ኢላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች ብዙም ባልተደረገበት ጨዋታ ኢትዮጵያ መድን በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በተገኘች ግብ ሀዲያ ሆሳዕናን መርታት ችሏል።
በሊጉ ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ኢትዮጵያ መድኖች ከሰባት ጨዋታዎች በኋላ በኢትዮጵያ ቡና ሽንፈት ካስተናገደው የመጀመሪያ ተመራጭ ስብስብ ውስጥ የአምስት ተጫዋቾች ለውጥን ሲያደርጉ በዚህም ሚሊዮን ሠለሞን ፣ አብዱልከሪም መሐመድ ፣ ሰይድ ሐሰን ፣ መሐመድ አበራ እና ጄሮም ፊሊፕ አሳርፈው ዋንጫ ቱት ፣ በርናርድ ኦቼንግ ፣ አዲስ ተስፋዬ ፣ ብሩክ ሙሉጌታ እና አለን ካይዋ ተክተው ሲቀርቡ ድሬዳዋ ከተማን አሸንፈው ወደ ዛሬ ጨዋታ የቀረቡት ሀድያ ሆሳዕናዎች በበኩላቸው ሁለት ለውጦች ሳሙኤል ዮሐንስን በሠመረ ሀፍታይ እንዲሁም ደስታ ዋሚሾን በዳዋ ሆቴሳ ለውጠው ቀርበዋል።
በፌደራል ዋና ዳኛ ሙሉቀን ያረጋል አጋፋሪነት ጅማሮውን ባደረገው የዕለቱ ብቸኛ ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ በፉክክርም ሆነ በግብ ሙከራዎች ረገድ እጅግ የተቀዛቀዘ ነበር።
ቡድኖቹ ሜዳ ላይ ከሚያደርጉት አጨዋወት ውጪ ጨዋታው በብዙ ረገድ የተዳከመ መልክ ነበረው። ጨዋታው ገና ከጅምሩ በ6ኛው ደቂቃ ግርማ በቀለ በጉዳት ምክንያት በመለሰ ሚሻሞ ከተተካበት አጋጣሚ ባለፈ በብዙ መልኩ ትኩረት የሚስቡ ጉዳዮች ባልነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ ኢትዮጵያ መድኖች በአንፃራዊነት ኳስን በማንሸራሸር ከመስመር መነሻቸውን ባደረጉ ሂደቶች ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል በመድረሱ በኩል ተሽለው ቢታዩም ኢላማውን የጠበቀ ሙከራን በማድረጉ ግን እጅጉን ደካሞች ነበሩ።
በአንፃሩ ሀዲያ በዲያ ሆሳዕናዎች በኩል ደግሞ ዳዋ ሆቴሳን ባማከሉ ረጃጅም ኳሶች አልፎ አልፎ ለመጫወት ሙከራዎች የነበሩ ቢሆንም ቡድኑ ሳጥን አካባቢ በቀላሉ የኳስ ፍሰቶቻቸው በመድን ተከላካዮች ሲነጠቅ በተደጋጋሚ ተስተውሏል።
42ኛው ደቂቃ ላይ የመድኑ አጥቂ አለን ካይዋ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ በግራ የሀዲያ ሳጥን ሰብሮ ገብቶ ወደ ግብ የሞከራት እና ሀዲያ ተከላካዮች ተጨራርፋ ከወጣችዋ ኳስ በስተቀር አንድም ጥራት ያለውን ሙከራ ሳንመለከት በብዙ መልኩ ደካማ የነበረው አርባ አምስት ያለ ጎል ተገባዷል።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ሲመለስ ምንም የተለየ የአቀራረብ ለውጥ ሳይኖረው ደካማ በነበረ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ሆኖ የቀጠለ ሲሆን ልክ እንደ መጀመሪያው አጋማሹ ሁሉ እምብዛም ከፉክክር የራቀው የቡድኖቹ ጨዋታ ወጥነት በሌላቸው ቅብብሎች ተሞልቶ ቀጥሏል።
የተጫዋቾች ቅያሬን በማድረግ በመጨረሻዎቹ 20 ደቂቃዎች በመጠኑም ቢሆን የተሻለ ለመንቀሳቀስ የሞከሩት መድኖች በመጨረሻዎች መሻሻላቸው ፍሬ አፍርቷል ፤ 82ኛው ደቂቃ ላይ አብዲሳ ጀማል ወደ ውስጥ ያሻማው ኳስ ሲመለስ በድጋሚ ኳሱን ያገኘው ብሩክ ነፃ አቋቋም ላይ ለነበረው ወገኔ ገዛኸኝ አመቻችቶ የሰጠውን ኳስ ወገኔ ገዛኸኝ በግንባሩ ገጭቶ ቡድኑን አሸናፊ ያደረገችውን ግብ አስቆጥሯል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በተሰጡ አሰተያየቶች የሀድያ ሆሳዕናው አሰልጣኝ ግርማ ታደሠ ጨዋታው ጥሩ እንደነበርና ለሽንፈታቸው ደግሞ በአጥቂው ክፍል ላይ የነበረው የዝግጅት ማነስ እና የጥራት ችግሮች እንደሆኑ አንስተዋል ፤ በአንፃሩ የኢትዮጵያ መድን አቻቸው አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ በበኩላቸው የቡድናወች የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በፈለጉት ልክ አለመሆኑንና ይህም ከሜዳ አስቸጋሪነት ጋር የተያያዘ ስለመሆኑም አንስተው የፈለጉትን ሦስት ነጥብ ማሳካታቸው ግን ዋናው ነገር መሆኑን ጠቁመዋል።