አርባምንጭ ከተማ የወሳኙን አማካይ ውል አራዘመ

የበርካታ ነባሮችን ውል እያራዘመ የሚገኘው አርባምንጭ ከተማ የአማካዩን ውል አድሷል።

በአሰልጣኝ በረከት ደሙ እየተመሩ ወደ አዲስ ዝውውር ከመግባታቸው አስቀድሞ በክለቡ የነበሩ ነባሮችን ውል በማደስ የተጠመዱት አዞዎቹ እስከ አሁን ዘጠኝ ነባር ተጫዋቾችን የውል ዘመናቸውን ያራዘሙላቸው ሲሆን አሁን ደግሞ የወሳኙ አማካይ እንዳልካቸው መስፍንን ውል ለተጨማሪ ዓመት አራዝመዋል።

እግር ኳስ በጋሞ ጨንቻ ክለብ ውስጥ የጀመረው የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ ወደ አርባምንጭ ከተማ ካመራ በኋላም ያለፉትን አራት የውድድር ዘመናት ለቡድኑ ግልጋሎት እየሰጠ የሰነበተ ሲሆን ከክለቡ ጋር አብሮ በመውረድ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ዳግም የተመለሰ ሲሆን የከፍተኛ ሊጉ የዓመቱ ኮከብ ተጫዋች ሆኖም ተመርጧል። አማካዩ ውሉ መጠናቀቁን ተከትሎ በበርካታ ክለቦች ሲፈለግ ቢቆይም በነባር ክለቡ አርባምንጭ ውሉን አራዝሟል።