የቢንያም ፍቅሬ ዝውውር ከምን ደረሰ?

ከቀናት በፊት በግብፅ ክለቦች ተፈልጎ ወደ ካይሮ ያቀናው ቢንያም ፍቅሬ የዝውውር ሂደቱ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል?

የወላይታ ድቻው አጥቂ ቢኒያም ፍቅሬ ከቀናት በፊት በግብፅ ክለቦች የሚያደርገውን ዝውውር መልክ ለማሲያዝ ካይሮ እንደሄደ ከዚህ ቀደም ባቀረብነው መረጃ መግለፃችን ይታወቃል። አሁን በግብፅ የሚገኘው ወኪሉ አዛርያስ ተስፋፂሆን እንደነገረን ከሆነ ከሁለት ቀናት በኋላ የቢንያም ፍቅሬ የዝውውር ሁኔታ መቋጫ ያገኛል።

እርሱን ያለ ሙከራ ለማስፈረም የመጀመርያው ፈላጊ ክለብ እስማኤሊያ ቢንያምን ለመውሰድ ለቀናት ያደረገውን ድርድር እንዳጠናቀቀ እና በዚህ ሁለት ቀን ውስጥ ክለቡ በማኀበራዊ ትስስር ገፁ ዝውውሩን ይፋ እንደሚያደርግ ተገልጿል።

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ በማድረግ በሊጉ ላይ ከደመቁ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው ቢንያም ፍቅሬ ከሳላዲን ሰዒድ ፣ ሽመልስ በቀለ፣ ዑመድ ኡኩሪ፣ ጋቶች ፓኖም እና አቤል ያለው በመቀጠል በግብፅ ሊግ መጫወት የቻለ ስድስተኛ ኢትዮጵያዊ ተጫዋች ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።