የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ክለቦች ማዘዋወር የሚችሉት የውጪ ተጫዋቾች ቁጥር ከሦስት ከፍ እንዲል ውሳኔ ተላልፏል።
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አምስት የነበረውን የሊጉ ክለቦች ማዘዋወር የሚችሉት የውጪ ተጫዋቾችን ብዛት ለሀገር ውስጥ ተጫዋቾች ዕድል ለመስጠት በሚል ከ2014 ጀምሮ ቁጥሩን በመቀነስ ሦስት ማድረጉ ይታወሳል።
ዛሬ ደግሞ ወቅታዊ የእግርኳሱ ሁኔታን በማገናዘብ እና የሊጉን ደረጃ ለማሳደግ እንዲያስችል ከዚህ የዝውውር ጊዜ ጀምሮ ክለቦች ማዘዋወር የሚችሉት የውጪ ዜጋ ተጫዋች ቁጥር 5 እንዲሆን ተወስኗል።
በውሳኔው መሰረት ክለቦች የሚያስፈርሙት በአፍሪካ ሊግ የሚጫወት ተጫዋች ከሆነ በዋና ሊግ ደረጃ የሚጫወት ተጫዋች መሆን የሚኖርበት ሲሆን ከአፍሪካ ሊግ ውጪ የሚጫወት ከሆነ በየትኛውም የሊግ ደረጃ የሚጫወት ተጫዋችን ማስፈረም የሚችሉ ይሆናል። በተጨማሪም ክለቦች የውጪ ዜጋ ተጫዋቾችን በአንድ ጨዋታ ያለ ገደብ ማጫወት እንደሚችሉ ፌዴሬሽኑ ገልፆል።