዶሎ ተጫዋች እንዲጫወቱ ያስገደደ ሆኗል።
በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ቅዱስ ጊዮርጊሶች አውንታዊ ለውጦችን በማድረግ በአንፃሩ ደግሞ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ደግሞ አሉታዊ ለውጦችን በማድረግ ያከናወኑት ቢሆንም ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች እጅግ ከፍተኛ ጫና አሳድረው የታጫወቱ ሲሆን ባህሩ ነጋሽ እና የቅዱስ ጊዮርጊስ የመከላከል መዋቅር ግን በቀላሉ የሚቀመሱ አልነበሩም በዚህም ጨዋታው በአንድ አቻ ውጤት ተጠናቋል።
ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሁንም በ58 ነጥቦች ሊጉን መምራቱን ሲቀጥል መቻል በአንድ ነጥብ ዝቅ ብለው ወደ መጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች የሚያመሩ ይሆናል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ በተሰጡ አስተያየቶች የቅዱስ ጊዮርጊሱ አሰልጣኝ ደረጀ ተስፋዬ ወጣት ተጫዋቾችን በብዛት እንደመጠቀማቸው የልምድ ማጣት የጨዋታውን ውጤት እንደወሰነው ገልፀው በጨዋታው እንደፈጠሩት ዕድል እና እንዳገኙት የቁጥር ብልጫ ከዚህም የተሻለ ውጤት ይዘው መውጣት ይገባቸው እንደነበረ ገልጿል በአንፃሩ የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ አሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ ከቀሪ መርሐግብሮች ውስጥ የዛሬውን ጨዋታ የተለየ ትኩረት በተጫዋቾቻቸው እንደተሰጠው መታዘባቸውን ገልፀው ጨዋታው በመጀመሪያው አጋማሽ ማለቅ የሚገባው እንደነበረ ያነሱ ሲሆን ከልክ ያለፈ መጓጓት እና ስሜትን መቆጣጠር አለመቻል ወሳኝ ሁለት ነጥብ ለመጣላቸው ምክንያት እንደነበር አንስተዋል አያይዘውም ከምንም በላይ ነገሮች በእጃቸው እንዳሉ ማመን እንደሚገባቸው ገልፀዋል።