መቐለ 70 እንደርታ ሁለት ተጫዋቾች ለማስፈረም ተስማምቷል።
ቀደም ብለው ሸሪፍ መሐመድ እና ያሬድ ከበደን ለማስፈረም የተስማሙት መቐለ 70 እንደርታዎች አሁን ደግሞ ቀናት ከፈጀው ድርድር በኋላ ግብ ጠባቂው ሶፈንያስ ሰይፈ እና ያሬድ ብርሃኑን ለማስፈረም ከስምምነት ደርሰዋል።
ያለፈውን አንድ ዓመት በከፍተኛ ሊጉ ከሚጫወተው ንብ ጋር የቆየው እና በውድድር ዓመቱ በሁለት መርሐግብሮች የጨዋታው ኮከብ ተብሎ መመረጥ የቻለው ግብ ጠባቂው ሶፎንያስ ሰይፈ ከዚህ ቀደም በደደቢት ወጣት እና ዋናው ቡድን ቆይታ የነበረው ሲሆን በ2009 አጋማሽ መቐለ 70 እንደርታን ከተቀላቀለ ወዲህ ቡድኑ ወደ ፕሪምየር ሊግ እንዲገባ ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ተጫዋቹ ምዓም አናብስት የሊጉን ዋንጫ ሲያሳኩም የስብስቡ አንድ አካል የነበረ ሲሆን አሁን ደግሞ ከዓመታት በኋላ ወደ ፕሪምየር ሊጉ በመመለስ የቀድሞ ክለቡን ለመቀላቀል ተስማምቷል።
ሌላው ቡድኑን ለመቀላቀል የተስማማው ደግሞ የመስመር ተጫዋቹ ያሬድ ብርሃኑ ነው። ባለፈው የውድድር ዓመት ኢትዮ ኤሌክትሪክን ወደ ፕሪምየር ሊግ ካሳለፈ ስብስብ አንድ አካል የነበረው ይህ ተጫዋች ከዓመታት በኋላ ወደ አሳዳጊ ክለቡ መቐለ 70 እንደርታ ለመመለስ ከስምምነት ደርሷል። ከዚህ ቀደም በሁለት አጋጣሚዎች ለመቐለ 70 እንደርታ፣ ደደቢት፣ ወልዲያ፣ ወልዋሎ፣ ሰሜን ሸዋ ደብረብርሃን እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ መጫወት የቻለው ይህ ተጫዋች ለሦስተኛ ጊዜ እናት ክለቡን ለማገልገል መስማማቱን ተከትሎ ከዓመታት በኋላ በፕሪምየር ሊጉ የምናየው ይሆናል።
ከዚ ቀደም ቡድኑን ያገለገሉት ያሬድ ከበደ፣ ሶፎንያስ ሰይፈ እና ያሬድ ብርሃኑን ጨምሮ ከአራት ተጫዋቾች ጋር የተስማሙት መቐለዎች በቀጣይ ቀናት ከሁለተኛው ቡድን ተገኝተው ላለፈው አንድ ዓመት ቡድኑን በማገልገል የቆዩትን በርከት ያሉ ተጫዋቾች ውል እንደሚያራዝምም ለማወቅ ተችሏል።