ሁለት የፍጹም ቅጣት ምት ግቦች ሀዋሳ ከተማን ከባህርዳር ከተማ ጋር 1ለ1 አለያይተዋል።
በ28ኛው ሳምንት የሊግ ጨዋታቸው ወቅት ሀዋሳ ከተማዎች ከወልቂጤ ከተማ ጋር 2ለ2 በተለያዩበት ጨዋታ ከተጠቀሙት ቋሚ አሰላለፍ በአምስቱ ላይ ለውጥን ሲያደርጉ ጽዮን መርዕድ ፣ ሲሳይ ጋቾ ፣ አማኑኤል ጎበና ፣ ማይክል ኦቱሉ እና እስራኤል እሸቱ ወጥተው በምትኩ ምንተስኖት ጊምቦ ፣ እንየው ካሳሁን ፣ ታፈሠ ሠለሞን ፣ አዲሱ አቱላ እና ቸርነት አውሽ ወደ ሜዳ ገብተዋል። በተመሳሳይ የጨዋታ ሳምንት አዳማ ከተማን ባሸነፉት ባህርዳር ከተማዎች በኩል የአራት ተጫዋቾች ቅያሪ ሲደረግ ያሬድ ባዬ ፣ በረከት ጥጋቡ ፣ ፍሬው ሠለሞን እና ቸርነት ጉግሳ በፍፁም ፍትህአለው ፣ ዓባይነህ ፊኖ ፣ ፍቅረሚካኤል ዓለሙ እና ሀብታሙ ታደሠ ተተክተዋል።
ፌዴራል ዋና ዳኛ ቢኒያም ወርቅአገኘሁ በመሩት የሳምንቱ የመክፈቻ ጨዋታ የመጀመሪያዎቹን አስር ደቂቃዎች ከፍ ባሉ የኮሪደር አጨዋወቶች ጫናን የፈጠሩት ባህር ዳሮች 10ኛው ደቂቃ ላይ መሪ የሆኑበት ግብ አግኝተዋል። የአብሥራ ተስፋዬ ከግራ በኩል ወደ ወደ ጎል የመታትን ኳስ የሀዋሳው ተከላካይ ሠለሞን ወዴሳ በሳጥን ውስጥ ኳስን በእጅ በመንካቱ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ፍቅረሚካኤል ዓለሙ ከመረብ አሳርፎ የጣና ሞገዶቹን ቀዳሚ አድርጓል።
ጨዋታውን ገና በጊዜ መምራት የጀመሩት ባህር ዳሮች በመስመር አጨዋወት በድግግሞሽ የተጋጣሚ ሦስተኛ የሜዳ ክፍል ደርሰው መመልከት ብንችልም የስልነት ችግሮች ግን በጉልህ ቡድኑ ላይ ተንፀባርቋል። ወደ ጨዋታው ለመግባት በእጅጉ ከብዷቸው የሰነበቱት ኃይቆቹ በተለመደው የዓሊ ፈጣን ሽግግር ለመንቀሳቀስ ቢሞክሩም የባህር ዳርን አጥር በቀላሉ መሻገሩ ላይ ግን ዕድለኞች አልነበሩም። ሆኖም 17ኛው ደቂቃ ላይ ከመሃል በረጅሙ የደረሰውን ዓሊ በቀጥታ መትቶ አላዛር ያወጣበት በቡድኑ በኩል የተደረገች ጠንካራ ልትባል የምትችል ሙከራ ሆናለች።
በእንቅስቃሴ ረገድ ቀጣዮቹ ደቂቃዎች የተዳከመ መልክ ቢኖራቸውም በሙከራዎች ረገድ ባህር ዳሮች ሻል ያሉ ነበሩ። በ35ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ፍራኦል አሻምቶ ፍቅረሚካኤል በግንባር ገጭቶ በግቡ ቋሚ ብረት በኩል የወጣችበት እና 45+1 ላይ ፍራኦል ከቅጣት ምት በቀጥታ መትቶ ምንተስኖት ይዞበታል። መደበኛው የጨዋታ ደቂቃ ተጠናቆ በተሰጠው ጭማሪ 45+3 ላይ ወንድወሰን በለጠ ከሳጥን ጠርዝ አክርሮ መቶ የግብ ዘቡ ምንተስኖት ጊምቦ በጥሩ ቅልጥፍና ኳሷን ከያዛት በኋላ አጋማሹ በባህር ዳር መሪነት ተገባዷል።
ከዕረፍት ጨዋታው ሲመለስ ሀዋሳዎች ኢዮብ ዓለማየሁ እና ቸርነት አውሽን አሳርፈው ማይክል ኦቱሉን እና እስራኤል እሸቱን ይዘው ቢመለሱም ልዩነት ለመፍጠር የነበራቸው ርቀት ግን ደካማ ነበር። ቡድኑ የተጫዋች ለውጥን ካደረገ በኋላ ከፍ ባለ ተነሳሽነት ሜዳ ላይ ለመንቀሳቀስ ቢሞክርም የተሻለ ሙከራን ለማድረግ የሚታትሩት በተቃራኒው የጣና ሞገዶቹ ሆነዋል። ወንድወሰን በለጠ ካደረጋት ቀላል ሙከራ መልስ በየአብሥራ ተስፋዬ አደገኛ ሙከራን ያደረጉት ባህር ዳሮች በምንተስኖት ጊምቦ ተመክቶባቸዋል።
ደቂቃ እየገፋ ሲሄድ ተባረክ እና ያሬድን ወደ ሜዳ በማስገባት ጨዋታውን ለመቆጣጠር በተወሰነ መልኩ መነቃቃት የሚታይባቸው ሀዋሳ ከተማዎች እንደነበራቸው መነቃቃት ጥቃት በመሰንዘሩ ረገድ ወረድ ያለ መልክ ነበራቸው። ጥንቃቄ መርጠው ነገር ግን የሚገኙ ዕድሎችን በሽግግር ለመጠቀም ጥረቶች ያልተለያቸው ነጭ ለባሾቹ በ60ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት ፍፁም ጥላሁን በቀጥታ መትቶ ምንተስኖት ካዳናት ኳስ በኋላ ግብ አስተናግደዋል። 79ኛው ደቂቃ ላይ ዓሊ ሱሌይማን በራሱ ላይ መሳይ አገኘሁ ሳጥን ውስጥ የሠራበትን ጥፋት ተንተርሶ የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት በማስቆጠር ሀዋሳን 1ለ1 ማድረግ ችሏል። ጨዋታውም በዛው ውጤት ተጠናቋል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ጨዋታው ተመጣጣኝ መሆኑን ጠቁመው ከዕረፍት በፊት ተጋጣሚያቸው ታክቲካል እንደነበር ፣ መሄድ ባለባቸው ሁሉ ይሄዱ ስለነበር ተቸግረውም እንደነበር ጠቁመው ከዕረፍት በኋላ ግን በቅያሪ ተጫዋቾች ቡድናቸው መስተካከሉን በንግግራቸው አውስተዋል። የባህር ዳር ከተማው ረዳት አሰልጣኝ መብራቱ ሀብቱ በበኩላቸው ረጃጅም ኳሶችን ተጋጣሚያቸው ይጠቀም እንደነበር ጠቁመው ዓሊን ትኩረት ያደረገ አጨዋወት ቢከተሉም ያንን ለመቆጣጠር እንደሞከሩ እና ወደ መጨረሻ ደቂቃ አካባቢ በትኩረት ማነስ በተፈጠረ ችግር ጎል እንዳስተናገዱ ገልጸው በአጠቃላይ ዘጠና ደቂቃው ሦስተኛ የሜዳ ክፍል ላይ ችግሮች እንደታዩባቸው ተናግረዋል።