ኢትዮጵያ ቡና ወሳኙን ጨዋታ በሜዳው እንደሚያደርግ አስታወቀ

ቡናማዎቹ የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የቅድመ ማጣሪያ የሜዳ ላይ ጨዋታቸውን በአበበ ቢቂላ ስታዲየም እንደሚያደርግ በማኅበራዊ ገፃቸው ይፋ አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ዋንጫን ማሸነፉን ተከትሎ ሀገሩን ወክሎ በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የሚሳተፈው ኢትዮጵያ ቡና ከኬንያ ፖሊስ ጋር የሚያደርገው የማጣርያው ሁለተኛ ጨዋታ በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስቴድየም እንደሚያከናውን ክለቡ ይፋ አድርጓል። ክለቡ ከፊቱ ለሚጠብቁት የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ እና የካፍ ኮንፌዴሬሽን ቅድመ ማጣርያ ጨዋታ ይረዳው ዘንድ መቀመጫውን አዳማ ከተማ በማድረግ ዝግጅቱን በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ስታዲየም በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ገልፆ ነሐሴ 19 የሚካሄደው የመልስ ጨዋታ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም እንደሚያከናውን እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት እንዲሁም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ላደረጉት ትብብር ምስጋና አቅርቧል።

ቀድም ብሎ ከሀገሩ ውጭ ጨዋታውን እንደሚያከናውን ጠቅሶ የነበረው የኬንያ ፖሊስም በተመሳሳይ የመጀመርያውን ጨዋታ በናይሮቢ ንያዮ ስታዲየም እንደሚያደርግ መረጃዎች እየወጡ ይገኛሉ ፤ ጨዋታውም ነሐሴ 12 ይካሄዳል።