ቻምፒዮኖቹ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን መቼ ይጀምራሉ?

ኢትዮጵያን በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ውድድር የሚወክለው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ሊጀምር ነው።

የ2016 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊ ክለብ የሆነው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቀጣዩ ዓመት የሊጉ ውድድር ከመጀመሩ በፊት ላሉበት የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎች ዝግጅቱን ለመጀመር እየተሰናዳ ይገኛል። በአሠልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ የሚመራው ቡድኑ በዝውውሩ ራሱን ለማጠናከር አብዱልከሪም መሐመድ እና ቢኒያም ካሣሁንን አስፈርሟል።

በቻምፒየንስ ሊጉ የዩጋንዳ ፕሪምየር ሊግ ሻምፕዮኑ ቪላን የሚገጥመው ክለቡ በዛሬው ዕለት በአዳማ ከተማ በመሰባሰብ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን እንደሚጀምር ታውቋል። ሁሉም የቡድኑ አባላት ዛሬ ከቀትር በፊት በካኖፒ ሆቴል ተሰባስበው አስፈላጊ ዝግጅቶች ከተደረጉ በኋላ በነገው ዕለት መደበኛ ልምምድ እንደሚጀምሩ ተጠቁሟል።