ኢትዮ ኤሌክትሪክ ወደ ዝውውሩ ገብቷል

ዳግም ወደ ሊጉ የተመለሰው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ወደ ዝውውሩ በመግባት ስድስት ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታን ከሾመ በኋላ ነባሮችን እና አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ቡድኑ በማምጣት የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ ቆይቷል። በዚህም ሂደት ስድስት ተጫዋቾችን ማስፈረሙ ታውቋል።

ግብ ጠባቂው አሸብር ተስፋዬ የክለቡ አዲስ ፈራሚ ነው። ከዚህ ቀደም በጎፋ ባሬንቺ፣ በፌደራል ፖሊስ፣ በጅንካ እና በየካ ክ/ከተማ የተጫወተ ሲሆን ያለፉትን በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በምርጥ አቋም በነገሌ አርሲ ቆይታ ያደረገ መሆኑ ሲታወቅ ዘንድሮ በከፍተኛ ሊጉ ኮከብ ግብጠባቂ በመባል መሸለሙ ይታወቃል።

ሁለተኛው ፈራሚ አማካይ በፍቃዱ አስረሳኸኝ መሆኑ ታውቋል። ቀድሞ በዱራሜ ተጫዋች የነበረው እና በሀምበሪቾን ከከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪሚየር ሊግ በማሳደግ ቁልፍ ሚና የነበረው በፍቃዱ ዘንድሮም በሊጉ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ማድረጉ ይታወሳል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክን የተቀላቀለው ሦስተኛ ተጫዋች ተከላካይ ዲንግ ኪያር ነው ይህም ተጫዋች ዘንድሮ በሀምበሪቾ ቡድን ውስጥ ጥሩ ተከላካይነት መሆኑን አሳይቷል። ሌላው ቡድኑን የተቀላቀሉት በጅማ አባ ጅፋር ቆይታ የነበረው ገለታ ሃይሉ እንዲሁም አማካይ ሄኖክ ገብረህይወት ዘንድሮ በጅማ አባ ጅፋር ሲጫወት የቆየ ሲሆን ከዚህ ቀደም በኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ20 ዓመት በታች ቡድን ውስጥ በአንበልነት ያገለገለ ሲሆን ዳግም ወደ ቀድሞ ቤቱ መመለስ ችሏል።

ቡድኑን የተቀላቀለው ስድስተኛ ፈራሚ የቀኝ መስመር ተከላካዩ አብዱላዚዝ አማን ሲሆን ከዚህ በፊት በቢሸፍቱ በባቱ ከተማ እና ዘንድሮ በቤንች ማጂ ቡና ጥሩ ጊዜ ካሳለፈ በኋላ በመጨረሻም መዳረሻው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሆኗል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ስድስቱንም ተጫዋች ለሁለት ዓመት ያስፈረመ ሲሆን በቀጣዮቹ ቀናት በሊጉ ከፍተኛ ልምድ ያለቸውን ተጫዋቾች ወደ ማዘዋወር እንደሚገባ ከክለቡ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።