በ29ኛ የጨዋታ ሳምንት የማሳረጊያ መርሃግብር መቻሎች ለቀኑ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ድል ምላሽ ሲሰጡ የዋንጫ ፉክክሩም ወደ መጨረሻው 90 ደቂቃ እንዲያመራ ማድረግ ችለዋል።
አዳማ ከተማዎች በ28ኛ ሳምንት መርሃግብር በባህር ዳር ከተማ ሽንፈት ካስተናገደው ስብስባቸው ባደረጓቸው ሦስት ለውጦች ሰዒድ ሀብታሙ ፣ አቤነዜር ሲሳይ እና ቦና ዓሊን አስወጥተው በምትካቸው በቃሉ አዱኛ ፣ አድናን ረሻድ እና ሱራፌል ዓወልን ሲተኩ በአንፃሩ ሲዳማ ቡና ላይ አራት ግቦችን አስቆጥረው በድል የተመለሱት መቻሎች በአንፃሩ ባደረጉት ብቸኛ ለውጥ በአምስተኛ ቢጫ ባጡት ወሳኙ አማካያቸው ከነዓን ማርክነህ ምትክ አቤል ነጋሽን ተክተው ወደ ዛሬው ጨዋታ ቀርበዋል።
ከበላያቸው ያለው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ማሸነፍን ተመልክተው ወደ ሜዳ የገቡት መቻሎች ገና በማለዳ ነበር ምላሽ መስጠት የጀመሩት ፤ 5ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ደስታ የአዳማ ከተማው የቀኝ መስመር ተከላካይ ጀሚል ያዕቆብ ላይ ጫና ፈጥሮ የነጠቀውን ኳስ በረከት ደስታ ወደፊት እየገፋ በመግባት ከሳጥኑ ጠርዝ በግሩም ሁኔታ በደካማ እግሩ አክርሮ የመታት ኳስ የግቡን አግዳሚ ለትማ ከመረብ ተዋህዳለች።
ከፈጣኑ አጀማመር በኃላ በተወሰነ መልኩ ወጣ ገባ እያለ በቀጠለው ጨዋታ መቻሎች ይበልጥ ወደ ግራ መስመር አድልተው ጥቃቶችን ለመሰንዘር ሲጥሩ በአንፃሩ አዳማዎች ኳሱን ተቆጣጥረው ዕድሎችን ለመፍጠር ሙከራ ሲያደርጉ ተስተውሏል በዚህም ሂደት በ18ኛው ደቂቃ አድናን ረሻድ ያገኘው እና ከግቡ በላይ የሰደዳት አጋጣሚ ተጠቃሽ ነበረች።
በ20ኛው ደቂቃ ግን መቻሎች መሪነታቸውን አሳድገዋል ፤ በጥሩ የቅብብል ሂደት ወደ አዳማ ሳጥን ያደረሱትን ኳስ ሽመልስ በቀለ ለምንይሉ ወንድሙ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ የአዳማው የመስመር ተከላካይ አህመድ ረሺድ ኳሷን አቋርጣለው በሚል ያደረገው ጥረት ሳይሳካ ኳሷ ወደራሱ ግብ ተቆጥራለች።
ከግቧ በኋላ ይበልጥ ተጨማሪ ግብ ፍለጋ ጫና ማድረጋቸውን የቀጠሉት መቻሎች ከመጀመሪያው አጋማሽ መጠናቀተቀቅ አስቀድሞ በ28ኛው ደቂቃ ሽመልስ በቀለ በቀጥታ ከቅጣት ምት ያደረገው ሙከራ ፣ በ33ኛው ደቂቃ በረከት ደስታ ከግራ መስመር ወደ ውስጥ ሰብሮ በመግባት ወደ ግብ ያደረገው ሙከራ እንዲሁም 40ኛው ደቂቃ በኃይሉ ግርማ ከሳጥን ውጭ በቀጥታ ያደረገው እና በቃሉ አዱኛ ያዳነበት ኳስ ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ።
ሁለተኛውን አጋማሽ አቤነዜር ሲሳይ ፣ ታዬ ጋሻው እና ቦና ዓሊን ቀይረው በማስገባት የጀመሩት አዳማዎች ያደረጓቸው ቅያሬዎች የተፈለገውን ለውጥ ግን ሜዳ ላይ ያመጡ አልነበሩም ፤ ግቦችን ይፈልግ የነበረው ቡድን የአጋማሹን ቀዳሚ ሙከራ በ61ኛው ደቂቃ በጀሚል ያዕቆብ አማካኝነት ያደረጉት ዒላውን ያልጠበቀ ሙከራ ነበር።
እንደ መጀመሪያው አጋማሽ በተጋጣሚ የሜዳ አጋማሽ ጫና ማሳደራቸውን የቀጠሉት መቻሎች በሁለተኛው አጋማሽ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ግን ዕድሎችን መፍጠር የቻሉበት አልነበረም።
ፍፁም በተቀዛቀዘ መልኩ በቀጠለው የሁለቱ ቡድኖች የሁለተኛ አጋማሽ ጨዋታ በ77ኛው ደቂቃ ሦሰትኛ ግብ ተቆጥሮበታል ፤ በቀኝ የሳጥን ጠርዝ ሽመልስ በቀለ ከሳሙኤል ሳሊሶ የተቀበለውን ኳስ በአስደናቂ የቴክኒክ ክህሎት ሁለት የአዳማ ተጫዋቾች አልፎ በበቃሉ አዱኛ አናት ላይ ባስቆጠራት እጅግ አስደናቂ ግብ መቻሎች አሸናፊነታቸውን አረጋግጠዋል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ አስቀድመው ያስተናገዷቸው ግቦች ጨዋታውን እንዳከበደባቸው ገልፀው ሁለተኛ አጋማሽ ነገሮችን ለማስተካከል ሙከራ እንዳደረጉ እና በእንቅስቃሴ ረገድ በሁለተኛው አጋማሽ የተሻሉ እንደነበሩ ገልፀዋል ፤ አያይዘውም የዛሬው ጨዋታ ውጤት ሌሎች ቡድኖች ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ ስላለ ተጫዋቾችን እንደፈለጉት ለውጠው እንዳይሞክሩ እንዳደረጋቸውም ተናግረዋል። በአንፃሩ የመቻሉ አለቃ ገብረክርስቶስ ቢራራ ጨዋታው እንደፈለጉት እንደሄደላቸው ገልፀው አሁንም ቢሆን ከንግድ ባንክ ውጤት ይልቅ የራሳቸውን የቤት ስራ ስለመወጣት ብቻ እንደሚጨነቁ ገልፀው የራሳቸውን የቤት ስራ በመወጣት የሚወጣውን ውጤት ለመቀበል ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል።