ባህር ዳር ከተማ የመጀመሪያ ተጫዋቹን አስፈርሟል

የጣና ሞገዶቹ የቀድሞ ተከላካያቸውን ዳግም ወደ ስብስባቸው ቀላቅለዋል።

በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በ50 ነጥቦች 4ኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ባህር ዳር ከተማ ዛሬን ጨምሮ ያለፉትን ቀናት የሦስት ነባር ተጫዋቾቹን ውል ማደሱን መግለፃችን ይታወሳል። ክለቡ አሁን ደግሞ ፊቱን ወደ ተጫዋቾች የዝውውር መስኮት በማዞር የመጀመሪያ ፈራሚውን ማግኘቱ ታውቋል።

ባህር ዳርን የተቀላቀለው የመጀመሪያው ተጫዋች ወንድሜነህ ደረጄ ነው። የቀድሞ የአራዳ ክፍለ ከተማ እና ሱሉልታ ተጫዋች የነበረው ተከላካዩ ከዚህ ቀደም በውሃ ሰማያዊው ቤት ግልጋሎት የሰጠ ሲሆን ያለፉትን አምስት ዓመታት ደግሞ ወደ ቡናማዎቹ ቤት አምርቶ የእግርኳስ ህይወቱን ቀጥሏል። ተጫዋቹ አሁን ውሉ መጠናቀቁን ተከትሎ ዳግም ወደ ቀድሞ ክለቡ በሁለት ዓመታት ውል የተመለሰበትን ዝውውር ከደቂቃዎች በፊት አገባዷል።